የባሕር በርን በተመለከተ የሚካሄድ ትግል

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የባሕር በር ከሌላቸው አስራ ሰባት ሀገሮች ሕዝቦች የሲሶው መኖሪያ ናት። አንድ መቶ ሀያ ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ ይዞ የባሕር በር የሌለው ሀገርም ከኢትዮጵያ ውጪ ማንም የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዳር ወር 2016 ዓ.ም የቀይ ባሕር አስፈላጊነትንና የባሕር በር ጉዳይን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ካቀረቡበት ጊዜ አንስቶ በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ሃሳቦች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀይ ባሕር የጋራ ተጠቃሚነትም ሆነ የባሕር በር ጥያቄ መጠየቅ ለኢትዮጵያ ትርፍ ጥያቄ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ እንደሆነም አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ሕልውና እና ልዕልና ከቀይ ባሕር ጋር የተሳሰረ ነው። የኢትዮጵያ የዘመኑ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ሠላምና አንድነትን ማስፈን፣ ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ በውሃ ተከባ ነገር ግን ውሃ የሚጠማት ሀገር ናት፣ ቀይ ባሕርና ዓባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ ከኢትዮጵያ የተቆራኙ ለኢትዮጵያ እድገትና ጥፋት መሠረት ናቸው። የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የመሆን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚ ጭምር ነው፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር ፍላጎቷን ማሳካት ትፈልጋለች ብለዋል።

አሁን አይቻልም ማለት ነገ አይቻልም ማለት ባለመሆኑ ተነጋግሮ ከተሳካ ይሳካል እንጂ ተዳፍኖ ይቅር የሚባል አይደለም ብለውም ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በቀጥታ በጉዳዩ ላይ ቅሬታ ካሰማችው ሱማልያ ጋር አንዳንድ ሀገራትም በጉዳዩ ዙሪያ እያንዣበቡ ይገኛል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ እየሰራችበት ባለው የባሕር በር የማግኘት እንቅስቃሴ የአንዳንድ ጎረቤት ሀገራት ምላሽ ለምን ቀና አልሆነም ስንል ባለሙያዎችን አነጋግረናል።

በዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተመራማሪና የሰላምና የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ደሳለኝ ማስሬ ላነሳንላቸው ጥያቄ በሰጡን ምላሽ ላይ እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ በራሷ የምትቆጣጠረው በራሷ የምታለማው የባሕር በር አንዲኖራት የተለያዩ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች።

ነገር ግን በቅርቡ ከሱማሌ ላንድ ጋር ያደረገችው የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት እያደረጉት ያለውን አንቅስቃሴ አይተናል። የእዚህም መነሻ ሊሆን የሚችለው አንደኛው ኢትዮጵያ የባሕር በር ካገኘች በቀጣናው ያላት ተቀባይነት እየጨመረ መምጣቱ አይቀርም። ይህም ለሀገሪቱ በፖለቲካና ኢኮኖሚው መስክ ተቀባይነት ከማስገኘት ባለፈ በጸጥታው ዘርፍ ከፍተኛ አቅም ስለሚፈጥር የበላይነታችንን እናጣለን ከሚል ስጋት ነው።

ሌላኛው ምክንያት የኢኮኖሚ ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ዘጠና በመቶ የሚሆነውን የወጪ ንግድ የምታስተናግደው በጎረቤት ሀገራት በኩል ነው። ጅቡቲ ከዓመታዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ስልሳ በመቶ የሚሸፈነው ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ በምታስገባቸውና በምታስወጣቸው ምርቶች ነው። ይህንን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር ካላት፤ ይህ ነገር ሊቀንስ ይችላል ወይም ሙሉ ለሙሉ ይቋረጣል የሚል ስጋት አለ።

ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚያዊ እድገቷ ፈታኝ ከሆኑባት ጉዳዮች ቀዳሚው የሯሷ የባሕር በር አለመኖሯ ነው። በዚህም በአገሪቱ በዓመት ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ ለባሕር በር አገልግሎት ትከፍላለች። የባሕር በር ባለቤት ከሆነች፤ ይህ ገንዘብ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስክ በሀገር ውስጥ ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ ማሰብ ቀላል ነው ይላሉ።

