“እንደ ተቋም በኮሪዶር ልማቱ ዘላቂ ተጠቃሚነትን አግኝተናል” – አቶ መላኩ ታዬ

– አቶ መላኩ ታዬ የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር

በኢትዮጵያ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም ዛሬም ድረስ በርካታ ዜጎች ለመብራት አገልግሎት የሚውል ኃይል እንኳን እያገኙ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱንም በለውጥ መንገድ ላይ መሆኑ በተደጋጋሚ ቢነገርም ዛሬም ድረስ ከተጠቃሚዎች የሚነሱ በርካታ ቅሬታዎች መኖራቸው ይታወቃል። እኛም ለዛሬው ዝግጅታችን ለእነዚህ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ የሰጧቸውን ምላሾች እንደሚከተለው አዘጋጅተን አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- አገልግሎቱ ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አኳያና ራሱን በማደራጀት ረገድ ሲሰራቸው የነበሩ ተግባራት እንዴት ይገለጻሉ ?

አቶ መላኩ፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ሁለንታናዊ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። የቅርብ ጊዜውን እንኳን ብንመለከት ያለፉት አራት ወራት ከመቼውም ጊዜ የላቀ ውጤት የተመዘገበባቸው ነበሩ ማለት ይቻላል። አገልግሎቱ ራሱን ለማሻሻል ከሚሰራቸው ቀዳሚ ስራዎች መካከል በሰው ኃይልና እና በግብአት ራሱን ለማደራጀት አንዲችል በቂ ገቢ መሰብሰብ ነው። በዚህም ረገድ አገልግሎቱ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከኢነርጂ ሽያጭ፣ ከአዲስ ደንበኞች መስተንግዶ፣ ከማያገለግሉ ንብረቶች ሽያጭ እና ከሌሎች ልዩ ልዩ የገቢ ምንጮች በአጠቃላይ 11 ነጥብ 55 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 11 ነጥብ አስራ 15 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ አመርቂ አፈፃፀም ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

በተጨማሪ ከኢነርጂ ሽያጭም ብር ስምንት ነጥብ 26 ቢሊየን ለመሰብሰብ ታቅዶ ስምንት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህም ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው ስድስት ነጥብ 21 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የ32 ነጥብ አንድ በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ከአዲስ ደንበኞች አገልግሎት ከተገኘ ገቢም ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር፥ እንዲሁም የማያገለግሉ ንብረቶችን በማስወገድና ከልዩ ልዩ የተገኘ ገቢ አፈፃፀም 183 ነጥብ ሶሰት ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር 41 ነጥብ አራት በመቶ ብልጫ አሳይቷል። ምንም እንኳን ይህ አሃዝ አገልግሎቱ ሊደርስበት ከሚገባውና አጠቃላይ እቅዱና እንደ ሀገር ከሚጠበቀው ለውጥ አንጻር ብዙ የሚቀረው ቢሆንም በተስተካከለ መንገድ ላይ መሆኑን ግን የሚያመላክት ነው።

ሌላው አገልግሎቱ እንደ እቅድ እየሰራባቸው ካሉ ጉዳዮች መካከል የተደራሽነት አድማሱን ማስፋት ነው። በዚህ ረገድ በሩብ ዓመቱ 120 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ከ90 ሺህ 726 በላይ አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በ2015 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት 46 ሺህ 713 አዳዲስ ደንበኞችን ነበር የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለው። አጠቃላይ የተቋሙን የደንበኛ ቁጥር ወደ አራት ሚሊዮን 850 ሺህ 800 ለማሳደግ በቅቷል። ባለፉት ሦስት ወራት ሰፊ የቅድመ መከላከል ጥገና፣ የአስቸኳይ ጥገና፣ የማሻሻያና መልሶ ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል። አዲስ 31 የገጠር ቀበሌዎችን ከዋናው ቋት (ግሪድ) በማገናኘት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 26 የገጠር ቀበሌዎችን ለማገናኘት ተችሏል። በዚህ ሁሉ ሂደት ለሦስት ሺህ 376 ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ተችሏል።

