ሰሞኑን የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ለባለድርሻ አካላት ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ የነበረውን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ጉዞ ምን እንደሚመስልና ያስገኘው ውጤት ምን እንደሆነ ማብራሪያ ሰጥቷል:: ማብራሪያውን የሰጡት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ ዶ/ር ሲሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያጠኑትም ጥናት መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የት ሊደርስ ይችላል የሚለውንም አስቀምጠዋል:: በቀጣይ በኢኮኖሚው ዘርፍ የበላይነትን ለመያዝ መደረግ ስላለባቸውና ስለተያዘው የወደፊት ርዕይ ላይም ገለጻ አድርገዋል:: አዲስ ዘመንም የተከታተለውን የሚኒስትሯን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርቧል::
የሀገራት የእድገት ደረጃ አመዳደብ
በዓለም ላይ ያሉ አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዋናነት ከአገራት ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ለመወሰን አገራትን በሶስት ደረጃ እንደሚከፍሉት ይታወቃል:: ይኸውም የሚከፋፍሏቸው ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ክፍፍል ያደርጋሉ:: በእነዚህ ሶስት መመዘኛዎች ውስጥ ያለው ዋናውና አንዱ ልዩነት የነፍስ ወከፍ ገቢ ልዩነት ነው:: ሌላው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ነው::
አጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ ዘርፎች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ደረጃቸው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት በጣም ዝቅተኛ ነው:: ምክንያቱም የቴክኖሎጂ ምርትም አያቀርቡም:: አብዛኛው ኢኮኖሚያቸው የሚመሰረተው በተፈጥሮ ሀብት ላይ ሲሆን፣ እነርሱም የመጀመሪያ ሴክተር የምንላቸው ግብርና እና ያልዘመነ የአገልግሎት ዘርፍ አካባቢ ነው:: በዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገራት በተለይ የአምራች ኢንዱስትሪው ዝቅተኛ ድርሻ ይይዛል:: ፈጠራና በምርምር ልማት ላይ ያለ ኢንቨስትመንትም እንዲሁ ዝቅተኛ ነው::
በመካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ከዝቅተኛ ገቢ ካላቸው አገራት በተሻለ ሁኔታ ቴክኖሎጂን ኮርጀውም ቢሆን የተሻለ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የተሻለ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው ናቸው::
ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ደግሞ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ አላቸው:: ኢኮኖሚያቸው የሚመሰረተው በአብዛኛው በቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን፣ በጣም ጥልቅ የሆነ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ያሳኩ ናቸው::
እነዚህ አገራት በተለይ የግብርና ዘርፋቸው በጣም ዝቅተኛ የሆነ ነው:: የአገልግሎት ዘርፋቸው በጣም ዘመናዊ ነው፤ ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረተ ነው:: ራሳቸው ያመረቱትን እቃ መሸጥ፣ ማገለባበጥ እና ኤክስፖርት ማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው:: ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በዝቅተኛ ገቢ ካላቸው አጋራት ተርታ የተሰለፈች ናት::
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለአንድ አገር በጣም ወሳኝ ነው:: በተለይ የማይበገር ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ነው:: የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ሲባል በኢኮኖሚ ውስጥ የዘርፎች ድርሻ ምን ይመስላል የሚለውን ነው የሚያሳየን ነው:: እሱ ማለት አምራች ኢንዱስትሪ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻን የሚመለከት ነው:: ከዚህ አንጻር በአደጉ አገራት ያለው ድርሻ ትልቅ ነው::
ሌላው የስራ ሰምሪትን ከመዋቅራዊ ሽግግር አኳያ ልናይ እንችላለን:: በአብዛኛው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ካሳካን አብዛኛው ስራ በአምራች ኢንዱስትሪ እና በዘመናዊ አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ነው ማለት ይቻላል:: ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት አብዛኛው ስራ ከ70 በመቶ በላይ የተፈጠረው በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ነው:: ስለዚህ ከስራ ስምሪትም አኳያ መዋቅራዊ ሽግግርን ልናይ እንችላለን::
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ያረጋገጡ አገራት ኤክስፖርታቸው በአብዛኛው በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ እና አምራች ኢንዱስትሪው እሴት የተጨመረበት ነው:: ከአገልግሎትም አኳያ ዘመናዊ አገልግሎት ነው:: ስለዚህ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ማረጋገጥ ካለብን የኤክስፖርት ዘርፎቻችን በዚያው መጠን የተለያየ ማድረግ ይኖርብናል::
ከዚህ ተነስቶ መዋቅራዊ ሽግግሩን ያረጋገጡ አገራት የሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ ውስብስብነት ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ የሚያመርቷቸው ቴክኖሎጂዎች ውስብስብነት ከጊዜ ወደጊዜ በጣም እየጨመረ የመጣ ነው:: መዋቅራዊ ሽግግሩ ደግሞ ከቴክኖሎጂ ውስብስብነት ጋር የሚመጣ ነው ማለት ነው::
ያደጉ አገራትን ስናስተውል ለማደጋቸው የራሳቸው ታሪክ ጠቅሟቸዋል:: እንዲህ ሲባል ግን ታሪክ መኖሩ ብቻውን ለእድገት በቂ አይደለም፤ በዚያ ታሪክ በአግባቡ መጠቀም ሲቻል ነው:: እናም የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው አገራት ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ የተሻለ እድል ይኖራቸዋል:: ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ በራሱ ጥቅም አለው::
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ያለችበት የአፍሪካ ቀንድ የተሻለ እድል የሚሰጣት ነው ተብሎ የሚነገር ነው:: በተመሳሳይ አገራት ያላቸው ባሕል ወሳኝ ነው:: ለምሳሌ በኢስያ የሚታየው የስራ ባሕል ወሳኝ ነው:: ሌላው የተሻሉ ተቋማትን መገንባት የቻሉ አገራት የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር ከማረጋገጥ አኳያ የተሻለ ነው:: የተፈጥሮ ሀብትም ተጠቃሽ ነው:: ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የተሻለ የተፈጥሮ ሀብት አላት::
ቴክኖሎጂን ማምረትና ቴክኖሎጂን መጠቀም ለአንድ አገር በጣም ወሳኝ ነው:: ይህ ማለት የሚያርፈው ማኑፋክቸሪንግ ወይም የአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ነው:: ለመዋቅራዊ ሽግግር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ወሳኝ የሆነው ከምንሰጠው በላይ ሰጥቶን ወደተሻለ ደረጃ ስለሚያሸጋግር ነው::
አምራች ኢንዱስትሪ የካፒታል ክምችትን ይፈጥራል:: ስለዚህ በፖሊሲ ደግፈን አምራች ኢንዱስትሪ ለማስፋት መንግስትና የግሉ ዘርፍ ተባብሮ መስራት ከተቻለ እንደ ግብርና ካሉ ሴክተሮች ይልቅ የአምራች ኢንዱስትሪ የካፒታል እድገትን እና ኢንቨስትመንትን በቀጥተኛ ሁኔታ የሚያበረታታ ነው::
የየስርዓቱ የኢኮኖሚ ልማድና ፖሊሲዎች ምን ይመስሉ ነበር? ውጤታቸውስ ምንድን ነው?
በንጉሱ ዘመን፣ በደርግ ዘመን፣ በኢህአዴግ እና ከለውጡ በኋላ ያለውን ዘመን ለማየት ያህል ከኢኮኖሚ ስርዓት አኳያ በንጉሱ ጊዜ የነበረው የፊውዳል ካፒታሊስት ስርዓት ነው:: በወታደራዊ መንግስት ጊዜ የእዝ ኢኮኖሚ የነበረ ሲሆን፣ መንግስት ኢኮኖሚውን ሙሉ ለሙሉ የሚቆጣጠርበትና ሶሻሊዝም የተተገበረበት ስርዓት ነበር::
በኢህአዴግ ዘመን የኢኮኖሚ ስርዓት ባህሪው የቅይጥ ኢኮኖሚ አይነት ያለው ነበር:: ካፒታሊዝም ነው፤ ግን አንዳንድ ቦታ ስናይ በውስጡ የተደበቀ የሶሻሊዝም ባህሪ ያለው ስለመሆኑ ጽሑፎች ያሳያሉ::