በሌላ በኩል የጸጥታ ጉዳዩም ከግምት ይገባል። ቀኝ ገዢ የነበሩት አውሮፓ ሀገራት ወደ ቀጣናው ይገቡ የነበረው በቀይ ባሕር በኩል ነበር። ኢትዮጵያ የራሷን የባሕር በር በምታስተዳድርበት በዛ ዘመን እነዚህን ቀኝ ገዢዎችና ከጎረቤት ሀገራት የሚመጡ ወራሪዎች አሳፍራ ለመመለስ ችላለች።

ከዛ በኋላም ኢትዮጵያ የኤርትራ መገንጠልን ተከትሎ የባሕር በር አልባ ከሆነች በኋላም ለራሷ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሀገራትም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጠንካራ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን አስመስክራለች። በዚህ መነሻነት ሀገሪቱ የባሕር በር ካገኘችና የራሷን የባሕር ኃይል መገንባት ከቻለች በአካባቢው ጠንካራ ኃይል ትፈጥራለች የሚልም ስጋትም ያለባቸው መሆኑን ይገልፃሉ።

እንደ አቶ ደሳለኝ ገለፃ፤ እነዚህ ነገሮች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ በአንድ ወገን እንደ ጅቡቲ ያሉ ሀገራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን መነሻ በማድረግ ጥቅም እንዳይቋረጥባቸው ሲሉ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች አሉ። በሌላ በኩል እንደ ኤርትራ ያሉ ሀገራት ኢትዮጵያ እየተጠናከረች መምጣት ካላቸው ታሪካዊ ግንኙነት አኳያ ስጋት ትሆንብናለች በሚል ነው።

ዋናዋ ተቃዋሚ ሶማልያ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ይህ ነው የሚባል መንግስት ያልመሰረተች የራሷን ሰላምና ደህንነት በቅጡ ማስጠበቅ ያልቻለች ሀገር ናት። አልሸባብና ሌሎች የታጠቁ ኃይሎች ዛሬም ድረስ እንዳሻቸው እያመሷት ይገኛል። በየአካባቢው ካለው አስተዳደር ይልቅ በየመንደሩ ያሉ ታጣቂዎች ተሰሚነትና ተቀባይነት የሚያገኙባት ሀገር ናት።

አሁን ያሉት ፕሬዚዳንትም በቅርብ የመጡ ቢሆንም በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በመሆኑም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የሀገራችንን ዳር ድንበር አስከብራለሁ በሚል ሰበብ ተቀባይነትና ተደማጭነት ለማግኘት የመረጡት አካሄድ ነው። ይህን የሚያሳየው ሶማልያ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ተጽእኖ አሳድራብኛለች የሚል ወሬ በመንዛት እና ስም በማጥፋት የአፍሪካ ሕብረት ከአዲስ አበባ አንዲነሳ ሞክራለች።

ከግብጽና ከሱዳን ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ጸብ አጫሪ ሀገር ተብላ እንድትፈረጅም ሲሰሩ ነበር። ሌላው ከሕዳሴው ግድብና ከሌሎች ታሪካዊ ግንኙነቶች በመነሳት ግብጽ ኢትዮጵያን ደካማና ሁል ጊዜ በፈተናዎች የታጀበች ሀገር ለማድረግ የጀመሩት እንቅስቃሴ ነው።

ይህም ሆኖ ጥያቄው ተገቢና ፍትሃዊነት ያለው በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል እንደቀጠለ ይገኛል። በመሰረቱ ኢትዮጵያ በታሪኳ የትኛውንም ሀገር ወርራ አታውቅም። የትኛውንም ሀገር ጥቅም ለማሳጣትም ተንቀሳቅሳ አታውቅም። አሁንም እየተንቀሳቀሰች ያለችው የየትኛውንም ሀገር ሉአላዊነት እና ጥቅም በሚጋፋ መልኩ አለመሆኑ ጥያቄው የጊዜ ጉዳይ እንጂ መሳካቱ አንደማይቀር አመላካች ነው ይላሉ።

