በርካታ ፀሀፍት አዲስ ዘመን የዜጎችን ሁሉ ስሜት ሲያንፀባርቅ እንደኖረ ከትበዋል። የገበሬውም ሆነ ነጋዴው፤ የወንዱም ሆነ ሴቱ፤ የተማሪውም ሆነ አስተማሪው፤ በተለይም የጦር ሠራዊቱ ሁሉ • • • አንደበት-ልሳን እንደ ነበር በህትመቶቹ ላይ በግልፅ ይታያል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ለማሳያ ያህል በዚህ አምድ ላይ ለማስታወስ እየሞከርን እንዳለነው ጋዜጣው በተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሳይታክት በብቸኝነት መረጃ ሲያቀብል ኖሯል። ዛሬም ከሀገር ፍቅር እስከ • • • ድረስ ያሉ ሀሳቦች የተካተቱበት የትውስታ ዝግጅት እንደሚከተለው ቀርቧል።
የዶላርን ነገር ጠንቀቅ
ኢንተርፖል የተባለው አለም አቀፍ የፖሊስ ድርጅት የዩናይትድ ስቴት የገንዘብ ሚኒስቴር የባንክ ኖቶቹን ባዲስ እንዲቀይር ምክር ለግሶታል። ለዚህ የተሰጠው አቢይ ምክንያት ከዩናይትድ ስቴት ጀምሮ በሁሉም የአለም ክፍሎች የውሸት ዶላሮች በዝውውር ላይ መገኘታቸው ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እነዚህ የባንክ ኖቶች ስራ ላይ ከዋሉ ጀምሮ 12ሺህ የውሸት ዶላር “ሠዓሊያን” ወይም “አታሚ” ወንጀለኞች ለፍርድ ቀርበዋል። ይህ ቁጥር በዓለም ያሉትን የመስኩን ወንጀለኞች 90 በመቶ ያካተተ መሆኑን የፓሪስ ሌሞንድ ጋዜጣ ዘግቧል። እኛም የውጭ ንግዳችን በዚሁ የአሜሪካን ገንዘብ ስለሆነ ግርዱን ከፍሬው ለመለየት ጠንቀቅ ነዋ!
(አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 14 ቀን 1980 ዓ•ም)
***
በሬው ባለቤቱን ከጅብ አዳነው
(ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ)
በጨርጨር አውራጃ ጭሮ ወረዳ ያብዶ ኮሎሎ በተባለው ቀበሌ በአቶ ወጋየሁ ወንድማገኘሁ መሬት ላይ እያረሰ የሚኖር አቶ ሙሳ ቡቲ የተባለ ገበሬ፤ሰኔ ፲፭ ቀን ፲፱፻፷ ዓ/ም ከሌሊቱ ፰ ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ በአንደኛው ቤት ውስጥ ካሉት ከብቶች መካከል አንዲት ፍየል ጅብ ጐትቶ ሲያወጣት ባለቤቱ ነቅቶ ጅቡን ሲከላከል ሆዱን ነከሰው፣ ሰውየውም የጅቡን አፍንጫውንና አገጩን አፍኖ ሲይዘው ሆዱን ለቆ የቀኝ ባቱን ነክሶ ፲፭ ሜትር ያህል ጐትቶ ሊበላው ሲተናነቅ የጥቁር ጋርማ ጐባ በሬ እውጭ ከታሠረበት ገመዱን በጥሶ ጅቡን ተከታትሎ በማባረር ባለቤቱን ከመበላት ያተረፈው መሆኑንና ሰውየውም በልዑል ሣህለ ሥላሴ ሆስፒታል ታክሞ የዳነ መሆኑን አቶ ወጋየሁ አስረድተውናል።
(አዲስ ዘመን ሐምሌ 7 ቀን 1960 ዓም)
*****
ኢትዮጵያ በፀጥታ ምክር ቤት መቀመጫ እንዲሰጣት ጠየቀች
ከተባበሩት መንግሥታት ኢትዮጵያና ሞሪታንያ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ አሁን በተባበረው ዓረብ ሪፑብሊክ የተያዘ የመካከለኛው መሥራቅ (ሥፍራ መቀመጫ) ለእኛ ይገባል ሲሉ ውድድር አቅርበዋል በማለት ከኒውየርክ የተገኘ ወሬ አስታውቋል።
ለምዕራበውያኑ አውሮፓ ክፍልና ለመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሆኑ ጠቅላላ ስምምነት ተደርሶባቸው የነበረው መቀመጫዎች፤ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ለማግኘት በመከራከር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ሌሎች መቀመጫውን ለመያዝ የሚወዳደሩ አገሮች ኢራን ሞሮኮና አፍጋኒስታን እንደሆኑ ታውቋል።
(አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 ቀን 1954 ዓ.ም)
*****
ይፍረድብኝ • • •
ምድርሽ ትፍረድ • • • እፅዋትሽ፤
ለምለም ስፍራሽ • • • ውብ አበባሽ፣
እናት አለም ጡት አጥብተሽ • • • አሳድገሽ
ተንከባክበሽ • • • ሁሉን አድርገሽ፣
ባለሽ አቅም • • • አስተምረሽ፣
እናት ምድሬን • • • እንዴት ልክዳሽ፣
እስኪ አዳምጭኝ እማምዬ
አንቺ እናቴ
ትቼሽ ብሄድ • • • ኮብልዬ
ይለወጣል እኔነቴ?
እዚያም ብሄድ • • • እዚያም ብደርስ፣
መልኬ ያው ነው አፍሪካዊ
የታወቅሁ ጥቁር ኢትዮጵያዊ
በቀውጢ ወቅት • • • በችግርሽ
አንችን ትቼ • • • አንችን ልሽሽ?
በብልፅግናሽ • • • በሀብትሽ ወቅት
ስትላቀቂ • • • ከረሀብ • • • ከድህነት
ዙሬ ላይሽ • • • ልመለስ?
ያፈራሽውን • • • ፍሬ ልቀምስ?
ምድርሽ ይፍረድ • • • የጎመራው
ወንዝሽ ይፍረድ • • • የምጠጣው
ማሳደግሽን • • • ማስተማርሽን
ይህን ዐቢይ • • • ውለታሽን
በዜግነቴ • • • ባለኝ አቅም
ውለታሽን • • • አልመልስም?
የጠጣሁት የበላሁት • • • ትዝ አይለኝም?
ወንዝ ጅረትሽ • • • ይፍረድብኝ
ዳገት ቁልቁለቱ • • • ዋጥ ያድርገኝ
የድንበር አጥርሽ • • • አንቆ ይድፋኝ
ፍርዴን ላግኝ • • • የሞት ቅጣት
ወገን ይያት • • • የኔን ሕይወት
አንችን ብተው • • • አንችን ብክድ
ብኮበልል • • • ብጓዝ ብሄድ።
(ሀብቱ በላይ)
(አዲስ ዘመን፣ ታህሳስ 5 ቀን 1979 ዓም)
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም