አዲስ ዘመን ድሮ

ዛሬ ለማስታወስ የመረጥናቸው የአዲስ ዘመን ቀደምት ዘገባዎች በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ ያነሳናቸው ነጥቦች ከበርካታ ጉዳዮች ጋር የሚያገናኟቸው ወፋፍራምም፣ ቀጫጭንም ክሮች ስላሏቸው በዛ መልኩ ይነበቡ፡፡ ጋዜጣውም ያኔን ካሁን ጋር በማያያዝ ሚናው ይታወስ ዘንድ እያሳሰብን ወደ ይዘቶቹ እንሄዳለን። ከዛ በፊት ግን 1980ን ከሁሉም ልዩ የሚያደርገው አንድ መሠረታዊ ጉዳይ የነበረ ሲሆን፤ እሱም በቅርቡ በሞት የተለየው አሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ መሪነት ኢትዮጵያ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ዋንጫን እራሷ አስተናጋጅ፤ እራሷም ዋንጫውን ወሳጅ በመሆኗ ምክንያት መላው ኢትዮጵያ ከደስታም በላይ በሆነ ደስታ የፈነጠዘችበት ልዩ ዓመት ነበርና ያንን የማይረሳ ታላቅ ድል ከጨዋታው በፊት ዋንጫው የእኛ ይሆን ዘንድ የተመኘውን ከሳምንት በኋላም ድሉን ተከትሎ የቀረበን ሌላ ግጥም እናስታውሳለን፡፡

ጠጅ ይመርመር

ሀገራችን የተለያዩ የባሕል ምግቦች እና መጠጦች ይገኙባታል። ከእነዚህም አንዱና ተወዳጁ የባሕል መጠጥ ጠጅ መሆኑ ይታወቃል። ጠጅ ሲዘጋጅ ከማር ሆኖ ጌሾ ብቻ እንደሚደባለቅበት ስለሚታወቅ ሌላ ቅመም ይታከልበታል የሚል ጥርጣሬ አልነበረም።

ይሁንና የጠጅ የጓዳ ምስጢር ከሆነና ለጠጅ ኃይል ለመስጠት (እንዲያሰክር) የተለያዩ ነገሮች እንደሚገቡበት ከተወራ ሰንበት ብሏል። በጠጅ ውስጥ ስለሚደባለቁት ኃይል ሰጭ ነገሮች እውቀት ባይኖረንም የጠጅ አጣጣል “ህቡዕ” ከወረደ ብዙ ጊዜ መሆኑን እናውቃለን።

ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በየእለቱ የሚጎነጩት ይህ መጠጥ [ጥንቃቄ] ከጎደለው ምን ያህል ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

በጠጅ ውስጥ የሚጨመረውን ውሕድ በዓይን በማየት ለመለየት አስቸጋሪ ስለሆነ የጤና ተቆጣጣሪዎች ለናሙና ጠጅን እየወሰዱ በዘመናዊ መሣሪያ መመርመርና መቆጣጠር አስፈላጊ ይመስለኛል። ይህም ጠጪዎችን ግፉበት ለማለትና ለመገፋፋት ሳይሆን የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ ከሚደረገው ጥረት አኳያ መታየት የሚገባው ነውና የጤና ተቆጣጣሪዎች የብርሌን ንፅሕና ብቻ ሳይሆን ውሃውንም ሊመረምሩት ይገባል እላለሁ።

(መክት ጋሻዬ፣ አዋሳ፣ አዲስ ዘመን፣ ጥር 18 ቀን 1980 ዓ•ም)

በእሳት የመቃጠል አደጋ

የእሳት ቃጠሎ አደጋ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ይመጣል። አብዛኛውን ጊዜ የሚመጣው በፈላ ውሃ፣ ዘይትና ቅባት ባለው ፈሳሽ ምክንያት ነው። ለሎች መነሻዎች ደግሞ እሳት ወይም የነዳጅነት ባሕርይ ያላቸው ነገሮችና ፈንጂዎች ናቸው።

አደጋው በደረሰ ጊዜ እጅን በንፁሕ ውሃና ሳሙና ታጥቦ ንፁሕ ጨርቅ ወይም ፎጣ በጨው በተበጠበጠ ውሀ ውስጥ ነክሮ ቁስሉን ማጠብ ነው። ይህም ስቃዩን ያስታግስልዎታል። ቅባትና ቫዝሊን ማድረግም ቁስለኛውን ይረዳዋል። ነገር ግን ጥልቀት ያለው ቁስል ከሆነ ቅባቱን ወደ ውስጥ ለማስገባት ስለሚያዳግት በፔኒሲሊን ዱቄት ማከም የተሻለ ነው።

የተቃጠለው የሰውነት ክፍል በልብስ የተሸፈነ ከሆነ በቁስሉ አካባቢ የሚገኘውን ልብስ በስለት ቆርጦ ከሰውነት ላይ ማስወገድ ያስፈልጋል።

