የቀይ ባሕር ቀጣና እና የኢትዮጵያ ሚና

የስህበት ማዕከል የሆነው የቀይ ባሕር ቀጣና ቀድሞም ቢሆን የየአገራቱን ትኩረት ሲስብ የነበረና አሁንም ድረስ እየሳበ ያለ አካባቢ ነው። አቅም በፈቀደ መጠን ቀጣናውን ለመቆጣጠር የማይተኙ አገራት በርካታ ናቸው። ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለቤት የሆነችውና የቀይ ባሕር ባለይዞታ መሆኗ የሚነገርላት ኢትዮጵያም ወደዚህ ቀጣና ለመቀላቀል የባሕር በር ሊያስገኝላት የሚያስችላትን የስምምነት ፊርማ ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር በማኖር አንድ ብላ መጀመሯ የሚታወቅ ነው።

የባሕር በር ለማግኘት የሚደረገው እንቅስቃሴ ብዙዎች እንደሚያስቡት ሸቀጥ ማጓጓዣ ብቻ አይደለም፤ ሕልውና ማስጠበቂያም ጭምር እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል። ከሌሎች አገራት ጋርም ሊያስተካክል የሚችል እንደሆነም የሚነገር ነው። ይህ ኢትዮጵያ ልታገኘው ፊርማዋን ያኖረችለት በቀይ ባሕር ቀጣና ያለው አካባቢ እንዴት ይገለጻል? የቀጣናው የትኩረት ማዕከልነቱ እንዴት ይታያል? ስንል ምሁራንን ጠይቀናል።

ካነጋገርናቸው ምሁራን አንዱ የታሪክ ምሁሩ አቶ ዳኛው ገብሩ ናቸው፤ እርሳቸው ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይም ሆነ በቀይ ባሕርም ተሳትፎ የነበራትና ያላት አገር ናት ሲሉ የዓባይ ወንዝን ጨምረው ይጠቅሳሉ። የሁለቱም የትኩረት አቅጣጫዎች በዋናነት የሚያርፈው ኢትዮጵያ ውስጥ ነውም ይላሉ። የቀይ ባሕርም ሆነ የዓባይ ጉዳይ የችግር መነሻውን የሚያደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርም የዓባይም ባለይዞታና ባለቤት በመሆኑዋ ነው ይላሉ።

እሱ ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹ አገሮች ጋር ኢትዮጵያ ስትነጻጸር ተጽዕኖ ልትፈጥር ትችላለች ተብሎ በሌላው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግምት የተሰጣት ናት ሲሉም ያክላሉ። ምናልባትም ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ያላት አገር ናት፤ ከዚህ የተነሳ ዓለም በትኩረት የሚመለከቷትና አልፎ አልፎ አንዳንዶቹም በስጋት የሚያይዋት እንደሆነችም ያመለክታሉ።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በቀይ ባሕር ላይ ምንም አይነት ሚና የላትም። የነበራትን ሚና ካጣች ቆይታለች ይላሉ። አንደኛ በአሰብ አካባቢ በርካታ ሀብት ነበረን። አሰብ ላይ ያለን ወደብ ብቻ አልነበረም፤ የነዳጅ ማጣሪም ጭምር ነበር። ከዚህ ሌላ በጣም ጠንካራ የነበረ የባሕር ኃይልም ነበረን ሲሉ ቁጭታቸውን ይናገራሉ።

በእርግጥ ቀደም ሲል ይላሉ ጥላሁን (ዶ/ር)፣ በቀይ ባሕር አካባቢ ኢትዮጵያ የነበራት ተጽዕኖ ከፍተኛ ነበር። ያንን ተጽዕኖ ይዛ ቆይታ ቢሆን ዛሬ ላይ የት በደረሰች ነበር? የገነባነው ጠንካራ የባሕር ኃይል ነበርና በሱማሊያ አካባቢ የሚታየው የባሕር ላይ ውንብድና ባልኖረም ነበር። ይሁንና አሁንም ቢሆን ተስፋ የሚቆረጥበት አይደለም። በቀጣይ ተጽዕኖ ይኖረናል የሚል እምነት አለኝ። እኔ ተስፋ አልቆርጥም። ይህ ግን የሚወሰነው የኢትዮጵያ መንግስት ሕዝቡን የሚይዝበት አያያዝና ሕዝቡ ለሰላም ቁርጠኛ መሆን ሲችል ነው።

