ለክፍለ ዘመን የተጠጋ እድሜ እንዳለው ይነገራል፤ የቅርጫት ኳስ ስፖርት:: ጅማሮውን በአሜሪካ ያደረገው ይህ ስፖርት በዚህ ወቅት በስፋት ከሚዘወተሩ ስፖርቶች ጎራ መሰለፍ ችሏል:: ስፖርቱ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች መስፋፋቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቀድመው ከተቀላቀሉ የአፍሪካ አገራት ቀዳሚ ነች:: እአአ በ1949 ዓለም አቀፉን የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በአባልነት ከመቀላቀል ባለፈ፤ የአፍሪካ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ቻምፒዮናን ከመሰረቱት አባል አገራትም ተጠቃሽ ናት::
ይህም በቅርጫት ኳስ ረጅም ታሪክና ልምድን ያካበተች አገር ያሰኛታል:: ስፖርቱን በኢትዮጵያ ያስተዋወቁት ከካናዳ የመጡ የሰውነት ማጎልመሻ መምህራን መሆናቸው ይነገራል:: ከዚያን ወዲህም በአዲስ አበባ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲስፋፋ፤ ቀስ በቀስም ዳብሮ በበርካታ የኢትዮጵያን ክፍሎች ሊዘወተር ችሏል:: የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ብሄራዊ ቡድን በአንድ ወቅት ከአፍሪካ ምርጥ ቡድኖች አንዱ መሆን ቢችልም ከ1960ዎቹ ወዲህ ግን ተዳክሞ በዓለም አቀፍ ውድድሮችም መሳተፍ ቅንጦት ሆኖባታል::
የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ብሄራዊ ቡድኑን ወደ ቀደመ ዝናው ለመመለስ ጽኑ ፍላጎት ቢኖረውም ችግሮች እንደገጠሙት አስታውቋል:: ፌዴሬሽኑ በበርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፍ ግብዣ ቢደረግለትም በፋይናንስ እጥረት ምክንያት መሳተፍ አልቻለም:: በዓለም አቀፍ ውድድሮች በሁለቱም ጾታዎች ከታዳጊዎች እስከ አዋቂዎች ውድድሮች ሲኖሩ እድሉን ለመጠቀም ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የበጀት ድጋፍ እንዲደረግለት ቢጠይቅም
ሊመለስለት አልቻለም:: ይልቁንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዶላር እጥረት ስላለበት ድጋፍ ለማድረግ እቸገራለው የሚል መልስ እንደሰጠውም ፌዴሬሽኑ ጠቅሷል:: ነገሩን አዳጋች ያደረገውም ለአንድ ውድድር ምዝገባ ብቻ ከ6ሺ ዶላር በላይ ማስፈለጉ ነው::
የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት አሳምነው፤ እንደ አገር የተዘጋጀና በየቀኑ ስልጠና የሚወስድ ባይሆንም ፌዴሬሽኑ ብሄራዊ ቡድን እንዲኖር እቅድ እንዳለው ያብራራሉ:: ነገር ግን እቅዱን ለማስፈጸም ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ገጥሞታል:: እንደ አቶ ዳዊት አስተያየት ሁሉንም ስፖርት በእኩል የማየት ልምድ የለም:: እንደ እግር ኳስና አትሌቲክስ የመሳሰሉ ስፖርቶች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲኖሩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያነሱት ኃላፊው ለሌሎች ስፖርቶችም መሰል ድጋፎችን በማድረግ እኩል ማየት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል::
ሁሌም በምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት ቅርጫት ኳስ የሚካፈለው ብሄራዊ ቡድኑ ዘንድሮም ተሳታፊ ለመሆን መንግስት የፋይናንስ እገዛን ማድረግ እንደሚገባውም ኃላፊው አንስተዋል:: ምክንያቱም ከመሰል ችግሮች በቀር በወንድም ሆነ በሴት በታዳጊ እንዲሁም በአዋቂ ለብሄራዊ ቡድን የሚበቁ ተጫዋቾች አሉ:: በሌላ በኩል በመንግስት የሚመደበው ዓመታዊ በጀት እስከ አሁን አልተለቀቀም፤ በመሆኑም ፌዴሬሽኑ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ከክለቦች ምዝገባና ከስፖንሰር በሚያገኘው ገንዘብ ነው:: የአገር ውስጥ ውድድሮችንም እየመራ የሚገኘው ከደጋፊ አካላት በሚያገኘው ገንዘብ ነው:: በቀጣይም ፌዴሬሽኑ ብሄራዊ ቡድኑን ለረጅም ጊዜ ስፖንሰር የሚያደርጉትን ተቋማት ለማግኘት እቅድ ይዞ እየሰራ ይገኛል::
ፌዴሬሽኑ ካስቀመጣቸው ዕቅዶች መካከል ስልጠናና ውድድር ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ አንዱ ነው:: የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪምየር ሊግም ሁለተኛ ዙር ተጠናቆ ሶስተኛ ዙር ውድድሩን ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ነው:: የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በሜዳና ከሜዳ ውጪ የሚደረጉ ውድድሮች ቀርተው የዙር ውድድሮችን መደረግ መጀመሩን አቶ ዳዊት ይጠቁማሉ::
ክለቦቹ ተቀራራቢ ነጥብ ስላላቸው ውድድሮች በገለልተኛ ሜዳዎች እንዲካሄዱ ተደርጓል:: ቀሪ ሶስት ጨዋታዎችም በተመሳሳይ በገለልተኛ ሜዳ የሚደረጉም ይሆናል:: ገለልተኛ ሜዳዎቹ ሲመረጡም የቅርጫት ኳስ ከፍተኛ አቅም ያለባቸውን ስፍራዎች ማዕከል በማድረግ ነው::
በመስክ ምልከታ በተገኘ ግብዓትም የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ እንዲሳተፍ መደረጉንም ፌዴሬሽኑ ጠቅሷል:: በመሆኑም አራተኛውን ዙር በጋምቤላ ለማድረግ በእቅድ ደረጃ ተይዟል:: እንደ ጋምቤላ፣ ደቡብ እና ምስራቅ ኢትዮጵያ የስፖርቱ አቅም ባለባቸው ስፍራዎችም ውድድሮችን ተዟዙሮ በማድረግ ጥሩ ስፖርተኞችን ለማግኘት እንደሚሰራም ኃላፊው ጠቁመዋል::
በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪምየር ሊግ በወንዶች አምስት ክለቦች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ በሴቶች ደግሞ አራት ክለቦች ተካፋይ ናቸው:: ክለቦቹ በአንድ ዙር በአጠቃላይ 16 ጨዋታዎችን የሚያደርጉም ይሆናል::
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2015