የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና በማደራጀት ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ የጸጥታ ተቋም ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል:: ልዩ ኃይሎችን በፌዴራልና የክልሎች የጸጥታ ተቋማት ውስጥ መደራጀቱ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው:: ልዩ ኃይል በመከላከያ፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልሎች ፖሊስ ስር እንዲደራጅ መደረጉ በዋናነት ሶስት ትላልቅ ፋይዳዎች አሉት የሚል እምነት አለኝ::
በመጀመሪያ ደረጃ ልዩ ኃይሎች በተለያዩ ጊዜያት ከመከላከያ ጎን በመቆም የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመቀልበስ የተጫወተው ሚና የሚካድ አይደለም:: በምስራቁ የአገራችን አካባቢ የአልሸባብን እንቅስቃሴ በመግታት እንዲሁም በቅርቡ በሰሜኑ የአገራችን አካባቢ በተከሰተው ጦርነት ከመከላከያ ጎን በመሆን የክልሎች ልዩ ኃይሎች የራሳቸውን ሚና እንደተጫወቱ ይታወቃል::
የክልሎች ልዩ ኃይሎች በአገራችን የህግ የበላይነት ስብራት እና ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዋነኛ ስጋት ተዋናዮች የሆኑባቸው አጋጣሚዎችም አልጠፉም:: በአንዳንድ አጋጣሚዎች የክልሎች ልዩ ኃይሎች ከህግ ማዕቀፍ ውጪ የመንቀሳቀስ አዝማሚያዎች ታይተዋል::
በአንዳንድ አጋጣሚዎች ህገ ወጥ ተግባራት ላይ ጭምር መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ያወጧቸው ሪፖርቶች አመላክተዋል:: ይህ ኃይል በጊዜው ተገርቶ የክልል እና የፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ውስጥ እንዲካተት ባይደረግ ለዜጎች ደህንነት ሳይሆን ስጋት ምንጭነታቸው እየጨመረ መሄዱ አይቀሬ ነበር:: እነዚህ ኃይሎች የክልሎች አመራሮችን ድጋፍ የሚያገኙ እንደመሆናቸው ያለተጠያቂነት እርምጃዎችን ሲወስዱ ተስተውለዋል::
ይህ ደግሞ የህግና ስርዓት መፈራረስ ሊያስከትል ይችላል:: በረጅም ርቀት ደግሞ አገሪቱን አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሊከታት ይችላል:: ይህ መሰል አስከፊ አደጋዎችን ሳያስከትል መስመር እንዲይዝ መደረጉ ለዜጎች እና ለአገሪቱ ሰላምና ደህንነት ከፍ ያለ ጠቃሜታ አለው::
በሁለተኛ ደረጃ የክልሎች ልዩ ኃይሎች በክልሎች ውስጥ የሚገኝ አብዛኛውን ብሄር በሚመስል መልኩ የተደራጁ ነበሩ:: በክልሎች ውስጥ የሚገኙ ህዳጣን ተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም:: በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ብዝሃነት በሚያንጸባርቅ መልኩ አለመደራጀታቸው አልበቃ ብሎ በክልሎች ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የማያንጸባርቁ መሆናቸው የበለጠ አሳሳቢ መዋቅር ያደርጋቸዋል:: እነዚህ ልዩ ኃይሎች በክልሎች ማንነት ላይ ተመስርተው አገሪቱን ሊከፋፍሉ እንደሚችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው::
እነዚህ ኃይሎች ከፌዴራል መንግስት የተለየ አቋም፣ ዓላማና ግብ ሊኖራቸው በሚችል የክልሎች ባለስልጣናት የሚዘወሩ እንደመሆናቸው ታማኝነታቸውም ክልሉን ለሚመራ አካል ነው:: ይህ ደግሞ አገሪቱ እና የአገሪቱ የጸጥታ መዋቅር በብሄር እንዲከፋፈል ከማድረጉ ባሻገር ታማኝነታቸው ለተለያዩ አካላት የሆኑ የታጠቁ ኃይሎች በአንድ አገር ውስጥ እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው::