ከ2010 በኋላ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ሪፎርሞች ሁሉ ወደ ፕራግማቲቭ ካፒታሊዝም ነው:: ይሁንና እኛን የሚመስል፣ የሕዛባችንን ሁኔታ ያገናዘበ፣ ችግራችንን የሚረዳ አይነት አካሔድ ለመሄድ ጥረት እየተደረገ ነው::
የመሬት ስርዓትን በተመለከተ
በንጉሱ ጊዜ መሬት በፊውዳሎች የተያዘ ነበር:: በደርግ ጊዜ ደግሞ የመሬት ሪፎርም ተደርጓል:: ትልቁ ሪፎርም መሬት ለአራሹ የሚለው ነው:: መሬት ቢከፋፈልም ከመሬት መምጣት ያለበት ለውጥ በዚያ ልክ ሳይመጣ ቆይቷል::
በኢህአዴግ ዘመን መሬት የመንግስት ነበር:: ይሁንና መሬትን የመጠቀም መብት ግን የተሻሻለበት ዘመን ነበር:: በኋላ ላይ ግን ከተማው ሲስፋፋ ትልቅ የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ የሙስና መገለጫም በመሆኑ ለትልቅ ቀውስ መነሻ ሆኖ ነበር:: ይሁንና ከደርግም ጊዜ በተሻለ መሬትን ለአርሶ አደሩ ጥቅም እንዲውል ተሰርቷል::
ከለውጡ በኋላ ደግሞ መሬት የመንግስት ነው:: መሬትን ሪፎርም ለማድረግም ተጥሯል:: አርሶ አደሩም መሬቱን የኢኮኖሚ መሳሪያ አድርጎ እንዲጠቀም የተደረገበት ነው:: በተሰጠው ሰርተፊኬት አስይዞም መበደር እንዲችል የተደረገበት ነው:: መሬት የኢኮኖሚ መሳሪያ እንጂ የፖለቲካ መሳሪያ መሆን እንደሌለበት እምነት ተወስዶበታል::
በየስርዓቱ ውስጥ የመንግስታቱ የልማት ፋይናንስ ምን ይመስል ነበር?
የኢንተርናሽናል ፋይናንሻል ኢንስቲትዩሽንስ በንጉሱ ጊዜ የተወሰኑ ፋይናንሶችን ይሰጡ ነበር:: ፋይናንስ ከምዕራቡም ይመጣ ነበር:: ወደ ደርግ ሲመጣ በተለይ ከሶሻሊስት ሀገራት ጋር ከፍተኛ የሆነ የልማት ትብብር የነበረበት ጊዜ ነበር:: ፋይናንስም ሆነ እርዳታም በአብዛኛው ከዚያ ይመጣ ነበር::
በኢህአዴግ ጊዜ የተረከበው ሀገር ጥልቅ ችግር የነበረው በመሆኑ የእዳ ስረዛ ተደርጎለታል:: የልማት ትብብር የተሻለ የነበረበት ጊዜ ነበር:: በወቅቱ ሀገሪቱ ከፍተኛ ብድር የተበደረችበት ወቅት ነበር:: ከአገር ውስጥም በተለይ ንግድ ባንክን በጣም የፈተነ የአገር ውስጥ ብድር ለመንግስት የልማት ድርጅቶች በከፍተኛ ሁኔታ የተወሰደበት ጊዜ ነበር:: ከውጭ በተለይ ኮሜርሻል የሆኑ ውድ የሆኑ ብድሮችም የተወሰደበት ጊዜ ነበር::
በዚህም ምክንያት ባለፉት ዓመታት ወደ አገር ከሚመጣ ገንዘብ በላይ እዳ ለመክፈል የተገደድንበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር:: ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ አስር ቢሊዮን ዶላር እዳ ከፍለናል:: ይህ የሆነበት ምክንያት የተበደርነው በጣም ትልቅ ወለድ ያለው፣ የአጭር ጊዜ የሚከፈል ኮሜርሻል ብድር በመሆኑና ተበድረን ያዋልንበት ቦታ ደግሞ ውጤታማ ባለመሆኑ ነው:: የተወሰዱት ብድሮች ፕሮጀክቶቹ አልቀው፣ ሸጠው፣ አገልግሎት ሰጥተው ገንዘብ አምጥተው ሳይሆን ከራሳችን ዶላር እንድንከፍል ተገድደናል::
የእቅድ ትኩረትን በተመለከተ
በንጉሱ ዘመን ሶስት የአምስት አምስት ዓመት እቅዶች ነበሩ:: ሁለቱ እየተተገበሩ ነበር፤ ሁለተኛው የአምስት ዓመት እቅድ ማኑፋክቸሪንግ ላይ ያተኮረ ነበር:: ሆኖም ግብርና ያላደገ በመሆኑ ምክንያት ግብዓት እጥረት አጋጠመ:: ስለዚህም ወደግብርና መሄድ አለብን በሚል ሶስተኛው የአምስት ዓመት እቅድ ግብርና ላይ ሆነ፤ ግን በመሬት ስርዓቱ ምክንያት ውጤት ማምጣት አልቻለም:: እንዲያም ሆኖ ኢንዱስትሪና ግብርና ዋና ትኩረት ነበሩ::
በደርግ ጊዜ አርሶ አደሩ የሚያመርተው ምርት ይነገረዋል፤ ካመረተ በኋላ የሚሸጥበት ዋጋ ይተመንለታል:: ስለዚህ ፊውዳል የሆነ የመንግስት ስርዓት ነው ማለት ይቻላል::
በኢህአዴግ ዘመን በዋናነት ትኩረቱ ግብርና ላይ ነበር:: የድህነት ቅነሳ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር:: በተለይ ደግሞ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና መሰረተ ልማት በማስፋፋት ለኢንዱስትሪዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ነበር::
አሁን ያለውን ፖሊሲ ስንመለከት በተለይ አምስት ዋና ዋና የኢኮኖሚ የእድገት ዘርፎች ላይ ያተኩራል:: እነዚህም ግብርና፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ ነው::
ባለፉት 60 ዓመታት ኢትዮጵያ ያሳካችው ምንድን ነው?
ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ ኢኮኖሚያችን በአማካይ በአራት ነጥብ ሁለት በመቶ አድጓል:: ይህ አማካይ ስለሆነ ነው እንጂ በደርግ ጊዜ ኢኮኖሚያችን ነጋቲቭ ሁሉ ሆኖ እንደነበር የሚታወስ ነው:: በንጉሱ ጊዜ ደግሞ ከአምስት በታች በሁለትና በአራት በመቶ አካባቢ ያደገበት ጊዜ ነበር:: በኢህአዴግ ዘመን ባለሁለት አሃዝን ጨምሮ ተለቅ ያለ ቁጥር የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ችለን ነበር:: ሕዝባችን ደግሞ በሁለት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ በአማካይ አድጓል:: የነፍስ ወከፍ ገቢ በአንድ ነጥብ ሶስት በመቶ ባለፉት 60 ዓመታት በአማካይ አድጓል:: የዜጎቻችን የኑሮ ደረጀ በሶስት ነጥብ አምስት እጥፍ ተሻሽሏል:: አማካይ በጤና የመኖር እድሜም 68 ነጥብ ሰባት ዓመት ደርሷል::
ባለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ሲወዳደር
ለምሳሌ በ2004 ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች:: ከምስራቅ አፍሪካ ደግሞ አንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች:: ከሰሃራ በታች ካሉት ሶስተኛው ትልቁ ኢኮኖሚ ማስመዝገብ ችላለች::
ይሁንና የዓለም ባንክ በ2029 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይደርሳል ብሎ የተነበየው 369 ቢሊዮን ዶላር በመድረስ ሶስተኛው የአፍሪካ ትልቁ ኢኮኖሚ ይሆናል በሚል ነው:: በጥቅሉ ሲታይ ግን ባለፉት 60 ዓመታት የሰራናቸው ስራዎች እዚህ አድርሰውናል::
ነገር ግን ባለፉት 60 ዓመታት የሰራናቸው ስራዎች አሻጋሪ ነበሩ ወይ? ለማለት ከእኛ ጋር አብረው የተነሱ አገራትን ለማሳያነት መመልከቱ ተገቢ ነው:: የእድገት ምንጫችንን ከኮሪያ ጋር ስናወዳድር በ1960ዎቹ አካባቢ ኮሪያና ኢትዮጵያ እኩል ነበሩ:: የኢትዮጵያ የጂዲፒ እድገት ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ በአማካይ ያደገው አራት ነጥብ ሁለት በመቶ ነው:: ኮሪያ ደግሞ በተመሳሳይ ዓመት ውስጥ በአማካይ ስድስት ነጥብ ሁለት በመቶ አድጓል:: በተለይ የመጨረሻዎቹ ሰላሳ ዓመታት ከአስር በመቶ በላይ ማደግ ችሏል:: ለተከታታይ ሰላሳ ዓመታት ያስመዘገቡት ባለሁለት አኃዝ ኢኮኖሚ በመሆኑ በጣም ትልቅ የኢኮኖሚ እድገት ነው::
ኢትዮጵያ ለተወሰኑ ዓመታት ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚ ማስመዝገብ ብትችልም ከዚያ ወዲህ ግን መውጣትና መውረድ ነበር:: የነፍስ ወከፍ ገቢያችንን ስንመለከት ኢትዮጵያ በአንድ ነጥብ ሶስት በመቶ ያደገ ሲሆን፣ የኮሪያ ደግሞ በአማካይ ሰባት ነጥብ ሶስት በመቶ አድጓል:: ስለዚህ ልዩነቱን ስንመለከት በየዘመኑ የነበሩ መንግስታት የየራሳቸውን ጥረት ቢያደርጉም የእኛ ኢኮኖሚ ተሻጋሪ አልነበረም::
ቀጣይ 60 ዓመት እንዳይባክን አሁን አዲስ መንገድ ተጀምሯል
ለምሳሌ የሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራት ላይ ነው:: ሌላው ለማደግ ወሳኝ የሆነው ኢነርጂ ሲሆን፣ እኛ በቂ ከመሆኑም በላይ ያለን አረንጓዴ ኢነርጂ ነው:: ፕሮጀክቶች የመፈጸም አቅማችንም በእጅጉ ተሻሽሏል:: ተበላሽተው የቆሙ ፕሮጀክቶችን ጭምር ማጠናቀቅ ተችሏል:: ከዚህ በተጨማሪ ግልጽ የሆነ ርዕይ አለን:: ማዕድን ዘርፉን ለማሳደግ አዋጅ በማውጣት ጭምር ትልቅ ስራ እየሰራን ነው::
ሌላው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ለረጅም ዘመን ዝግ ከነበረበት ወጥተን ከዓለም ጋር የተቀላቀልንበት ጊዜ ነው:: የማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩን ለማገዝ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመ ኮሚቴ አለ፤ ይህ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲሆን፣ ስራው ተጀምሯል:: መሰረተ ልማትን የተሻለ ለማድረግና የቱሪዝም አቅማችንን ለማሳደግ ትልልቅ ስራዎች ተሰርተዋል:: በኢኮኖሚው ዲፕሎማሲ በተሰራው ስራ ብሪክስን መቀላቀል ችለናል::
