በበዙ ትናንቶች ድልድይ እየተሸጋገረ ዘመናትን አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል። ትናንትናን በዛሬ እየቃኘ ዛሬ ደግሞ አዲስ ዘመን ድሮ እያለ ኋላውን በትዝታ ይቃኛል፡፡ አዲስ ዘመን ድሮ ምን ይመስል ነበር…ቆየት ካሉ የአዲስ ዘመን ትዝታዎች ቀንጨብጨብ እያደረግን እንቃኛቸዋለን፡፡ በወሊድ ላይ ሳሉ ሕይወታቸው ባለፈ አንዲት ሴት ምክንያት ሆስፒታሎች ተወዛገቡ…ይለናል፤ በሻላ ሐይቅ ማዕድናት ተገኙ እንዲሁም ደግሞ በመዲናችን አዲስ አበባ በአንድ የአፍሪካ መሪ ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎ ነበር..ለመሆኑ ይህ መሪ ማነው..በዚሁ የግድያ ሙከራ ላይ በተሳተፉ ሦስት ወንጀለኞች ላይ ደግሞ የሞት ፍርድ ስለመፈረዱ የወጡ ዜናዎችን እንዲሁም የማህበረሰቡ የውስጥ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥያቄዎች ከሚቀርቡበት መፍትሄ ቢሆንዎ(?) ገጽ ላይ አንዲት ሀሳብ በማካተት አቅርበንላችኋል።
በወሊድ ላይ ሕይወታቸው ባለፈው ሴት ምክንያት ሆስፒታሎች ተወዛገቡ
ባለፈው ከየካቲት ወደ ጥቁር አንበሳ የተላኩ ወይዘሮ ገኔ ሽኩር የተባሉ ነፍሰ ጡር ሴት ሕይወታቸው የማለፉ ምክንያት ሕክምና ሳይደረግላቸው በመቅረቱ ነው ሲሉ ቤተሰቦቻቸው ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ ሆስፒታሎች ግን የግለሰቧን አማሟት አንዱ በአንዱ በማሳበብ ተወዛገቡ፡፡ በአዲስ አበባ በወረዳ 4 የቀበሌ 59 ነዋሪና የሟቿ ባለቤት የሆኑት አቶ ሸምሱ ሙደሲር ባለቤታቸው ነሐሴ 28 ቀን 1989 ዓ.ም ሌሊት ድንገት ስለታመሙባቸው ወደ የካቲት 12 ሆሰፒታል የወሰዷቸው መሆኑን ገልጠው፣ ነገር ግን የዕለቱ ተረኛ በወቅቱ የሕክምና እርዳታ ለማድረግ የማይችሉ መሆናቸውን ስለነገሩአቸው ወዲያውኑ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል መውሰዳቸውን አመልክተዋል፡፡
(አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 1989ዓ.ም)
በሦስቱ አሸባሪዎች ላይ የሞት ቀጣት ተበየነ
(ኢ.ዜ.አ) የግብጹን ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን አዲስ አበባ ላይ ለመግደል የሞከሩና ሁለት ኢትዮጵያውያንን ገድለው ሦስቱን ያቆሰሉ አሸባሪዎች በሞት እንዲቀጡ ትናንት ያስቻለው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ፡፡ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ እንዳስታወቀው ሰውፊት ሃሰን፣ አብዱል ቃኒ፣ አብዱል ከሪም አብዱልናዲና አልአረብ ሳዲቅ ሃፊዝ በተባሉ ግብጻውያን ላይ ቅጣቱ የተበየነው አቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ማስረጃ በዝግ ችሎት ላይ ሲመለከት በነበረው ፍርድ ቤት በመረጋገጡ ነው፡፡
አሸባሪዎቹ ለወንጀሉ አፈጻጸም የሚረዱ የጦር መሣሪያዎችንና ፈንጂዎችን በሱዳን አየር መንገድ አስጭነው በአዲስ አበባ የአየር መንገድ ጽሕፈት ቤት እንዳኖሩና ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችንም ከአገር እንደገዙ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን አቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡን የገለጠው ይሄው የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ፣ የሥራ ክፍፍል በማድረግ መኪናና ቤቶች በመከራየት አቅደው መንቀሳቀሳቸውንም የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ መቅረቡን አስረድቷል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 1989ዓ.ም)