አቶ ዳኛው ገብሩ አክለውም ውሃ የዓለም ፖለቲካ ቁጥር አንድ አጀንዳ ነው የሚሉት የታሪክ ምሁሩ፣ ውሃ ከነዳጅም ከወርቅም የሚበልጥ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማያዊ ወርቅ ነው ተብሎ እንደሚነገር ይገልጻሉ። እንደ እርሳቸው አባባል፤ ሌሎቹ ሀብቶች በሌላ ሊተኩ ይችላሉ። ውሃ ግን የማይተካ ሀብት ነው። ምናልባትም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሶስተኛው የዓለም ጦርነት የሚነሳ ከሆነ መነሻው ውሃ ነው ብለው ብዙዎቹ ምሁራን በስጋትነት እንደሚተነብዩ ይናጋራሉ። ምክንያቱ ደግሞ የዓለም ሕዝብ በውሃ ጥማት ውስጥ መኖሩ ነው።

እንደሚታወቀው ከዓለም ክፍል 71 በመቶ የሚሆነው ውሃ ነው። ከዚህ ውስጥ በቀጥታ ጥቅም ላይ መዋል የሚችለው የውሃ መጠን ሶስት ነጥብ አምስት በመቶው ብቻ ነው። 96 ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆነው ውሃ በቀጥታ ለአገልግሎት የማይውል ውሃ ነው። ውሃው እንኳ ቢኖር ለጥቅም ማዋል የሚቻለው በከፍተኛ ወጪ ነው።

ታዲያ ይላሉ አቶ ዳኛው፣ ዓለም የሚሻኮተው ሶስት ነጥብ አምስት በመቶው ውሃ ላይ ነው። ከሶስት ነጥብ አምስት በመቶ ከሚሆነው ውሃ ውስጥ ደግሞ 61 በመቶ የሚሆነው ውሃ የሚገኘው ሰው በማይኖርበት በአርክቲክና በአንታርክቲክ አካባቢ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ዓለም የሚራኮተው ከአንድ ነጥብ አምስት በመቶ ያልበለጠ ድርሻ ባላቸው በኢትዮጵ ውስጥ እንደሚገኙ አይነት አገር አቋራጭ ወንዞች ላይ እንደሆነ ይናገራሉ።

እንደ ታሪክ ምሁሩ ገለጻ፤ ዓለም፣ በውሃ አስተዳደር፣ አጠቃቀምና አያያዝ ላይ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ውስጥ ነው። በዚህ ምክንያት ደግሞ አገሮች ይጣላሉ፤ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ አገሮች የሚዋጉት በውሃ ምክንያት ነው። ብዙ አገሮች የሰላም እጦታቸው እና የችግር መነሻቸው ውሃ ነው። ምናልባትም ወደፊት የውሃ እጥረቱ በርካታውን የዓለም ሕዝብ ወደ እልቂት ውስጥ ያስገባዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ስለዚህ የውሃ ፖለቲካ በዓለም ላይ ትልቅ አጀንዳ ነው ሲሉ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያም ያለችው በዚሁ የውሃ ፖለቲካ ውስጥ ነው ይላሉ። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን ስንመለከት በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ማዕከል የሆነች አገር ናት። የመጀመሪያ የኢትዮጵያን የውጭና የአገር ውስጥ ፖለቲካ ሲወስን የቆየው የዓባይ እና የቀይ ባሕር ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ ባሳለፈችባቸው በውጭ ፖሊሲ፣ የውጭ ግንኙነት፣ የውስጥ ችግሯና ግጭቷ አባባሽና መነሻው የዓባይና የቀይ ባሕር ጉዳይ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ እነዚህን ሀብቶቿን በብዛት ሳትጠቀም የዘለቀች፤ በተለይም ዓባይን ሳትጠቀምበት የቆየችበት ውሃ ሲሆን፣ እስካሁንም ድረስ ጠላት ሲጠራብን እዚህ ደርሷል። በእርግጥ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለመጠቀም አቅም አልነበረንም የሚሉት አቶ ዳኛው፣ ሲደረግ የነበረውም ሙከራ ጥቂት ነበር ብለዋል።

የታሪክ ምሁሩ አቶ ዳኛው፣ ሌላኛው ጉዳይ ቀይ ባሕር ነው ይላሉ። ቀይ ባሕር ጥንትም ቢሆን የተወሰነው ክፍል የኢትዮጵያ ይዞታ እንደነበር ይታወቃል። ምንም እንኳ ሰዎች የወደብን ጉዳይ ከሸቀጥ ጋር ቢያመሳስሉትም ቀይ ባሕርን ያጣነው አለአግባብ ነው፤ እኛን ጨምሮ ዓለም በቀይ ባሕር ላይ ያለው ፍላጎት የወደብ ብቻ አይደለም፤ የሕልውናም ጉዳይ ጭምር ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የባሕር በር ትፈልጋለች ሲባል የወደብ ጉዳይ ብቻ ሆኖ አይደለም። እንደ አገር ሕልውናዋን ጭምር ለማስጠበቅ በማሰብ ነው። ስለዚህ የቀይ ባሕር ጉዳይ የወደብ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ መረዳቱ የግድ ነው። ቀይ ባሕር የዓለምን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ሊፈጥር ወይም ደግሞ ሰላማዊ ሊያደርግ የሚችል ወሳኝ የሆነ ቀጣና ነው።