በተመሳሳይ «ኢትዮጵያ የባሕር በር የምትፈልገው በሌሎች ላይ ለመዝመት ወይም ተጽእኖ ለማሳደር አይደለም።» የሚሉት ደግሞ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አደም ካሚል ናቸው። ፕሮፌሰር አደም እንደሚገልጹት፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር የሚያስፈልጋት ምርቶቿን ወደ ውጪ በመላክና ገቢ በማግኘት ስራ አጥነትን ለመቅረፍ ብሎም ሕገወጥ ፍልሰትን ለማስቀረት እና አጠቃላይ ድህነትንን ለማጥፋት ነው።

ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባው ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ምርት ወደ ውጪ የምትልከውም ስላላት ደህንነቱ የተጠበቀ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ወደብ የማስፈለጉ ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም። በኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሶማልያም ሆነ የሌሎች ሀገራት ቅሬታ ውስጥ መግባትም ጥቅማቸውን መሰረት በማድረግና ኢትዮጵያን ለማዳከም በማሰብ እንጂ ውሃ የሚቋጥር ስጋት ስላለባቸው አይደለም። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ግብጽ ውስጥ ሰላሳ ሺህ የሚሆኑ የሳውዲ ኩባንያዎች ሰባት ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ካፒታል በመያዝ እየተንቀሳቀሱ ናቸው።

የገልፍ ሀገራት ደግሞ የምግብ ዋስትና እና የውሃ ችግር አለባቸው። ግብጾች እነዚህን ሁሉ የሚያስተናግዱትና ለዚህ ምላሽ የሚሰጡት ከኢትዮጵያ በአባይ አማካይነት የሚሄደውን ውሃና ለም አፈር በመጠቀም ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ ሰላም ካገኘችና አንድነቷን ማጠናከር ከቻለች እነዚህን ኢንቨስተሮች ይነጥቁናል የሚልም ስጋት አለባቸው። በእርግጥም ኢትዮጵያ ሰላም ከሆነች ምርቶቿን ከመላክ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከመሆን ባለፈ በቱሪዝምም ተመራጭ ሀገር መሆኗ አይቀርም ይላሉ።

ከረሀብ እንውጣ፤ ከድህነት እንውጣ፤ ከኋላ ቀርነት እንውጣ የሚል ለውጥ እየታወጀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ግብጾች ኢትዮጵያ ከበለጸገች ለእኛም ሆነ ለአካባቢው ስጋት ትሆናለች ብለው ያስባሉ። በመሆኑም ይህንን ለመቀልበስ ማዳከም አለብን በማለት አጀንዳ አስቀምጠው ውስጥ ለውስጥ እየሰሩበት ይገኛል። ይህ ነገር በተለይ የግብጾችን ሚድያ ለሚከታተል ሰው አዲስ አይሆንም። ግብጾች በርካታ ሚድያዎች ያላቸው ሲሆን፤ ለቁጥር የሚታክቱ ጋዜጠኞችን በዚህ ላይ እያሰሩ ይገኛሉ። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ አሁንም በዲፕሎማሲው መስክ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ከቻለች ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በአረቡ ዓለም ዘንድ የተለየ ቦታ የሚኖራት ይሆናል ብለዋል።

በሌላ በኩል ጸጥታን በተመለከተ ቀይ ባሕር ራሱ አካባቢው ሰላም አለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። መካከለኛው ምስራቅ እስራኤል፤ ኢራን፤ የመን አጠቃላይ አካባቢው ቀውስና ጦርነት ውስጥ ናቸው። በዚህ ሂደት ደግሞ ሁሉም የቀጣናው ሀገራት ሲመቻች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በጉዳዩ ውስጥ እጃቸውን ሲያስገቡ ይታያል።