የቅርብ ጊዜ ሪፎርሞች
በለውጡ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ፈተና ያጋጠመበት ጊዜ ነበር:: ሪፎርም መደረግ ባይቻል ኖሮ ትልቅ የኢኮኖሚ ቀውስንም ያስከትል ነበር:: ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ወደስራ የገባበት ጊዜ ነበር፤ ኮቪድ 19 ከባድ ጫና መፍጠሩ የሚታወስ ነው:: እንዲዚያም ሆኖ ሁሉን ተቋቁሞ ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢኮኖሚያችን በሰባት ነጥብ ሁለት በመቶ ማደግ ችሏል::
ወቅቱ የመንግስት የልማት ተቋማት ሪፎርም የተደረጉበት ነበር፤ አምና ብቻ ኢትዮ ቴሌኮም 27 ቢሊዮን ብር ግብር መክፈል ችሏል:: የሕግ ማነቆዎች የተፈቱበት ጊዜም ነው:: ምንም እንኳ ከኮቪድ በኋላም የአገር ውስጥና የውጭ ግጭቶች ፈተና ሆነውበት የቆዩ ቢሆንም ብዙ ውጤቶችን ግን ማስመዝገብ ችለናል::
በ2016 የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተገባበት ሲሆን፣ ከዚያ ውስጥ አንዱ የሆነው የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ገበያን እንዲወስን መደረጉ የሚታወቅ ነው:: ዘመናዊ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበር የተጀመረበትም ጊዜ ላይ ነው ያለነው ማለት ይቻላል::
የኢኮኖሚ እድገቱ
ኢትዮጵያ በ2023/24 በዓለም በኢኮኖሚ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ አስር አገራት ውስጥ አንዷ መሆን ችላለች:: ለምሳሌ በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ እድገት ስምንት ነጥብ አንድ በመቶ አድጓል:: ጂዲፒው 210 ቢሊዮን ዶላር ሲደርስ፣ የነፍስ ወከፍ ገቢ ደግሞ አንድ ሺ 937 ዶላር ደርሷል::
የባለፉት ስድስት ዓመታት ገቢን በተመለከተ በ2010 ዓ.ም የታክስ ገቢ 176 ቢሊዮን ብር ነበር:: በ2016 ዓ.ም ላይ 512 ቢሊዮን ብር ማድረስ ተችሏል:: በ2017 ዓ.ም የመጀመሪ ሩብ ዓመት 180 ቢሊዮን ብር ነው:: ይህ በ2010 ዓመቱን ሙሉ ከተገኘ የታክስ ገቢ በላይ ነው:: ይህ የሪፎርሙ ቀዳሚ ውጤት እንደሆነ መረዳት ይቻላል:: ከጂዲፒ አኳያ ሲታይ ግን እየቀነሰ መሄዱን ማስተዋል ይቻላል:: ይህ ኢኮኖሚው ማመንጨት የሚችለው ገቢ እንዳልመነጨ ያመላክታል::
የውጭ እና የአገር ውስጥ እዳ
ኮሜርሻል ብድር ሳንበደር ቆይተን፣ እዳችንን ስንከፍል ቆይተናል:: ለምሳሌ አስር ቢሊዮን ዶላር እዳ ከፍለናል:: እዳ በመክፈላችንና ብድር ላለመበደር በመወሰናችን ምክንያት ከጂዲፒያችን 13 ነጥብ ሰባት በመቶ ማምጣት ችለናል:: ሪፎርም በማድረጋችን ምክንያት የእዳ ስረዛ ሳይሆን ሽግሽግ አግኝተናል:: በየዓመቱ በአማካይ እስከ 2015 ድረስ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ስንከፍል ነበር:: ዘንድሮ ግን በዓመቱ የሚጠበቅብን አንድ ቢሊዮን ዶላር ነው:: በእዳ ሽግሽጉ ምክንያት በአማካይ አንድ ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አግኝተናል ማለት ነው::
በሪፎርሙ ምክንያት የተገኘ አንድ ውጤት ደግሞ 900 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ብድር ለመንግስት የልማት ድርጅቶ መንግስት ተበድሮ መክፈል ያልቻሉ በመሆናቸው ንግድ ባንክን ፈተና ውስጥ ከትተውት መቆየታቸው ይታወቃል:: ይህ ብድር ወደ መንግስት እንዲዞር ተደርጓል::