ኢትዮጵያ ይህን ባሕር በስህተት አጥታው ቆይታለች። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ቀይ ባሕርን እንደሌሎቹ ቀጣናውን ፈላጊ አገራት መጋፈጥ ያስፈልጋል። ይህን የምናደርገው ደግሞ ለአገራችን ሰላም ሲባል ነው። ቀይ ባሕርን ስናስተውል በርካታ ጸጋዎች ያሉት ነው። በተለይም ሸቀጦችን እና ጥሬ ሀብቶችን ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ቦታ ለማጓጓዝ ርካሽ የሚባለው የውሃ ላይ ትራንስፖርት ነው። የዓለም ሸቀጥና ጥሬ ሀብት በውሃ ላይ መጓጓዝ ካለበት ደግሞ ዋናው ማዕከሉ ቀይ ባሕር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ቀጣናው ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዓለም ሕዝብ የሚኖርበት ይህ ቀጣና፣ ከፍተኛ የሸቀጥ ዝውውር የሚካሔድበትና በተለይም የአፍሪካ ሰፊ ጥሬ ሀብት የሚገኝበትም ነው የሚሉት አቶ ዳኛው፣ ሰፊ ገበያም ያለው መሆኑን ያስረዳሉ። በንግዱ ስራ አትራፊ መሆን የሚቻለውም ዓለም በዚህ በቀይ ባሕር ላይ ሲጓጓዝ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ቀይ ባሕር አሁን ያለው በችግር ውስጥ ሲሉ ይናገራሉ።

ዶክተር ጥላሁን እንደሚሉት በዙሪያችን ያለው ወደብ በሙሉ ማለት ይቻላል በአረብ ሊግ አባል አገራት የተያዘ ነው። ኤርትራም ተለዋጭ የአረብ ሊግ አባል መሆኗ ሊረሳ አይገባም። ስለዚህ የራሳችን ወደብ የሚያስፈልገን መሆኑ የግድ ነው ይላሉ። የምንጠቀምበት የጅቡቲ ወደብ እንደመሆኑ የቀይ ባሕር ቀጣና ካለበት ከፍተኛ ትኩረት የተነሳ በጊዜ ሒደት ጅቡቲ ተጽዕኖ ውስጥ ልትገባ ትችላለች።

ሱማሊያም ብትሆን የፈረሰች አገር ከመሆኗ በተጨማሪ አልሸባብም እያስቸገረ ነው። ሌላውም ወደብ የራሱ ተጽዕኖ ያለበት ከመሆኑ በተጨማሪ የቀድሞ ቅኝ ገዥዎች የእጅ አዙር ተጽዕኖ ያለበት ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ስለዚህ እኛ ወደብ እንድናገኝ ማድረግ ያለብንን ሁሉ በእቅድ በመያዝ ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ አለብን። በአሁኑ ወቅት ግን እኛ በቀይ ባሕር ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ መፍጠር አንችልም ብለዋል።

የታሪክ ምሁሩ አቶ ዳኛው እንደሚገልጹት ከሆነ ደግሞ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቀይ ባሕር የተሰጠው ትኩረት በሶስት መንገድ የሚፈረጅ ነው ይላሉ። የመጀመሪያዎቹ በቀይ ባሕር ጉዳይ ሃያ አራት ሰዓት የማያንቀላፉ አገራት ናቸው፤ ሁለተኞቹ ደግሞ ሃያ አራት ሰዓት የሚያንቀላፉ ሲሆኑ፣ ሶስተኞቹ ደግሞ በቀይ ባሕር ዙሪያ ችግር ጠንሳሾች ናቸው። ይህንን ሲያብራሩ እንደሚሉት፤ አንደኛ ሃያ አራት ሰዓት ከቀጣናው አይናቸውን ለአፍታ የማያነሱ አገራት ሲስተዋሉ ሁሉም በሚያስብል ደረጃ ተረባርበው በቀይ ባሕር አካባቢ ከጅቡቲ እስከ ሱማሊያ ድረስ ወደብና የጦር ሰፈር እየተከራዩ ተቀምጠዋል።

