አዲስ ዘመን ድሮ

አዲስ ዘመንን ይዞ ምን ጎድሎ እንዲሉ ነውና የዛሬው “አዲስ ዘመን ድሮ” የተለያዩ፤ ምናልባትም የሚያዝናኑ ርእሰ ጉዳዮችን ጭምር ይዞ ቀርቧል። በተለይ የአዳኞች “የማእረግ ስም” እና “ሹመት”፣ ማህበራዊ ስፍራቸው፤ የኢራኑ ንጉሥ፣ የጫጉላ ሽርሽራቸውና የጦርነቱ ድግስ በትውስታ ፈገግ ያደርጋሉና እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ጆሞ ኬንያታ

በዚህ ወር ውስጥ ስለ ኬንያ ሕገ መንግሥት ጉዳይ በለንደን በሚደረገው ስብሰባ ላይ የቀድሞው የማኦ ማኦ መሪ ጆሞ ኬንያታ ተካፋይ እንዲሆን መንግሥቱ ባይፈቅድም ቅሉ ከኬንያታ አንድ ማስታወሻ በአፍሪካ ምክር ቤት አባሎች በኩል ወደ ለንደን ይላካል ሲሉ የኪኪዩ መሪ ዶክተር ጊኮንም አስታውቀዋል።

የሰባቱ አውራጃ የፖለቲካ ማህበር መሪዎች ባደረጉት ስብሰባ ላይ ለንደን ላይ በሚደረገው ስብሰባ ተካፋዮች ለሚሆኑት ለአፍሪካ መልእክተኞች መሪ ጆሞ ኬንያታ መሆን አለበት ያለ በለዚያ ግን ምንም አይነት ስብሰባ አይደረግም ሲሉ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

በዚህም ምክንያት ለአፍሪካ መልእክተኞች መሪ እንድትሆን ተመርጠሃል የሚል ቴሌግራም ለጆሞ ኬንያታ የተላከ መሆኑ ታውቋል።

(ጋዜጣው በዚሁ ዐቢይ ርእስ ስር የሚከተለውን ንኡስ ርእስ አያይዞ አቅርቧል።)

 አፍሪካ ከአሥር ዓመት በኋላ

የታንጋኒካ ናሲዮናሊስት መሪ በቢቢሲ ሲናገሩ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ አፍሪካ በሙሉ ነፃ ትወጣለች ካሉ በኋላ አፍሪካ በሙሉ ነፃ ከሆነች በኋላ የውጭ ሀገር ተወላጆች (ነጮች) በአፍሪካ እንዲቀመጡ ትፈቅዳላችሁን? በማለት ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ በእርግጥ ይፈቀድላቸዋል፤ ብለዋል።

(አዲስ ዘመን፣ ታህስ 30 ቀን 1952 ዓ/ም)

አደንና አዳኝ

ምንም እንኳን በሀገራችን በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በሌላው ዓለም ውስጥ የሌሉ በጣም ብርቅዬ የሆኑ የዱር እንስሳት ቢገኙም፤ ከጥንቱ ጋር ሲወዳደር ግን በቁጥርም ሆነ በአይነት በጣም አናሳ መሆናቸው በተለያዩ ጊዜያት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ክፍሎች ተገልጿል። ለዚህም የዱር እንስሳት ቁጥር እያቆለቆለ መሄድ ዋነኛው ምክንያት ኋላ ቀር የነበረው ሥርዓት የወለደው ልማድና ወግ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ባለፉት መቶ ዓመታትና ከዚያም በፊት ባህሉ በፈጠረው መሠረት በህብረተሰቡ ውስጥ ሙያቸውን አደን ያደረጉ ሰዎች እንደ አደኑት እንስሳ አይነትና መጠን ከህብረተሰቡ ልዩ ክብርና ሙገሳ ስለሚሰጣቸው ነው። ለአብነትም ያህል የሚከተለውን እንመልከት።