ልብሱ ከአካላቱ ጋር የተጣበቀ ከሆነ ግን ለማስለቀቅ ያለ መሞከሩ ይሻላል። ቁስሉን ከጀርሞች ለመጠበቅ ንፁሕ በሆነ ጨርቅ ጠምጥሞ ከተቻለ ወደ ሐኪም ቤት መውሰድ ነው። ቁስለኛው ወደ ሐኪም ቤት በሚሄድበት ጊዜም የቆሰለው ገላው ከጤናማው ሰውነቱ ጋር እንዳይነካካ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ቃጠሎውም በአጥንቱ መጋጠሚያ ላይ ከሆነ ቁስለኛው ቅልጥሙን ወይም ክንዱን እንዳያነቃንቅ ጠንከር ባለ ቅርፊት ወይም በእንጨት ስንጣቂ ደግፎ ማሰር ይረዳል።

ከዚህም ሌላ የመቃጠል አደጋ የደረሰበት ሰው በሰውነቱ ቆዳ ላይ በሚገኙ ወንፊት መሳይ ጥቃቅን ቀዳዳዎች አማካኝነት ብዙ ፈሳሽ ስለሚፈሰው ሰውነቱ እንዳይዝልና ብርድም እንዳይሰማው በቃጠሎ ምክንያት የተቀነሰበትን የፈሳሽ መጠን እንዲተካ መርዳት ነው። ይህንን ለማድረግም ብዙ ዘዴዎች አሉ።

አንዱ ዘዴ በተለይም ከባድ የመቃጠል ጉዳት የደረሰበት ሰው ከአንድ እስከ አራት ጠርሙስ ውሀ ማጠጣት ነው። ቢሆንም ውሀው ብቻውን ሳይሆን በእያንዳንዱ ጠርሙስ ከግማሽ እስከ አንድ ማንኪያ ጨው መጨመር ያስፈልጋል።

ሌላው ዘዴ ደግሞ ብዙ ስኳር ያለበት ትኩስ ሻይና ወተት በማጠጣት እቤት ውስጥ ወይም ከጥላ ስር አመቻችቶ ማስተኛት ሊሆን ይችላል። ይህ ሁሉ የሕመምተኛውን ስቃይ ይቀንስለታል። ያም ሆነ ይህ አደጋው የአካል ጉድለት፣ ሞትና የኑሮ ችግር ሊያመጣ ስለሚችል በእሳት በምንገለገልበት ጊዜ በጣም መጠንቀቅ ይኖርብናል።

(አዲስ ዘመን፣ ታኅሣሥ 15 ቀን 1980 ዓ•ም)

የኛው ትሁን!

የሀገር ፍቅር • • • የጽናቱ

የወገን ፍቅር • • • የጥልቀቱ

ትላንት ዛሬ • • • ነገም • • • ተነገ ወዲያ

ከሀገር ድንበር ከዚያ • • • እዚያ

ሰንደቅ ቆሞ • • • በሰንደቅ ላይ

የሀገር ሲሳይ • • • የዘር ክፋይ።

ስታደሚ • • • በፍቅር ፊት

አሁንም • • • አሁንም • • • አሁንም ወደ ፊት

ሙሽራዬ • • • የኔ ሎጋ

አበባዬ • • • የኔ ሸጋ

ነገም • • • ወዲያው • • • ወደኛጋ!

ሆ! እንበል • • • በምድራችን

በእግር ኳሱ ሜዳ • • • በቀዬአችን

  • • • • • • • • • ሙሽራዬ
  • • • • • • • • • አበባዬ

የእኛ ትሁን የእማማዬ

ዛሬም በሜዳችን • • • • • • • • •

ገድል ይዘን • • • ገድል ቋጭተን

እማማችን፤ • • • ከአፍሪካ • • • ይዋል ስሟ

በምድራችን እናም • • •

አደራ ነው • • • ለሕዝብ ፍቅር

አደራ ነው • • • ለሀገር ክብር

ተጫዋቹ ወገናችን • • •

የእኛው ክፋይ ልጃችን

ለድል ጥቢ • • • ለድል ብሥራት

ለሀገር ክብር • • • ለወገን ኩራት

ዛሬም • • • እንደ ትናንት • • • በምድሯ

በአየሩ ዓውድ • • • በእምባችን

ሐሴትን አፍርተህ ሐሴትን ለግሰን

  • • • • • • • • • ሙሽራዬ
  • • • • • • • • • አበባዬ

የእኛ ትሁን የእማማዬ።

አዎ • • •

የኛ ትሁን • • • ዋንጫይቱ

አደራ ይዛችሁ ባደራ ላይ

  • • • • ወገኖቼ ተበራቱ

ከኃይለየሱስ ጌታሁን (4 ኪሎ)

(አዲስ ዘመን፣ ታኅሣሥ 18 ቀን 1980 ዓ.ም)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You