እነዚህን ስራዎች ለማከናወን እና ከላይ የተጠቀሰውን ውጤት ለማስገኘት የአገልግሎቱ ሰራተኞች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል። የሰሜኑ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ በትግራይ መልሶ ግንባታ እግር በእግር እየተከታተለ በማካሄድ ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ለዚህ እንደ አብነት ይጠቀሳሉ። በቅርቡም በምእራብ ኦሮሚያ በወለጋ እና አካባቢው ለዓመታት ያለ ኤሌክትሪክ የቆዩ ከ150 በላይ አካባቢዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል። ለዚህ ውጤት ተቋሙም እንደ አሰራር ሰራተኞቹም እንደ አንድ ግለሰብ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም በመሆን የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብዙ ተሰርቷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰራተኞች የአደጋ መከላከያ ቁሳቁስ በማቅረብና በእንቅስቀሴ ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የተካሄዱ ስልጠናዎችም ውጤታማ በመሆናቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጉዳት የሚዳረጉ ሰራተኞችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል። በሶስተኛ ወገን በሕብረተሰቡ ላይ እየደረሱ ያሉ አደጋዎች ግን ዛሬም ትኩረት የሚፈልጉ ናቸው። በተለይም ከቆጣሪ ውጪ ወደ ቤት በሚገባ መስመር በሚፈጠር ንክኪ በሚደረስ አደጋ። እንዲሁም ከአንድ ግለሰብ ወደሌላ ሰው ቤት በሕገወጥ መንገድ ደረጃውን ባልጠበቀ ገመድ ኤሌክትሪክ በመውሰድና በቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ እቃዎች ጋር በተያያዘ የሚደርሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል።

አዲስ ዘመን ፡- አገልግሎቱ ለሕብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በማቀላጠፍ እና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ ምን ምን ስራዎችን አከናውኗል ?

አቶ መላኩ፡- በሩብ ዓመቱ የተለያዩ የክፍያ አማራጮችን በማስፋፋት በተለይ የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። በአሁኑ ወቅት ከድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች ውስጥ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ወርሃዊ የፍጆታ ክፍያቸውን እያከናወኑ ያሉት በዲጂታል የክፍያ አማራጭ ነው። በዚህም ከሁለትና ከሶስት ዓመታት በፊት በየቦታው ይታይ የነበረውንና በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረውን ረዥም ሰልፍ ማስቀረት ችለናል። የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚ በተጨማሪም ደንበኞችም ወደ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በመቅረብ ኃይል መሙላት ሳያስፈልጋቸው ቤታቸው ሆነው በኦንላይን የሚከፍሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ያሉ ሲሆን በዚህ ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይታሰባል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 120 ሺህ አዳዲስ ደንበኞች 62 በመቶ የሚሆኑት በተቀመጠው የጊዜ እቅድ መሰረት ኤሌክትሪክ አገልገሎት ለማግኘት በጠየቁ በአስር ቀናት ውስጥ ቆጣሪ እንዲገባላቸው ማድረግ ተችሏል። በቅርቡ ደግሞ «አንድ ቀን የኤሌክትሪክ ዘመቻ የሚል » በማካሄድ በተለያዩ ቦታዎች ጥያቄው በቀረበበት ቀን ቆጣሪ እንዲያገኙ እየተደረገም ይገኛል። ይህ አሰራር ዛሬም ድረስ እየተተገበረ ያለና ለብዙዎች እፎይታ የሰጠም ነው።