ሀ• ዝሆን ገዳይ – አዳኙ 40 ሰው እንደ ገደለ ይቆጠርለታል።

ለ• አውራሪስ ገዳይ – አዳኙ 15 ሰው እንደ ገደለ ይቆጠርለታል።

ሐ• አንበሳ ገዳይ – አዳኙ 5 ሰው እንደ ገደለ ይቆጠርለታል።

መ• ቀጭኔ ገዳይ – የቀጭኔ ገዳይ ሚስት በውሃ መቅዳት ላይ ቅድሚያ ይሰጣታል።

ሠ• ግሥላ ገዳይ – ግስላ ገዳይ ሳይፎክር ቀድሞ የሚነሳ የለም።

ረ• ተኩላ ገዳይ – ሌሎች ገዳዮች እየፎከሩ ሳሉ ተኩላ ገዳይ ቢነሳ ሁሉም ዝም ይላል።

ሰ• ነብር ገዳይ – ነብር እሰው አጥር ጊቢ ገብቶ ሴት ገደለችው የሚል ንግርት ስላለ ገዳዩ ለ15 ቀን ብቻ ቅቤ ይቀባል።

(አዲስ ዘመን፣ መስከረም 9 ቀን 1980 ዓ/ም)

ኢራክና ኢራን

ኢራክና ኢራን “ሻቴል ዓረብ” በተባለው የባህር ዳርቻ ምድር የተነሳ የወሰን ግጭት አንስተዋል፤ “ሻቴል ዓረብ” የጤግሮስና የኤፍራጥስ ወንዞች” “ፔርሺያን ጋልፍ” ከተባለው የባህር ሰላጤ ጋር በሚገናኙበት ቦታ ላይ የሚገኘው ክፍለ ሀገር ነው። በዚህ ስፍራ አቅራቢያ የኢራን ዋና የዘይት ማውጫ ማእድን ይገኝበታል፤ ነገር ግን የኢራክ መንግሥት በዚህ ስፍራ ውስጥ 3 ማይል ያህል ስፋት ያለው መሬት የኔ ነው ስትል ሃሳቧን ገልጣለች፤ በዚህ ምክንያት በዚህ ወሰን አጠገብ የኢራን መንግሥት የመከላከያ ኃይሏን ማከማቸት ይዛለች።

ኮራማሻይር በተባለ ታላቅ የንግድ ወደብ ዙሪያ ብዙ የጦር ኃይል በዚህ ከተማና በኤባዳን ከተማ ዙሪያ ተጠራቅሟል። የባህሩን ሰላጤ እያለፉ ወደ ጤግሮስና ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ የሚሄዱት የንግድም ሆኑ የመንገደኛ መርከቦች በኢራን ጠረፍ ሲደርሱ እየተፈተሹ ነው እንጂ እንዲያው መተላለፍ አይቻልም፤ መከላከያው ኃይል በተከማቸበት ስፍራ ወታደሮች እንጂ ሲቪል ሊተላለፍ አይችልም፤ ፈቃድ የተሰጣቸው ወታደሮች ሁሉ በንቃት ታጥቀው እንዲጠባበቁ ተደርጓል።

ኢራክም በበኩሏ ይህንን ነገር ተመልክታዋለች፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሜጀር ጀነራል ቃሲም “ኢራን ፀብ በማንሳት ሠላምን ለማጥፋት ተነሥታለች፤ ለሚመጣው ሁሉ ሃላፊነቱ የኢራን ነው። እስካሁን ድረስ ወደ ወሰኑ የጦር ኃይል (አላክንም)፤ ወረራ ከመጣብን ግን ወራሪ ጠላታችንን ለማጥፋት ደቂቃ እንኳን አይወስድብንም፤ በወሰናችን ላይ የጦር ኃይል አለማከማቸታችንን መላው ዓለም ይመሰክርልናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢራን ንጉሥ ግን 3ኛ ሚስታቸውን ካገቡ ገና ስምንት ቀን ሆናቸው፤ ንግሥቲቱን ይዘው የጫጉላ ጊዜአቸውን ለማሳለፍ ወደ ካስፒአን ባህር ጠረፍ ሄደዋል፤ ንጉሡ ለ10 ቀን ያህል ከሙሽራዪቱ ጋር ሲያድኑ፣ ፈረስ ሲጋልቡና በጀልባ ሲንሸራሸሩ እንደሚቆዩ ተነገረ። ንጉሡና ሙሽራዪቱ ወደ ካስፒአን ባህር መሄዳቸው በኢራንና በኢራክ መካከል ያለው ግጭት የማያሰጋ መሆኑን ያመለክታል።

(አዲስ ዘመን፣ ታህሳስ 21 ቀን 1952 ዓ/ም)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም

Recommended For You