መንግስት በአሁኑ ወቅት ከብሔራዊ ባንክ ምንም አይነት ብድር አልወሰድም፤ በሌላ አነጋገር ብር አልታተመም ማለት ነው:: በአጠቃላይ ግን በዚህ ሪፎርም የተገኘው ውጤት የእዳ ሽግሽግ ወደ አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ነው::
ኤክስፖርት
በ2010 ዓ.ም ከሸቀጥ ኤክስፖርት የተገኘው ሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ነው:: በ2016 ላይ ደግሞ ሶስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል:: ዘንድሮ የተሻለ እንደሚገኝ የሩብ ዓመቱ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ውጤት አመላካች ነው:: አምና በሶስት ወር 821 ሚሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ ነበር:: ዘንድሮ ግን እንደተጠቀሰው ልቆ በመገኘቱ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ84 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል:: ቡና እና ወርቅ ለውጤታማነታችን ትልቅ ድርሻ ያላቸው ናቸው::
የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በ2010 ዓ.ም ሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ገብቶ ነበር፤ በ2016 በጀት ዓመት ላይ ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ማሳካት ተችሏል::
ሬሚታንስን ስንመለከት ደግሞ አምና በዚህ ሰዓት 719 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ዘንድሮ 883 ሚሊዮን ዶላር በሶስት ወር ማሳካት ተችሏል::
ሌላኛው ከሪፎርሙ አኳያ የምንመለከተው የውጭ ምንዛሬ ገበያ ጤናማነት ሲሆን፣ በተለምዶ ጥቁር ገበያ በምንለውና በባንክ መካከል የነበረው ልዩነት ከሪፎርሙ በፊት መቶ በመቶ በሚያስብል ደረጃ ሆኖ ነበር:: አሁን ከአምስት በመቶ በታች ይገኛል::
የፋይናንስ ሴክተር
የፋይናንስ ሴክተር እሴት ጭመራ ላይ በ2010 በጀት ዓመት 52 ቢሊዮን ብቻ ነበር :: አሁን በ2016 ላይ 91 ቢሊዮን ደርሷል:: ስለዚህ የፋይናንስ ሴክተሩ በኢኮኖሚ ውስጥ ጂዲፒው ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ማለት ነው:: በጂዲፒው ውስጥ ካለው ድርሻ ሶስት በመቶ ከነበረበት ወደ ሶስት ነጥብ አምስት በመቶ ማደጉን ማየት ይቻላል::
ግሽበት
ግሽበት ዛሬም የአገራችን ትልቁ ፈተና ነው:: ይሁንና 2016 በጀት ዓመትን ስንመለከት እየተረጋጋ ነው ማለት ይቻላል:: የሚጨምርበት መጠንም እየቀነሰ መጥቷል:: ለምሳሌ አጠቃላይ ግሽበት 19 ነጥብ ስድስት ነው መስከረም ላይ ስንል ከአምና መስከረም ዘንድሮ በ19 በመቶ ጨምሯል ማለት ነው:: ግን እስከ 30 በመቶ በላይ የጨመረበት ሁኔታ ነበር:: ግሽበት በየትኛውም ኢኮኖሚ ላይ ይኖራል::
ግብርና
በ2010 በጀት ዓመት በዋና ዋና ሰብሎች ያመረትነው 306 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ነው:: በ2016 ደግሞ 507 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማምረት ችለናል:: በዚህ በአምስት ዓመቱ 200 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ ምርት ተመርቷል::
ለምሳሌ የስንዴን ብቻ ብንመለከት በአጠቃላይ 2016 ላይ 230 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ማምረት ተችሏል:: ከዚህ አኳያ ስንዴ ኤክስፖርት ማድረግ ጀምረናል:: በዚህ ውስጥ ትልቅ ሚና የተጫወተው የመስኖ ስንዴ ነው:: እኤአ በ2020 ላይ 700 ሺ ኩንታል አካባቢ ብቻ ነበር በመስኖ ያመረትነው::
ማኑፋክቸሪንግና ማዕድን