እዚህ ላይ ዋናው መታየት ያለበት፤ ነገር ለምን የባሕር በር ጥያቄና ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረግ የግንኙነት ጉዳይ የኢትዮጵያ ሲሆን፤ በልዩነት ይታያል የሚለው ነው። ከዚህ ቀደም አረብ ኢምሬትስ በበርበራ ላይ ስምምነት አድርገው ፊርማ ተፈራርመዋል።

የዛን ጊዜ እንኳን የዚህ ያህል ጩኸት ይቅርና ምንም የተባለ ነገር አልነበረም። ዛሬ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ያደረገችው ሱማሌ ላንድ እንደ ሀገር ቆማ ራሷን ማስተዳደር ከጀመረች ከሰላሳ ዓመት በላይ ሆኗታል። ከተለያዩ ሀገራትም የውስጥ እውቅናን አግኝታለች ይህ ሁሉ ሲሆን፤ ምንም ሳይባል ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ወንጀል እና ነውር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችልበት ሁኔታ መኖር የለበትም።

ይህም ሆኖ የተጀመረውን ከግብ በማድረስ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለግብጻውያን በቀጥታ ከሕዳሴው ግድብ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በግብጽ በኩል እየተሰሩ ያሉ ሴራዎችን ለማክሸፍ በርካታ ስራዎች ይጠበቃሉ። ለምሳሌ ከሀይማኖት ተቋማት ጀምሮ የየትኛውም ሀይማኖት መሪ በበቂ ሁኔታ እየሠራ አይደለም ለማለት እችላለሁ። ከግብጽ እንቅስቃሴ አኳያ እዚህ ግባ የሚባል ትልልቅ ሥራ እየተሠራ አይደለም።

በተለይ በሚድያ ዘመቻ ረገድ ምንም እየተሰራ አይደለም ለማለት ያስደፍራል። የሀገር ውስጥ ሚድያዎች በሙሉ የግልም የመንግስትም ትኩረታቸው ሁሉ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ነው። በአንጻሩ ግብጾች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የአረቡን ዓለም ሚድያ ሁሉ ተቆጣጥረው እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት እየተጠቀሙበት ይገኛል። በኢትዮጵያ በኩል ይኸው ሊደረግ ይገባል። ይህ የሀገር የትውልድ ጉዳይ ነው ይላሉ።

በውጨው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የሚጠበቅባቸው በርካታ ስራ አለ። አስር ሚሊየን የሚደርሱ ግብጻውያን ከሀገራቸው ውጪ በስደት እንደሚኖሩ ይገመታል። ስምንት መቶ ሺ የሚደርሱ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኤክስፐርቶች አሏቸው። እነሱ በሁሉ በየሚዲያው በተለይ በአረብኛ በሚተላለፉት ላይ በዚህ ጉዳይ በንቃት ይሳተፋሉ። የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የአንድ አካባቢ ጥያቄ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ነው። ዲፕሎማቶችም አረብኛ ቋንቋ የሚችሉ የአካባቢውን ባህሉን የሚያውቁ መመደብ አለባቸው። በመንግስት በኩልም ለብዙሀኑ ተደራሽ አንዲሆን የፓናል ውይይቶችን ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ስራዎች የሚጠበቁ ይሆናል።

የቀድሞ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም የሕዳሴን ግድብ በተመለከተ የተናገሩትን እናስታውሳለን። አሁን ደግሞ በምርጫ እየተወዳደሩ ነው ቢያሸንፉ አጠቃላይ በኢትዮጵያና በግብጽ ግንኙነት ላይ የሚኖራቸው አቋም ምን ይሆናል የሚለውም መታየት አለበት። ለዚህ ደግሞ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብዙ ይጠበቃል።

በእርግጥ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እስካሁን ድረስ ትኩረት ያደረጉት በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ያኮረፉ አካላትም ቢሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ነገር መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ያም ሆነ ይህ የውስጥ ሰላም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከተቻለ የባሕር በር ጥያቄው ዛሬም ባይሆን ነገ ምላሽ ማግኘቱ አይቀሬ ነው።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You