ይህም ሆኖ አገልግሎቱ ውድ እንደመሆኑ ለብልሹ አሰራር ተጋላጭ መሆኑ ግልጽ ነው። በዚህም ከአዲስ አገልግሎት ፈላጊ ጋር እና ከአስቸኳይ ጥገና ጋር በተያያዘ የሚታያዩ በርካታ ክፍተቶች ነበሩ። ይህንን በዘላቂነት ለመፍታት ቀዳሚው መንገድ ቴክኖሎጂ መጠቀም ነው። ይህም አገልግሎት ጥያቄ የማቅረቡን ሂደት እና ቅሬታ የማቅረብንም አካሄድ የሚመለከት ይሆናል። ይህም ሆኖ በማንኛውም ጊዜ በሙስና እና በብልሹ አሰራር የሚገኙ የተቋሙ ሰራተኞች ላይ ተገቢውና አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡ ይህ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- መንግስት ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ በጣም የተጋነነ ከመሆኑ በተጨማሪ ወቅቱን ያላገናዘበና የዜጎችንም አቅም ከግምት ያላስገባ ነው ይባላል። የታሪፍ ማስተካከያ ለማድረግ ሲወሰን በአገልግሎቱ በኩል ምን ጥናት ተካሂዶ ነው?

አቶ መላኩ፡- የታሪፍ ማሻሻያው በኢነርጂ መመሪያው መሰረት በየአራት ዓመቱ ተግባራዊ የሚደረግ ነው። ነገር ግን የዛሬ ሁለት ዓመት ማሻሻያው ባለመደረጉ አሁን እየተተገበረ ያለው ከስድስት ዓመት በኋላ መሆኑ መታወቅ አለበት። ላለፉት ሁለት ዓመታት ተገልጋዩ ክፍያ ሲፈጽም የነበረው ማሻሻያ ሳይደረግ ቀድሞ በነበረው ነው። ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ግን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተውጣጡ ባለሙያዎች ረዘም ያለ ዝርዘር ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። በተጨማሪም ተመሳሳይ ጥናት በሶስተኛ ወገን እንዲካሄድ ተደርጓል። ይህንን ጥናት መሰረት በማድረግ የአገልግሎቱ ተቆጣጣሪ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ጥናቱን መርምሮ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀ ታሪፍ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ምንም እንኳን ታሪፉ የጸደቀው ከ2016 ዓ.ም ከሰኔ ወር በፊት ቢሆንም ተግባራዊ የሚደረገው ከዘንድሮ መስከረም አንድ ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ጥናቱ የተካሄደው በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ካለው ሀገራዊ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሪፎርምም በፊት የተጠናቀቀ ነው። ጥናቱ ሲካሄድ ከግምት አስገብቶ መረጃ ሲሰበስብባቸው ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ የኅብረተሰቡ የመክፈል አቅም ነበር። በዚህም የአገልግሎቱ 65 በመቶ የሚሆነው ደንበኛ ከ50 ኪሎ ዋት በታች የሚጠቀም ነው። እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚጠቀሙት የኃይል መጠን በጣም ዝቅተኛ ሲሆን፣ ከአጠቃለይ ኃይል ስምንት በመቶ ብቻ የሚወስድ ነው። በዚህም መነሻ ከዜሮ እስከ ሀምሳ ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች የ75 በመቶ የታሪፍ ማሻሻያ ድጎማ ተጠቃሚ ናቸው።

በተመሳሳይ ከ51 እስከ አንድ መቶ ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች 40 በመቶ የታሪፍ ማሻሻያ ድጎማ ተጠቃሚ ናቸው። እንዲህ እያለ ሄዶ እስከ 300 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙት ደግሞ አራት በመቶ የታሪፍ ማሻሻያ ድጎማ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ከዚህ በላይ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች በመጀመሪያ ደረጃ በቁጥር በጣም ትንሽ ሲሆኑ፣ በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ በመሆኑ ከፍተኛ ገቢ ያገኛል ተብሎ ይታሰባል። በመሆኑም በእነዚህ ለይ ታሪፉ ሙሉ ለሙሉ የሚተገበር ይሆናል።

