የአንድን አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ከሚወስኑ አበይት ጉዳዮች መካከል በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄደው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል:: ኢንቨስትመንት ለአንድ አገር እድገት ያለው ጠቃሜታ ዘርፈ ብዙ ነው:: ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከማስቻሉም በላይ የውጭ ምንዛሬ ምንጭም በመሆን አገርን ከዶላር እጥረት ይታደጋል::
የውጭ ኢንቨስትመንት ለአገሪቱ ልማት ተገቢውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ማድረግ እና በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ኢንቨስትመንት የሥራ ዕድልን በመፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማምጣት ሰፊ ሚና ይጫወታል::
ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ እጅጉን ሲፈተን ቆይቷል፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክንያት ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ዘርፉ ተዳክሞ ቆይቷል፤ በተለይ የኢትዮጵያ ትልቋ የውጭ የኢንቨስትመንት አጋር የሆኑት ቻይናን የመሳሰሉ አገራት በኮቪድ መጠቃታቸው በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ የራሱን የሆነ ጫና አሳድሯል::
ስለዚህም ያለፉት ሁለት አመታት ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፈታኝ ጊዜዎች ነበሩ:: በችግሩ ልክ ጠንካራ ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዶ ወደ ተግባር በመቀየሩ ባጋጠመው ቀውስ ልክ ውድቀት እንዳይኖር ለማድረግ እንደተቻለ እና ምንም እንኳ የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ ለመሆን ባይቻልም ችግሮችን ተቋቁሞ ለማለፍ ጥረት እንደተደረገ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያት ሲገልፅ ቆይቷል:: በ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 31 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አስመዝግቦ የነበር ሲሆን፣ ይህም በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚዋ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሳበች አገር አድርጓታል፤ በአጠቃለይ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ይዛለች:: ይህም በብዙ ፈተና ውስጥ መልካም የሚባል ውጤት መመዝገቡን የሚያሳይ ነው::
በያዝነው ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 95 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ ወደ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ እንደተቻለ ይህም የዕቅዱን 64 ከመቶ እንደሆነ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ገልጿል፤ ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 16 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ እንዳለው በማስታወስ፤ በቀጣይ 12 ወራት ደግሞ 6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማምጣት ታቅዷል፤
በ2015 የበጀት ዓመት የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨቱ አወንታዊ ተፅዕኖ አምጥቷል፤ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ያሉ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች መጨመር እና የዓለም አቀፍ ጫና መቀነሱ ለዕቅዱ መሳካት ወሳኝ እንደነበር ተገልጿል:: አገሪቱ በግጭት እንደመቆየቷ የተመዘገበው ውጤት ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልፃሉ::
ለማክሮ ኢኮኖሚው ትልቅ አቅም እንደሚሆን የሚጠበቀው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩበትም ችግሮችን እየተቋቋመ ተጨማሪ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚጠበቅበት የስድስት ወራት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ የዘርፎች ዕቅድ አፈፃፀም በተገመገመበት ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል::