ይህ በክልሎች መካከል ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ፣ በክልሎች የጸጥታ መዋቅሮች እና እና በፌዴራል መንግስት የጸጥታ መዋቅሮች መካከል መጠነኛ ግጭቶች እንዲቀሰቀስ ምክንያት ከመሆን አልፎ አገሪቱን የለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሊከታት ይችላል:: ኢትዮጵያ ከእርስ በርስ ጦርነት ገና በመላቀቅ ላይ ያለች አገር ነች:: አሁን የክልሎች ልዩ ኃይሎችን ዳግም ለማደራጀት እየተደረገ ያለው ጥረት የእርስ በርስ ግጭት ምዕራፍን ለመዝጋት እና ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር እገዛው ከፍ ያለ ነው::
በሶስተኛ ደረጅ ልዩ ኃይሉ ዳግም የማደራጀት ስራ በፍጥነት ባይሰራ እኩይ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች የክልሎች ልዩ ኃይሎችን የፌዴራል መንግስቱን ህጋዊነት ለመናድ ሊጠቀሙበት ይችላል:: የፌዴራል መንግስቱ ህጋዊነት ሲናድ እና ሲዳከም እነዚህ ኃይሎች አካባቢዎችን ወደ መቆጣጠር የመሄድ አዝማሚያ ሊኖራቸው ይችላል:: ይህ ደግሞ የፌዴራል መንግስቱን ከጥቅም ውጪ ሊያደርግ እና አገሪቱን የክልሎች ኃይሎች እጅ ስር ሊያደርጋት የሚችል ነው::
ሲጠቃለል የክልል ልዩ ኃይሎች አገር አንድነት ስጋት የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነበር:: እነዚህ ኃይሎችን ዳግም የማደራጀት ስራ ባይሰራ መለያየትን በመፍጠር የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን መናድ እና የህግ የበላይነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችሉ ነበር:: የክልል የጸጥታ መዋቅር ሀሳቡ ጠቃሚ ቢሆንም እነዚህ ኃይሎች በፌዴራል መንግስት እና በፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ መደረጉ ወቅታዊ እና የብዙ ጊዜያት የአገራችን ህዝቦች ጥያቄ የነበረ ነው:: የክልሎች ብሎም የጥቂት ብሄሮች ጠባብ ፍላጎቶች አገራዊ ጥቅምን እንዲያናጋ ሊፈቀድ አይገባም::
የፌዴራል መንግስት ልዩ ኃይሎችን ዳግም ለማደራጀት የጀመረው እርምጃ የአገሪቷ አንድነት እና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ያለውን የላቀ ፋይዳ በመገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መንግስት የጀመረውን የጸጥታ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ስራ ከዳር እንዲያደርስ እገዛ ሊያደርግ ይገባል:: የክልሎች ልዩ ኃይሎችን ዳግም ለማደራጀት የሚደረገውን ጥረት ሌላ ትርጉም በመስጠት ህዝቡን የሚያደናግሩ አካላት ከተግባራቸው ሊቆጠቡ ይገባል::
የፌዴራል መንግስት የክልሎች ልዩ ኃይሎችን መልሶ በማደራጀት በመከላከያ፣ ፌዴራል እና የክልሎች ፖሊስ መዋቅር ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር የጸጥታ መዋቅሮች ውስጥ መካተት ለማይፈልጉት እና ሌላ ስራ ላይ የመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል:: የተሃድሶ ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ አምራች ዘርፍ እንዲሰማሩ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል:: ከዚህ ጎን ለጎን ልዩ ኃይሎች እንደገና በመደራጀታቸው ምክንያት በክልሎች ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ለመሙላት መደበኛውን ሰራዊት የማጠናከር ስራ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል::
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 11 ቀን 2015 ዓ.ም