አገር እንደ አገር የሉዓላዊነቷ ከፍታ የሚገለጠው፤ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ያለ ልዩነት የደህንነት ስጋቱ ተወግዶ የተረጋጋ ሰላምን የሚያጣጥመው የሁሉም ሆኖ ለሁሉም በመቆም ዋጋ በሚከፍል የአገር መከላከያ ኃይል ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ ጠንካራ፣ አስተማማኝ እና ከሁሉም ለሁሉም የሆነ የመከላከያ ኃይል እና የደህንነት ተቋም መኖር፤ ለአገርም ሁለንተናዊ ክብርና ከፍታ ዋልታ፤ ለሕዝብም የሰላምና ደህንነት አለኝታነቱ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንምና ነው፡፡
በዚህ ረገድ አንቱታን ያተረፉ አገራት አሉ፡፡ ያኔ ዓለም እንዲህ በቴክኖሎጂና በተራቀቁ የኃይል ሚዛን ማስጠበቂያ የጦር ቴክኖሎጂዎች ባለቤት ባልሆነችበት ዘመን፤ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ከኋላ ሆና በጦር ኃይሏ ግን ከፊት ቀድማ ደማቅ ገድልን የጻፈች አገር ናት፡፡ የጥንቱ ቀርቶ የመካከለኛውና የቅርቦቹ አገራዊ ዓለም አቀፍ ገድሎቿ፤ እንዲሁም የውስጥ ሰላምና አንድነትን ያስጠበቁ ተግባሮቿ የጠንካራ ማዕከላዊ ኃይል ባለቤትነቷ ሕያው ምስክር ናቸው፡፡
ዛሬም ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮችና ፈተናዎች እየተፈተነች ያለች ቢሆንም፤ እነዚህን ችግሮቿን በመሻገር ሂደት ውስጥ የመከላከያ እና ደህንነት ተቋማቷ ተኪ የሌለው ሚናቸውን በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡ ፡ በዚህ ሂደት ግን ለእነዚህ ተቋማት አጋዥ የሆኑ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች የመኖራቸውን ያህል፤ እነዚህ አደረጃጀቶች ደግሞ በሂደት አቅም እየፈጠሩና እየጠነከሩ በሄዱ ቁጥር ለአገር ሳይሆን ለክልል፤ ለሕዝብ ሳይሆን ለቡድን መጠቀሚያ በመሆን አገርንና ሕዝብን የሕልውና አደጋ ውስጥ ሲጨምሩ ታይቷል፡፡
ከዚህ መለስ ባሉ የሕዝብ ሰላምን በማደፍረስ፤ የዜጎችን የመዘዋወር፣ ሰርቶ ሃብት የማፍራትና በሕይወት የመኖር መብትን ጭምር አደጋ ላይ ሲጥሉም ተስተውሏል፡፡ እነዚህ አደጋዎች ለአገር ሉዓላዊነት አደጋ፤ ለዜጎችም ሰላምና ደህንነት ስጋት ከሆኑ ውለው አድረዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ለአገርም ሆነ ለዜጎች ፈተና የሆኑ ችግሮችን ከማስቀረት አኳያ እንደ መንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ሲሆን፤ በተለይ በእነዚህ አደረጃጀቶች ምክንያት በአገር እና ሕዝብ ላይ ከተደቀነው አደጋ መቀልበስ እና ሰላምን መመለስ በተቻለ ማግስት፤ የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀቶች ያላቸውን አቅምና ልምድ ለጥፋት ሳይሆን ለላቀ አገራዊ አቅም እንዲያውሉ በሚያስችል መልኩ መልሶ የማደራጀት ተግባር ውስጥ ተገብቷል፡፡
ከእነዚህ መካከል አንዱ ልዩ ኃይሎች ከፍ ላለ አገራዊ ኃላፊነት እድል ያገኙበትን የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል የመሆን ሂደት ሲሆን፤ የፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም የክልል መደበኛ ፖሊስን ተቀላቅሎ ለላቀ ኃላፊነት መሰማራትንም ይጨምራል፡፡ ይሄንን አልሻም ያሉም በሲቪል መደበኛ ሕይወት ውስጥ ገብተው የሚኖሩበት እድል ተመቻችቷል፡፡ እነዚህ ልዩ ኃይሎች በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ እንዲቀላቀሉ የተሰጠው እድል ደግሞ አገር እንደ አገር ከፍ ያለ አቅም ያለው አንድነቱ የጸና የመከላከያ እና የደህንነት ኃይል ለመፍጠር እድል የሚሰጥ ሲሆን፤ ይሄንን እድል ለመጠቀም የወሰኑ የክልል ልዩ ኃይሎችም ተግባራቸው ሊመሰገንና ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡
ምክንያቱም የክልል ልዩ ኃይልነት ከአንድ አካባቢና ክልል የዘለለ አገራዊ ሕልምና ኃላፊነትን የሚነጥቅ ነው፡፡ በአንጻሩ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባል መሆን ከአገር አልፎ ዓለማቀፍ ኃላፊነትን የመሸከም የገዘፈ ታላቅ ጥሪ ነው፡፡ ይሄ መጠራት ደግሞ ከሁሉም ለሁሉም የሆነ ኃይልን የመገንባት፤ የአገርን ሉኣላዊነትና ግዛት የማስከበር፣ ሕዝብንም የሰላምና ደህንነት ስሜት እንዲጎናጸፍ የማስቻል፤ ዓለምአቀፍ ተልዕኮንም ለመቀበል መጠራት ነው፡፡
በዚህ ረገድ ጥሪውን ተቀብሎና የመንግስትን ዓላማ ተረድቶ አዎንታዊ ምላሽ የሰጠው የልዩ ኃይል ብቻ ሳይሆን፤ መላው ሕዝብና ሌላውም ባለድርሻ የመልሶ ማደራጀቱን ዓላማ እና ግብ ተረድቶ መሰል አዎንታዊ ድጋፉን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ለአገር ክብርና ሉዓላዊነት፤ ለሕዝብም አብሮነት፣ ሰላምና ደህንነት የተበታተነ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ሳይሆን ጠንካራ እና አገራዊ የጸጥታ ኃይል እውን ማድረግ የግድ ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና ያለው ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት እንደመሆኑ፤ የአገር እና ሕዝብ የደህንነት ምንጭ የሆነውን መከላከያ ኃይል በማጠናከር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2015