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ የዘርፉ ምሁራን ሃሳብ አላቸው:: የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ክቡር ገና እንደሚናገሩት፤ ለኢንቨስትመንት መነቃቃቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው የጦርነቱ መቆም ነው። ጦርነት ባለበት ሁኔታ የውጭ ኢንቨስትመንት ይመጣል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም፣ ጦርነት መቆሙ ከዚህ በፊት ኢንቨስት ለማድረግ የፈለጉ እና በጦርነቱ ምክንያት ኢንቨስትመንቱን ለጊዜው ያዝ ያደረጉ አገራት እና ኩባንያዎች ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት የቻሉበት ሁኔታ አለ፣ ከዚህ ውጪ መንግሥት ያስተካከላቸው ሁኔታዎችም አሉ፣
በተለይ የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ ብዙ ጥረት መደረጉ ለውጦች እንዲመጡ አስችሏል:: በየአገሩ ጉብኝት እየተደረገ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መከፈት እና በተለይ ደግሞ የጦርነቱን መቆም አስታኮ ለበርካታ ካምፓኒዎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል:: ከጅቡቲ ጀምሮ፣ ወደ መካከለኛ ምሥራቅ ያሉትን ኢንቨስተሮች የበለጠ ለመሳብ ጥረት ተደርጓል የዚህ ውጤት ነው አሁን የተሻለ ለውጥ ያሳየው ብለዋል።
ሆኖም የተነቃቃው ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲጠናከር መሻሻል አለባቸው ያሏቸውን ነጥቦች አቶ ክቡር ገና አስቀምጠዋል:: ለኢንቨስትመንቱ ዋና አጋዥ የሆነው የኃይል አቅርቦት ሳይቆራረጥ በመደበኛነት መቅረብ አለበት:: የመሬት አቅርቦቱንም ማስተካከል ያስፈልጋል:: የተጀመሩ የመሠረት ልማት ሥራዎች በፍጥነት መጠናቀቅ አለባቸው:: የውጭ ምንዛሬ ሁኔታዎች መስተካከል ይኖርባቸዋል:: በእነዚህ ሁኔታዎች በመጠኑም ቢሆን መንግሥት እየሠራበት ቢሆንም ቶሎ ቶሎ በፍጥነት መስተካከል እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እና በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህሩ ዶክተር ዘላለም እጅጉ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው የውጭ ኢንቨስትመንት መነቃቃት ወደኋለ መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል ይላሉ:: ከመንግሥት ለውጡ ማግስት የተወሰኑ መነቃቃቶች ነበሩ፤ ከዚያ በኋለ ግን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ ደግሞ ወደኋለ እንዲመለስ አድርጎታል፤ ከዚያ በኋላ በመንግሥት የተለያዩ ጥረቶች ተደርጓል:: ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ቀስ በቀስ በማገገምም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ውጤት ማሳየት ችሏል ብለዋል::
ለዚህም ምክንያቶቹም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አስፈላጊነቱን መንግሥት በማመኑ በተለይ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ድህነትን ለመቀነስ እንደ ፖሊሲ መያዙ እና የመንግሥት ቁርጠኝነት መኖሩ፤ ሁለተኛው ነገር ከፖሊሲ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ የመጣው የቴሌኮሙኒኬሽንን ለግል ባለሀብቶች ፍቃድ መስጠቱ በራሱ ወደ 860 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ገቢ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል::
ሌላው ነገር ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መቋቋም በተለይ የይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ሀዋሳ፣ እና ሌሎችም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የውጭ አልሚዎች በደንብ ወደ ሥራ መግባት መቻላቸው የወቅቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ እንዲሆን ወይም እንዲጨምር አስችሏል ይላሉ ዶክተር ዘላለም ::
እስካሁን ባለው የውጭ ኢንቨስትመንቶች ምንን መሠራት አድርገው ነው ወደ አገራችን የሚመጡት የሚለው ሲታሰብ ትልቁ ነገር በአፍሪካ ትልቅ የገበያ ዕድል መኖሩ ነው:: አፍሪካ ሁለተኛው የሕዝብ ብዛት ያለት አህጉር ናት፤ በተጨማሪም ወጣት ወይም አምራች የሰው ኃይል በብዛት መኖሩ ሌላው ሳቢ ምክንያት ነው:: ከዚህ በተጨማሪ በመንግሥት ፖሊሲ የኢንቨስትመንት ሕግ ላይ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ማበረታቻዎች መካተታቸው እንደ አንድ ዕድል ሊታይ የሚችል ነገር ነው::