ይህም ሆኖ ከዚህ በፊት የታሪፍ ማሻሻያዎች ተግባራዊ ሲደረጉ ምንም እንኳን በየአራት ዓመቱ የሚደረጉ ቢሆንም ከጸደቁበት ጊዜ አንስቶ ጭማሪውን በሙሉ ተገልጋዩ እንዲከፍል ይደረግ ነበር። በአሁኑ ዓመት ግን ከቀደመው በተለየ አካሄድ የማኅበረሰቡን የመክፈል አቅም ከግምት በማስገባት የሚኖርበትን ጫና ለመቀነስ ክፍያው በየሩብ ዓመቱ እየተሻሻለ እንዲሄድ ተደርጓል። ይህም ማለት በጥናቱ የተወሰነውና የጸደቀው የገንዘብ መጠን ሙሉ ለሙሉ የሚተገበረው የዛሬ ዓመት ይሆናል ማለት ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በዋናነት ሊታወቅ የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ የታሪፍ ማሻሻያ ለምን ይደረጋል የሚለው ነው።

ይህንን ስንመለከት ለኤሌክትሪክ አገልግሎት የምንጠቀምባቸው መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት የሚውሉ ግብአቶች ከሰባ በመቶ በላይ ከሌሎች ሀገራት በውጪ ምንዛሬ የሚገባ ነው። እነዚህ ግብአቶች ከዓለም ገበያ የሚሸመቱ በመሆናቸው ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስፈልግ ይሆናል። ማለትም አገልግሎቱ በትንሹ በየወቅቱ የሚያወጣውን ወጪ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እየሸፈነ መቀጠል ይኖርበታል። ይህ የሚደረገውም በአንድ ወገን አገልግሎቱ አሁን እየሰጠ ያለውን አገልግሎት እንዳያቋርጥ ወይንም እንዳይቀንስ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በየወቅቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ፍላጎት የሚቀርብ በመሆኑ እነዚያን ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ኃላፊነትም ስላለበት ነው።

በተጨማሪ ሁሉም ደንበኞች ሊባል በሚያስደፍር መልኩ ዘመኑ የደረሰበትን የተሻሻለ ዘመናዊ አገልግሎት ማግኘት ይፈልጋሉ። ወቅቱን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ በየከተማው የመልሶ ግንባታና የኔትወርክ ማሻሻያ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። እንደ ሀገር በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚው ሕዝብ ቁጥር እንደ ሀገር ከ54 በመቶ የዘለለ አይደለም። ይህ ማለት አገልግሎቱ ቀሪውን 46 በመቶ ዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የማድረግ ኃላፊነት ይጠበቅበታል ማለት ነው። እነዚህ ከላይ ያነሳናቸው ዝርዝሮች እንደሚያመለክቱት የታሪፍ ማሻሻያው ጊዜውን ያማከለ፣ ተመጣጣኝ እና የተሻለ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለመስጠት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር እየተካሄደ ባለው የኮሪዶር ልማት በርካታ ቤቶች ሲነሱ የኤሌክትሪክ መቋረጥ እንደተከሰተ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ የፍጆታ ክፍያና የአገልግሎቱን ሀብቶች በመሰብሰብ ረገድ ምን ምን ተግባራትን አከናውናችኋል ?

አቶ መላኩ ፡-የኮሪዶር ልማቱን ተከትሎ ከአገልግሎቱ በርካታ ስራዎች ይጠበቁ እንደነበር እናውቃለን። በዚህም መሰረት ከተጀመረ አንስቶ ከሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን። በእያንዳንዱ የኮሪዶር ልማት አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥም የአገልግሎቱ ተወካዮች እንዲኖሩ ተደርጓል። በመጀመሪያው ዙር የአዲስ አበባ የኮሪዶር ልማት 24 ሰዓት ስንሰራ ነበር። ከኮሪዶር ልማቱ በፊት የነበሩን ኔትወርኮች በጣም አስቸጋሪ የነበሩ እንደ ሸረሪት ድር እርስ በእርስ የተጠላለፉና ለአደጋና ለኃይል መቆራረጥ ምቹ የሆኑ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን የኮሪዶር ልማቱ በተከናወነባቸው ቦታዎች በሙሉ መስመሮች ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ በመሬት ውስጥ እንዲገነቡ ለማድረግ ተችሏል። በኮሪዶር ልማቱ በተነሱ ሰፈሮች የነበሩ ቤቶች ላይ ካሉ ቆጣሪዎች ከመነሳታቸው በፊት በባለሙያዎች የተጠቀሙትን ንባብ ወስደናል።

