ሰላም ከሚኖረው ሁለንተናዊ ጠቀሜታ አንጻር የትኛውም ማኅበረሰብ /ሕዝብ ለሰላም ልዩ ዋጋ ይሰጣል። ለሰላም ዋጋ ለመክፈልም ያለው መሻት፤ የሰላም እጦት ሊያስከትል ከሚችለው ሰብአዊና ቁሳዊ ከዛም ባለፈ ስነልቦናዊና መንፈሳዊ ስብራት አንጻር ሁሌም ከፍያለ ነው።
በተለይም በየወቅቱ ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ ዋጋ ለመክፈል የሚገደዱ ሕዝቦች፤ ስለ ሰላም የሚኖራቸው መሻት የሚመነጨው ትናንት የሰላም እጦት ካስከፈላቸው ዋጋ በመሆኑ፤ ሰላማቸውን ለመጠበቅና አጽንቶ ለማቆም የማንንም ምክርና ጣልቃ ገብነት የሚፈልጉ አይደሉም።
ለችግሮቻችው ራሳቸው መፍትሄ ሆነው ለመቆም ሆነ፤ ከችግሮቻችው በላይ ሆነው ፈተናዎቻቸውን ለመሻገር የሚበቁ፤ በዘመናት በተለያዩ ውጣ ውረዶች የተፈተኑ፤ ስለ ሰላም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከመጮኸ ባለፈ፤ አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል አቅም የሚሆኑ ትናንቶች ባለቤት ናቸው።
ከነዚህ ሕዝቦች መካከል የጎረቤት አገር ሱዳን ወንድም ሕዝብ አንዱ ነው። የሱዳን ሕዝብ በተለያዩ ወቅቶች ሰላሙን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም እንደ ሕዝብ ሰላም ወዳድ፤ ስለ ሰላሙም አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል ሁሌም ራሱን ያዘጋጀ፤ ለዚህም የሚሆነው ቁርጠኝነት ያዳበረ ሕዝብ ነው።
የውስጥ ችግሮቹን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በራሱ የመፍታት አቅም እና ጥበብ ያለው፤ በዚህም እንደ አገርና ሕዝብ ጸንቶ መቆም የቻለ፤ ወደ ፊትም ጸንቶ መቆም የሚያስችሉ የዳበሩ መንፈሳዊ፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ እሴቶች ባለቤትም ነው። አሁን ላይ ያጋጠመውን ችግር በነዚህ ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ እሴቶች መፍታት የሚያስችል ማኅበረሰባዊ ቁመና ያለው፤ ትናንት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ የሰላም እጦቶች ከከፈላቸው አላስፈላጊ ዋጋዎች ብዙ ተምሮ፣ ዛሬዎቹን ብቻ ሳይሆን ነገዎቹ ላይ ትልቅ ተስፋ ሰንቆ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት መንገድ የጀመረ ሕዝብ ነው።
ይህ ሕዝብ ለሰነቀው ትልቅ ተስፋ የሰላም አስፈላጊነት የቱን ያህል አልፋና ኦሜጋ እንደሆነ ያውቃል፤ ይህንን እውነታ ለመረዳት የማንንም አስተርጓሚነት ሆነ ጣልቃ ገብነት አይፈልግም፤ ተስፋውና ለዘመናት የዳበረው ግጭት መፍቻ እሴቱ ከሁሉም በላይ ስለሰላሙ ዘብ እንዲቆም ያስገድደዋል።
የሱዳን ሕዝብ ለሰላም ያለው ቁርጠኝነት ከቋንቋ ያለፈ፤ ለአገሩ ካለው ፍቅር የሚመነጭ፤ ትናንት ላይ ተፈትኖ ፍሬ አፍርቶ የታየ፤ ስለነገም የተሻለ ተስፋ ሰንቆ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ መግቢያ በር ላይ እንዲቆም ያስቻለው ነው።
ኢትዮጵያውያን ወንድም የሆነው የሱዳን ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ነፃነቱን የሚወድ፤ ብሔራዊ ክብሩን አስጠብቀው የቆየ ከመሆኑ አንጻር፤ አሁን ላይ ያጋጠመውን ችግር ነጻነቱን እና ብሄራዊ ክብሩን በሚመጥን መልኩ በሰላማዊ ውይይትና ድርድር በራሱ አቅም ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ይፈታዋል ብለን እናምናለን።
አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት የሚያስችል የተሟላ አቅም እንዳላቸው፣ ትናንት ላይ ከራሳችን ተሞክሮ በተጨባጭ መማር እንደቻልን ሁሉ፤ ከሱዳን ወንድም ሕዝብ ጋር ከምንጋራቸው ሰፊ መንፈሳዊ፣ ባህላዊ እና ማህበራዊ እሴቶች አኳያ ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት እንደሚችሉ አብዝተን እንተማመናለን።
ይህ ከሱዳን ወንድም ሕዝብ ማህበራዊ ማንነት የሚመነጭ ስብእና አሁን እንደ ሕዝብ ያጋጠሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ መሻገር የሚያስችል ብቸኛ አቅም ነው፤ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም በሱዳን ሰላም ለማስፈን የሚያደርጋቸው የትኞቹም ዓይነት ጥረቶች ከሁሉም በላይ ለዚህ አቅም ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 11 ቀን 2015 ዓ.ም