እንደምሁሩ ገለጻ በአስር አመቱ መሪ የልማት እቅድ የተካተቱ ቁልፍ የሆኑ ሴክተሮች አሉ :: በተለይ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የተደረጉ የማግባባት ሥራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው:: ከዚያ በተጨማሪ እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በመንግሥት በኩል ያለው የመሠረተ ልማት አቅርቦት ጥሩ ዕድል ነው ብለዋል::
ነገር ግን እነዚህን ዕድሎች በደንብ እንዳንጠቀም ያደረጉ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ዶክተር ዘላለም እጅጉ ያብራራሉ:: አሁን ያሉ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ አለመረጋጋቶች ትልቅ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ:: ነባር ኢንቨስትመንቶች ደግሞ ተረጋግተው እንዳይቆዩ ትልቅ እንቅፋት ይሆናሉ:: ስለዚህ መንግሥት የሚጠበቅበት የተረጋገጠ ሰላም እና መረጋጋት እንዲኖር መሥራት ነው፤ የኢኮኖሚ መረጋጋት ስንል ከዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና መሰል ከማክሮ ኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ነገሮች መቅረፍ መቻል ይኖርበታል ብለዋል::
ሌላው በቂ የማስፈፀም አቅም ያላቸው ተቋማት አለመኖር ወይም ደግሞ ያሉትም ቢሆኑ የማስፈፀም አቅም ውስንነት ችግር ያለባቸው መሆናቸው ነው፤ ጥሩ ጥሩ ሕጎች አሉ እነዚያን ሕጎች በአግባቡ መፈፀም አለመቻል ኢንቨስተሮች በራስ መተማመን እንዳይኖራቸው ያደርጋል፤ ኢንቨስትመንት ደግሞ መተማመን እና ተገማች የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ሲኖር ነው ጥሩ ውጤት የሚኖረው:: ሌላው በውጭ ኢንቨስትመንት ብድር አወሳሰድ ላይ ያሉ የማስፈፃም ክፍተቶች፣ ከውጭ የሚገቡ ማሽነሪዎች ውጤታማነትና በክልል መንግሥት እና በፌዴራል መንግሥት ያሉ የመሬት አቅርቦት ላይ ያሉ ውስንነቶችን መቅረፍ አስፈላጊ ነው:: መንግሥት እነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሠራ ይገባል ብለዋል::
ዶክተር ዘላለም በተጨማሪ ሲናገሩ፤ አገሪቱ ወደብ አልባ ከመሆኗ አንፃር ከፍተኛ የሆኑ ወጪዎች ይኖሩባታል:: በገቢና ወጪ ዕቃዎች ላይ የየብስ ትራንስፖርት ወጪውም ከፍተኛ ነው:: ከወደብ ወደ አገር ቤት ለመምጣት ደግሞ የቢሮክራሲ ችግር አለ፤ በቀላሉ ሊፈፀሙ የሚችሉ ነገሮች ብዙ የሥራ ቀናትን ይወስዳሉ፤ በጉምሩክ አካባቢ ያሉ የሙስና ድርጊቶች ለኢንቨስትመንቱ እክል ናቸው:: ስለዚህም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ መንግሥት ያሉትን ዕጸጾች ማጽዳት ይጠበቅበታል ብለዋል::
ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ ያጣችውን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ ገበያ የመለክ ዕድል (አገዋ) መንግሥት ባደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት የመነሳት ዕድል ስላለው ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል:: ይሄም ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ተጨማሪ መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንም አብራርተዋል::
አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው፤ አሁን ያለው ጥሩ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሰላም መቀጠል እንዳለበት ያሰምሩበታል:: የሰላም ሂደቱ ያዝ ለቀቅ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፤ አለመግባባቶች ከመስመር ወጥተው ወደሌላ ችግር እንዳይወስዱን መጠንቀቅ ይገባል ብለዋል::
ሌላው የማስተዋወቅ ሂደቱ መቀጠል አለበት፤ ሌሎች ኢንቨስተሮችን የመፈለግ እና ኢንቨስተሩን ሊያረካ በሚችል መልኩ ሥራዎችን በቅልጥፍና እንዲሠራ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ ደንቦችን ማስተካከል፣ ሕጎችን የበለጠ ለንግዱ በሚጠቅም መልኩ መከለስ ያስፈልጋል በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል::
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2015