በዚህም ክፍያ ያለበት እንዲከፍል እየተደረገ ቆጣሪው ወደተቋሙ እንዲለመለስ ተደርጓል። ሌላ ቦታ ሲገቡ አዲስ የኃይል መስመር የሚዘረጋላቸውም የመጀመሪያውን አገልግሎት ማጠናቀቃቸውን የሚገልጽ ማረጋገጫ ሲያቀርቡ ነው። አሁንም ሁለተኛውን ዙር በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች በየሳምንቱ እየተከታተልን እየገመገምን እየሰራንበት ይገኛል። የኮሪዶር ልማቱ ከግብአት እጥረት አንጻር የገጠሙ ክፍተቶች ቢኖሩም እንዳጠቃላይ ለአገልግሎቱ ብዙ ትምህርቶችንም የሰጠ ነው ለማለት ያስደፍራል። ከዚህ ቀደም ዓመታት ይወስዱ የነበሩ ስራዎችን ቀን ከሌሊት በመስራት በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ የሚያስችለን ብቃት አግኝተንበታል። የስራ ባህላችንንም ፈትሸን እንድንቀይር ያስቻለም ነው። በዚህም እንደ ተቋም በኮሪዶር ልማቱ ዘላቂ ተጠቃሚነትን አግኝተናል ለማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን ፡- አገልግሎቱን በተመለከተ በተደጋጋሚና በስፋት ከሚነሱ ቅሬታዎች መካከል የኃይል መቆራረጥ ይነሳል። እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች ፈረቃ ከተጀመረ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለምን በግልጽ አይነገረንም እስከማለት የተደረሰበት ሁኔታ በዚህ ረገድ ምን ስራ እየተከናወነ ይገኛል ?

አቶ መላኩ፡– የኃይል መቆራረጥ ችግር በአንዳንድ አካባቢዎች መኖሩን እናውቃለን። በፈረቃ አገልግሎት እየተሰጠ እንዳልሆነ ግን ሁሉም ዜጋ ሊያውቅ ይገባል። የኃይል መቆራረጥ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያልተደገፈ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማቅረቢያ መሰረተ ልማት ባላቸው ሀገራት ይቅርና ባደጉትም ሀገራት የሚከሰት ነው። የኃይል መቆራረጥን ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ባይቻልም መቀነስ ግን እንደሚቻል ግልጽ ነው። በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው የኃይል መቆራረጥ የመጀመሪያው ምክንያት መሰረተ ልማቶቹ ለረዥም ዓመት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩና ያረጁ በመሆናቸው ነው። እነዚህ መሰረተ ልማቶች ዛሬ ያለውን ተገልጋይ ታሳቢ አድርገው የተገነቡ ባለመሆናቸው የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እየሰጡም አይደለም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር ከተሞች በከፍተኛ ደረጃ እያደጉና እየተስፋፉ ይገኛል።

ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቁ ትልልቅ ፎቆች በሁለም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተገነቡ ሲሆን ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠይቁ ኢንዱስትሪዎችም በስፋት እየተገነቡ ይገኛል። በአንጻሩ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከማመንጫ ጣቢያዎች የሚወጣውን ኃይል አስተላልፎ ወደ ተገልጋዩ ሊያደርስ የሚችለው መሰረተ ልማት ያለውን እድገት በሚሸከም መልኩ እያደገ አልመጣም። በዚህ ምክንያት በበርካታ ቦታዎች በማስተላለፊያዎች ችግር የኃይል መቆራረጥ ይገጥማል።

በተጨማሪ ደግሞ በየወቅቱ ቀላል የማይባል እንደ ስርቆት እና ውድመት ያሉ ሰሰው ሰራሽ ችግሮች በመሰረተ ልማቶች ላይ እየደረሱ የኃይል መቆራረጥ እንዲከሰት ምክንያት እየሆነ ይገኛል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰነ መሻሻል ቢታይም የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚደርሰው ዝርፊያና ውድመት ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት እየሆኑ ይገኛል።