በሻላ ሐይቅ ማዕድንና ኬሚካል አለ ተባለ
(ኢ.ዜ.አ) በስምጥ ሸለቆ በሚገኘው ሻላ ሐይቅ እስካሁን ጥቅም ላይ ያልዋለ ከ388 ሚሊዮን ቶን በላይ ሶዳ አሽ ማዕድንና የሶዲየም ክሎራይድ ኬሚካል እንዳለ መረጋገጡን የአብያታ ሶዳ አሽ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡ ሥራ አስኪያጁ አቶ ታከለ ውቤ እንዳመለከቱት 1987ዓ.ም የውጭና የአገር ውስጥ ባለሙያዎች ሐይቁ ላይ ባካሄዱት ጥናት የሶዳ አሽ ማዕድን ክምችትና በአምስተኛ ደረጃ ደግሞ ሶዲየም ክሎራይድ ኬሚካል መኖሩ ተረጋግጧል፡፡
(አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 1989ዓ.ም)
በአንድ የመናዊ ላይ ተደራራቢ ክሶች ተመሰረቱ
(ኢ.ዜ.አ) በሕግ ያልተፈቀደላቸውን የመንግሥት መሬት ተመርተዋል፣ በሕገ ወጥ ካርታ ከባንክ 10 ሚሊዮን ብር ተበድረዋል፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀደ የባንክ ሥራ ላይም ተሳትፈዋል በተባሉ አንድ የመናዊ ላይ አቃቤ ሕግ ክስ መሠረተ። ምክትል ረዳት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሳህሉ ገብረየስ ትናንት ለኢዜአ እንዳስታወቁት፣ ግለሰቡ በተለያዩ ደረጃ ላይ ከነበሩ ባለሥልጣናት ጋር በጥቅም በመጎዳኘት ፋብሪካዎችን አቋቁማለሁ በሚል 463 ሺህ 380 ካሬ ሜትር በቡራዩ እንዲሁም 86ሺህ ካሬሜትር መሬት በቃሊቲ ከተሞች ያለ በቂ የፕሮጀክት ጥናት ወስደዋል። በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል የተባሉ ባለሥልጣናት ተከሰዋል።
አቃቤ ሕጉ እንደሚሉት ግለሰቡ “ከቀበሌ ሹሞች ጋር በመመሳጠር ደስ ሲላቸው አህመድ አብዶ፣ ሌላ ጊዜ አህመድ ረመዳን ወይንም አህመድ አብዶ አልረመዳን ሲያሻቸው ደግሞ አህመድ አብዶ መሃመድ በማለት በአራት ስሞች በተለያዩ የእድሜ ዘመናት በተነሷቸው ፎቶግራፎችና መታወቂያዎች ይጠቀማሉ። በዜግነትም አንዴ የመናዊ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ ይላሉ”። በተመሠረተው ክስ መሠረት ግለሰቡ በተዘጋጁላቸው የተለያዩ ስሞችና መታወቂያዎች በቡራዩ አካባቢ አቶ አህመድ አብዱ አልረመዳን፣ በአቃቂ ደግሞ አህመድ አብዶ መሃመድ ተብለው ለሕዝብና ለመንግሥት ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኙ የሚችሉ ሰፋፊ የመንግሥት ቦታዎችን ከልለው በመያዝ ተደራራቢ ወንጀሎች ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
(አዲስ ዘመን መጋቢት 24 ቀን 1988ዓ.ም)
መፍትሄ ቢሆንዎ(?)
የሚስቴን እህት ምከሩልኝ
ጥያቄ እኔ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ። ባለቤቴ በአሁኑ ወቅት ያለችው ውጭ አገር ነው። ከሕፃንነቷ ጀምሮ ያሳደኳት የባለቤቴ እህት ግን የምትኖረው እኔ ጋር ሲሆን የ14 አመትና የ8ኛ ክፍል ተማሪም ሆናለች። በጣም አስቸጋሪ እድሜ በመሆኗ ባለቤቴ በነበረች ጊዜም ሆነ ዛሬ ከመምከር አልተቆጠብኩም። እሷ ግን ባሰባት። ይልቁንስ ጎረምሶች ይዛ ወደቤት እየመጣች በኢኮኖሚ ትጎዳኛለች። ወደቤተሰቦቿ እንዳልካት አቅጣጫዋን ቀይራ ለጉዳት ትዳረጋለች ብዬ ሰጋሁ። እኔ ጋር እንዳትቆይም ላልተፈለገ እርግዝና፣ ለአባላዘር በሽታና ለኤድስ እንዳትዳረግ ፈራሁ። እና ምን ባደርግ ይሻለኛል?
ዘለቀ ባንጀቱ ከአዲስ አበባ
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2015