አዲስ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ እንዲሁም በማዕድን ላይ የሕግ ማዕቀፉ ከፍተኛ ለውጥ ተደርጎበታል:: የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ሁሉ ለማበረታታት በትልቁ የተሰራባቸው ዘርፎች ናቸው::
በማዕድን በኩል ያለብን ትልቅ ክፍተት ምን እንዳለንና እንደሌለን አለማወቃችን ጭምር ነው:: በዘርፉ ግልጽ የሆነ መረጃ የለንም:: ክፍተቱ ታይቶ ግን የጂኦሎጂካል መረጃ እየተጠናከረ ይገኛል:: አሁን ትልቅ እምርታ እያሳየ ነው:: በአምራች ኢንዱስትሪው የአቅም አጠቃቀም 50 በመቶ ከነበረበት ወደ 59 በመቶ ማድረስ ተችሏል::
ቱሪዝም
ቱሪዝም መታወቅ ያለበት የመጀመሪያው ነገር መስህብ ስላለን ብቻ ሳይሆን መዳረሻም አስፈላጊ መሆኑ ነው:: ስለዚህ በርካታ መዳረሻ ስራዎች ተሰርተዋል:: አምና አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል:: በኮቪድ ዘመን 210 ሺ ብቻ እንደነበር ይታወሳል:: ሌላው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ሴክተሩ በትልቁ የተሻሻለ ነው:: በ2017 ሩብ ዓመት ብቻ 30 የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ ብቻ ተደርገዋል::
ኢነርጂ
ከኢነርጂ አኳያ በ2010 ላይ አራት ሺ 478 ሜጋ ዋት ነበር:: የሕዳሴ ግድባችን የሚያመርቱትን አራት ተርባይን ጨምሮ ስድስት ሺ 457 ሜጋ ዋት ማድረስ ተችሏል:: ይሁንና 48 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍላችን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት እጥረት ያለበት ነው::
የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ርዕይ እና በገለልተኛ አካል የተደረገ ጥናት
የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ርዕይ እኤአ በ2026 ዓ.ም ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን የምንሸጋገርበት ነው ብለን እናስባለን:: በ2030 በአስር ዓመት እቅዳችን ላይ የተቀመጠው አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የምትሆን አገር ትሆናለች በሚል ነው:: በ2050 ደግሞ ዓለም አቀፍ የብልጽግና ተምሳሌት የምትሆን አገር ትሆናለች የሚል ነው:: በጥቅሉ ኢትዮጵያ ቢያንስ በዓለም ላይ ካሉ 20 ትልልቅ ኢኮኖሚ ካላቸው ውስጥ ትገባለች::
አንድ ትልቅ የሆነ ዓለም አቀፍ ተቋም እንዳለው ኢትዮጵያ በ2075 ማለትም ከ50 ዓመት በኋላ አሁን እያደገች ባለችበት የኢኮኖሚ እድገት ስድስት ነጥብ ስድስት በመቶ በዓመት ብታድግ ስድስት ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ኢኮኖሚ ገንብታ በዓለም 17ኛ ኢኮኖሚ ትሆናለች በሚል ገልጿል:: በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ትልቅ የተፈጥሮ ሀብት ካላቸው ከእነ ሳዑዲ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊ፣ ጣሊያን እንዲሁም ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ የቀደመ ኢኮኖሚ ይሆናሉ የሚል ትንበያ ነው ጥናቱ የሚያሳየው::
ኢትዮጵያ ርዕዩን ለማሳካት በቀጣይ ማተኮተር ያለባት
ኢትዮጵያ በቀጣይ ማተኮር ያለባት ምን አይነት ዘርፎች ላይ ነው ሲባል እስከ 2030 ድረስ በእቅድ ላይ የተቀመጡ የትኩረት መስኮች አሉ:: ከ2030 እስከ 2040 በትራንስፖርት ላይ፣ ኬሚካልና የኬሚካል ምርት ላይ ሜጋ ማሽኖች፣ ብረትና የብረት ውጤቶች፣ የሚዲካል ኢኩፕመንት፣ የመኪና መገጣጠሚያ እና የመኪና መለዋወጫዎችን ላይ አተኩረን ብንሰራ የሚል ነው::
ከ2040 እስከ 2050 ደግሞ የኤሌክትሪክ ማሽኖችን፣ ሰሚ ኮንዳክተሮችን፣ ኮምፒውተሮችን፣ አውቶሞቲቮችን፣ የቴሌኮም መሳሪያዎችነን፣ የሶላር ኢነርጂ መሳሪያዎችን እና ትልልቅ ትራኮችን ላይ ትኩረት አድርገን ብንሰራ ጥሩ ይሆናል የሚል ነው:: የተቀመጠውንም ግብ ማሳካት ያስችለናል የሚል ነው::