እነዚህ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያለማቸውና የሚያስተዳድራቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስር ባሉትም የሚፈጸም ነው። በዚህ ረገድ ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት የሆኑ በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ ምሰሶዎች ላይ የተፈጸሙ ዝርፊያና ጉዳቶች ነበሩ። ለአብነት ወደ አሶሳ በሚሄደው መስመር ላይ በተደጋጋሚ ሲከሰት የነበረውን ማስታወስ ይቻላል። ለዚህ አገልግሎቱ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የጸጥታ አካላትና ኅብረተሰቡም የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል። የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽንና የብልሽት ማስተካከያ ቆይታ ጊዜን ለማሳጠር አጠቃላይ ችግሮችን ለመቅረፍ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል። ይህንንም ይበልጥ ለመቀነስ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሻሽሉ በርካታ ፕሮጀክቶችና የእድሳት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል። በሩብ ዓመቱ በተጣሩ የብልሹ አሠራር ጥቆማዎች መሠረት ሀያ የአገልግሎቱ ሠራተኞችን እና አመራሮች ተጠያቂ ተደርገው ጉዳያቸው በየደረጃው በሚመለከተው አካል እንዲታይ ተደርጓል።

በዚህም ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ ደመወዝ የመቁረጥ፤ ከስራ የማሰናበትና እንደ ጥፋቱ በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ርምጃዎች ተወስደዋል። ይህም ሆኖ ከላይ ከተጠቀሱት ውጪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሁለት ምክንያቶች ብቻ እሱንም ለማኅበረሰቡ በማሳወቅ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲቋረጥ የሚያደርግባቸው አጋጣሚዎች አሉ። አንደኛው እያረጁ ያሉ ኔት ወርኮችን መልሶ ለመገንባት ሰፋፊ ሜጋ ፕሮጀክቶች በየከተሞች እየተከናወኑ ይገኛል። በዚህ ወቅት በታቀደ መልኩ ኃይል የሚቋረጥ ሲሆን ይህም ለደንበኞች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን መረጃው ተደራሽ የሚደረግ ይሆናል። ሁለተኛው በተመሳሳይ በታቀደ መልኩ የቅድመ መከላከል ስራዎች ሲከናወኑ ነባሩን ኮሪዶር በመከተል የሚሰራ በመሆኑ የኃይል መቆራረጥ ይከሰታል።

ከዚህ ውጪ አንዳንድ ችግሮች ደርሰው አስቸኳይ ጥገና ማድረግ ሲያስፈልግ ለአጭር ጊዜ የሚኖር የኃይል መቆራረጥ ይኖራል። ይህም ሆኖ አንዳንዶቹ ችግሮች ከአገልግሎቱ አቅም በላይ ሲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመቅፍ እየተሰራ ይገኛል። ባጠቃላይም የኃይል መጥፋት የቆይታ ጊዜውም ሆነ ድግግሞሹ ከዚህ በፊት ከነበረው ከፍተኛ መሻሻሎች የታዩበት ነው።

ይህም ሆኖ የኃይል መቆራረጡን በሚፈለገው ልክ ደርሷል ለማለት አያስችልም። በተጨማሪም የቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ ወይም ምላሽ አሰጣጡ ተገልጋዮች በሚጠብቁት ልክ አለመሆኑንም እንገነዘባለን። አንዳንድ ፕሮጀክቶችም በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቃቸው ይታወቃል። በመሆኑም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እነዚህ ችግሮች መቶ በመቶ መቅረፍ ባይቻል እንኳን አፈጻጸሙ ከሕዝቡ ፍላጎትና ጥያቄ ጋር የተቀራረበ እንዲሆን በርካታ ስራዎችን ለማከናወን እቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን ፡- ስለነበረን ጊዜ እናመሰግናለን።

አቶ መላኩ ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You