ይህ ሲጤን ወደብ ፍለጋ አይደለም። ለፖለቲካዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለወታደራዊ አቅም ስትራቴጂክ ቦታ የመፈለግና የመያዝ ጉዳይ ጭምር ነው። ምክንያቱ ደግሞ ቀይ ባሕር ላይ በመራኮት ላይ ያሉ አገሮች ወደብ ሞልቶ የተረፋቸው ናቸው። እነዚህ የማያንቀላፉ አገሮች የአፍሪካንና የኢስያን ኢኮኖሚ ሊቀራመቱ፣ ሰፊ የሆነውን የሰው ጉልበት ሊበዘብዙና ገበያውን ሊጠቀሙ የሚችሉ አገሮች ሲሆኑ ለአፍታ እንኳ የማያሸልቡ ናቸው።

የታሪክ ምሁሩ በሁለተኛ ደረጃ የፈረጁት ደግሞ ሃያ አራት ሰዓት የሚተኙቱን ሲሆን፣ እነርሱም የአካባቢው አገሮች ናቸው ብለዋል። ለአብነትም ሲጠቅሱ ሱዳን፣ ሱማሊያ፣ የመንም ጭምር እንደሆኑ ገልጸው እነርሱም እንቅልፋሞች ናቸው ሲሉ ይገልጿዋቸዋል። እነዚህ የአካባቢው አገራት እንቅልፋሞች ባይሆኑ ኖሮ፤ በተናጠል ጥቅማቸውን ማስከበር ባይችሉም፤ ሕብረት በመፍጠር ጥቅማቸውን ያስከብሩ እንደነበር አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለችው ኅብረት እንፍጠር ነው። ሰጥቶ በመቀበል መርህ አንድነታችንን በማጠናከር ጥቅማችንን እናስከብር ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ስትል የተለያዩ አገሮች የሚያይዋት በስጋት ነው። የአካባቢው አገራት ቀድሞም ቢሆን ደካማ ናቸው። በተናጠል መራመዳቸው ደግሞ የሌሎቹ ሃያ አራት ሰዓት የማይተኙ አገሮች መረማመጃ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ እየሆነ ያለና ወደፊትም አይቀሬ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ዳኛው አገላለጽ፤ በሶስተኛው ላይ የሚፈረጁት ደግሞ በቀጣናው ችግር የሚጠምቁ አካላት ናቸው። በአካባቢው ድሮን ጭምር በመጠቀም ዓለምን የሚያስቸግሩ፤ ቀጣናውንም የሚያምሱ አካላት አሉ። ከዚህ የተነሳ ቀይ ባሕር ወንበዴዎች የሚፈነጩበት ቀጣና ነው። ከዚህ የተነሳ አካባቢው የተጨናነቀ ነው።

የመን የፈረሰች አገር ናት፤ በተመሳሳይ ሶማሊያም እንደዚያው ናት። ሱዳንም በትርምስ ውስጥ የምትገኝ ያልተረጋጋች አገር ናት። ከዚህ በተጨማሪ ቀይ ባሕርን ስናነሳ የአረብና የእስራኤል ግጭት ያለበት አካባቢ ነው። ሁለቱ ደግሞ የበረታ አለመግባባት የሚስተዋልባቸው ናቸው።

አቶ ዳኛው፣ በዚህ በችግር ውስጥ ባለ ቀጣና የሚገኙ ሀገራት የሕልውና ስጋት አለባቸው ይላሉ። ስለዚህ እኛም ሸቀጦቻችንና ጥሬ ሀብቶቻችን በሰላም በባሕሩ ላይ እንዲተላለፉ ባለቤት በመሆን ጥቅማችን ማስከበር መቻል እንዳለብን ይገልጻሉ። ሁለተኛው ደግሞ የትኛውም አገር እኛን እንዳይተነኩሰን የራሳችንን ኃይል ቀይ ባሕር ላይ መፍጠር መቻል ይጠበቅብናል ሲሉ ያመለክታሉ።

ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ቀይ ባሕር ከወደብ በዘለለ የኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ መሆኑ ነው፤ በመሆኑም ቀይ ባሕር ላይ መውጫ ኮሪደር ያስፈልገናል በሚል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የወሰዱት ወሳኝ አቋም የእኔም ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ ትክክለኛ ነገር ነው።

እኛ የቀይ ባሕር ባለቤቶች ነን፤ ስለሆነም የተወሰደብንም ቀይ ባሕር ይዞታ መመለስ አለበት፤ ጥያቄ ስናነሳ መላ ኢትዮጵያዊ ሊተባበረን ይገባል፤ ምክንያቱም ቀይ ባሕር ላይ ድርሻ የማይኖረን ከሆነ ዘለቄታ ያለው ሕልውና ሊኖር አይችልም ብለዋል።

አዲስ ዘመን ህዳር 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You