ኢኮኖሚውን ለማሻገር ምን ያስፈልጋል
የውጭ ካፒታልን መሳብ ያስፈልጋል:: የመንግስት አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል:: ሰላምንና ሕግን ማረጋገጥ ያስፈልጋል:: የአገር ውስጥ የቁጠባ ባሕልን ከፍ ማድረግ የግድ ይላል:: ጠንካራ የፋይናንስ ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋል:: ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ትልቅ ሚና መጫወት ይኖርበታል:: የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው ሚና ማሳደግና መንግስትም ለዚህ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅበታል:: ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅምን ማሳደግ ተገቢ ነው:: የሰውና የካፒታል ነጻ እንቅስቃሴ በአገር ውስጥ በደንብ ሊሰራበት ይገባል:: የፌዴራል መንግስት ከክልሎች፣ ክልሎች ከፌዴራል መንግስት ጋር ያላቸው ግንኙነት ሊጠናከር ይገባል:: እንዲሁም የሰው ሀብት ልማቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል::
ከግሉ ዘርፍ የሚጠበቀው
የግሉ ዘርፍ በተፈጥሮ ሪስክ አቮይድ ስለሚያደርግ ሪስካቸው ዝቅ ያለ፤ ነገር ግን ከትራንስፎርሜሽን አኳያ ጥሩ የማንላቸው ዘርፎች ላይ የማተኮር ባህሪ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባህሪ መሆኑ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት:: ይህንን ግን መንግስት መደገፍ ይኖርበታል:: በተለይም ሪስኩን በመጋራት ደረጃ መደገፍ ይኖርበታል::
ይሁንና የግሉ ዘርፍ አስቀድሜ የጠቀስኩት የ60 ዓመታት አልተሳኩልንም ብለን ካልንባቸው ምክንያቶች አንዱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መልማት አለመቻል ነውና የግሉ ዘርፍ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ላይ በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ ኢንቨስት የማድረግ ልምምድ መጠናከር አለበት::
ስነ ምግባር የታከለበትና የንግድ እንቅስቃሴ ማካሔድ ይጠበቃል:: በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ታክስ መክፈልም ከግሉ ዘርፍ የሚጠበቅ ነው:: የቴክኖሎጂ እድገት ላይ መንግስት የሚኖረው ሚና እንዳለ ሆኖ ኢንቨስት ማድረግ ይኖርበታል::
በተመሳሳይ ደግሞ የፋይናንስ ሴክተሩ ተወወዳዳሪ የሆነ አገልግሎት መስጠት አለበት፤ አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ መሆን ይጠበቅበታል:: ጤናማ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴን ማበረታታት አለበት:: ከአዲስ ቴክኖሎጂ ጋር ፈጥነው እራሳቸውን ማዋሃድም ይኖርባቸዋል::
በጥቅሉ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በቴክኖሎጂ ብቻ የሚዘወር መሆኑን ማየት ችለናል:: በዚህ ምክንያት የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን በጣም ዝቅተኛ ስለነበር ያለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ጉዟችን አሻጋሪ እንዳልነበር አይተናል:: ቀጣዮቹ ሃምሳና ስልሳ ዓመታት እንዳይባክኑብን መሰረት የሚጥሉ ስራዎች ሪፎርሞች ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል:: በዚህ ውስጥ የመንግስት ሚና በጣም ትልቅ ይሆናል:: ዜጎችም በዚህ ጉዳይ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2017 ዓ.ም