ከስድስቱ የፕላቲኒየም ደረጃ ካላቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል የቦስተን ማራቶን ከትናንት በስቲያ ተካሂዷል:: ከውድድሩ አስቀድሞ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከፍተኛ የውጤታማነት ግምት ባገኙበት በዚህ ሩጫ የአየር ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም በሴቶች እንዲሁም በፓራሊምፒክ ስኬት ተመዝግቧል:: ቀዝቃዛና ዝናባማ በነበረው ሩጫ አትሌት አጽበሃ ገብረመስቀል በፓራሊምፒክ እንዲሁም አትሌት አማኔ ጎበና በሴቶች ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል::
የመጀመሪያውን ዘመናዊ ኦሊምፒክ መካሄድ ተከትሎ በፈጠረው ተነሳሽነት የቦስተን ማራቶን በቀጣዩ ዓመት እንዲዘጋጅ ተደረገ:: እአአ ከ1897 አንስቶ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ማራቶን ከዓለም በጥንታዊነቱ ከቀዳሚዎቹ መካከል የሚቀመጥ ሲሆን፤ በዓለም አትሌቲክስ ቀዳሚ ከሚባሉት ስድስት ማራቶኖች ውስጥ አንዱ ነው:: በርካታ ታሪካዊ ሁነቶችን በ127ቱ ዓመታት ያስተናገደው ውድድሩ የዚህን ዓመት ሩጫውንም ከትናንት በስቲያ አካሂዷል::
በየዓመቱ በአርበኞች ቀን የሚካሄደው ይህ ውድድር በተለያዩ ምድቦች ውድድሩን ያካሄደ ሲሆን፤ በፓራሊምፒክ ውድድርም ኢትዮጵያዊው አትሌት ለመጀመሪያ ጊዜ ውጤታማ ሊሆን ችሏል:: 30ሺ ሯጮች ከ18 አገራት የተሳተፉበት ይህ ውድድር፤ ለመዝናናት ከሚሮጡት ባሻገር የዓለም እና የኦሊምፒክ ቻምፒዮናዎች፣ የክብረወሰን ባለቤቶች፣ በቦስተን ማራቶን አሸናፊ የነበሩ አትሌቶች እንዲሁም ፓራሊምፒክ ተወዳዳሪዎች ተካፍለውበታል::
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያዊው አትሌት አጽበሃ ገብረመስቀል በእጅ ጉዳት የፓራሊምፒክ ዘርፍ ተወዳድሮ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል:: ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው ይህ አትሌት በሪዮ ፓራሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ የተወዳደረ ሲሆን፤ በተሳተፈበት የ1ሺ500 ሜትር ርቀት 9ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው:: አዳጋች በነበረው በዚህ ውድድርም ሞሮኳዊውን አትሌት ተከትሎ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል:: አትሌቱ ሩጫውን ለመፈጸም የፈጀበት ሰዓትም 02:43:57 ሆኖ ተመዝግቦለታል::
ከ2ሰዓት ከ21 ደቂቃ በታች ሰዓት ያላቸው 16 የማራቶን አትሌቶች በተካፈሉበት የሴቶቹ ውድድር፤ አሸናፊ የሆነችው ኬንያዊቷ አትሌት ሄለን ኦቤሪ ናት:: ጥቂት ሰከንዶችን ብቻ ዘግይታ በመግባቷ በውድድሩ ሁለተኛ ደረጃን መያዝ የቻለችው አትሌት ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አማኔ በሪሶ ናት:: ጠንካራ ከሆኑ የማራቶን አትሌቶች መካከል ተጠቃሽ የሆነችው አትሌቷ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2:21:50 የሆነ ሰዓት ነው የፈጀባት:: ቫሌንሺያ ማራቶንን 2:14:58 በመሮጥ ሦስተኛውን ፈጣን የማራቶን ሰዓት ያስመዘገበችው አማኔ በሪሶ፤ የኢትዮጵያ የማራቶን ባለ ክብረወሰንም ናት::
ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቦስተን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው አትሌት አባበል የሻነህ ለአሸናፊነት ሰፊ ግምት የተሰጣት ቢሆንም፤ በአራተኛነት ነው የገባችው:: ይህንንም ተከትሎ አትሌቷ ‹‹ያለፈው ዓመት የቦስተን ማራቶን አስደናቂ ነበር፤ ሩጫው በሚካሄድበት ጎዳና የነበረው ድጋፍ የሚረሳ አይደለም:: ዘንድሮም ለማሸነፍ ተዘጋጅቼ ነበር ወደ ውድድሩ የገባሁት፤ ሆኖም ጥቂት ሜትሮች ላይ ተሸነፍኩ›› ስትል ሁኔታውን አስረድታለች::
ሌላኛዋ ተጠባቂ አትሌት ሕይወት ገብረማርያም በበኩሏ 8ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ ችላለች:: ያለፈው ዓመት ኦሪገን ላይ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አሸናፊ የነበረችውና በዚህ ውድድርም ድሉን ትደግመው ይሆናል በሚል እጅግ ትጠበቅ የበረችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጎይተቶም ገብረሥላሴም እንዳሰበችው ሳይሆን 10ኛ ደረጃን ይዛ ሩጫዋን ፈጽማለች::
ክብረወሰን አሊያም አስደናቂ ፉክክር ይታይበታል በሚል ተጠባቂ የነበረው ይህ ውድድር በዓለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤቱ ኢሉድ ኪፕቾጌ ይመራ ነበር:: ለአሸናፊነቱም ከእርሱ የበለጠ ግምት የተሰጠው አልነበረም፤ ይሁንና የዕለቱን የአየር ሁኔታ መቋቋም ባለመቻሉ ስድስተኛ ደረጃን ለመያዝ ተገዷል:: አስቸጋሪ በነበረው በዚህ ውድድር ከኬንያውያን አትሌቶች እኩል ግምት አግኝተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወንድ አትሌቶችም ስኬታማ መሆን አልቻሉም::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2015