አዳሪ ትምህርት ቤቶች ልዩ ችሎታና ተሰጥዖ ያላቸውን ተማሪዎች በመለየት ልዩ ድጋፍ በማድረግ ይታወቃሉ። እንደ አፍሪካ ባሉ አገራት ግን አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚፈለገውን ያህል ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ይነገራል። በኢትዮጵያም ቀድሞ ለአዳሪ ትምህርት ቤቶች ይሰጥ የነበረው ትኩረት አሁን ላይ እየተሰጠው ነው ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም።
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አኳያ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ግን ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል። ለዚህም ማሳያም የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የፈተና ውጤት ነው።በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ፈተና አዳሪ ትምህርት ቤቶች አነሰ ቢባል 90 በመቶ ተማሪዎቻቸውን ለከፍተኛ ትምህርት ማብቃታቸው ይታወሳል። ከነዚሁ ትምህርት ቤቶች ከ50 በመቶ በላይ ያመጡም በርካቶች ናቸው።እነዚህ የዛሬ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመጪዎቹ ዘመናት በማናቸውም መስኮች ሀገርን በብቃት ፊት አውራሪ ሆነው ያገለግላሉ ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸዋል።
እነዚህ ትምህርት ቤቶች ከእውቀት ማዕዳቸው ውስጥ ለተማሪዎች ምርጡን መስጠት የሚያስችል አቅም ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ተማሪዎች ንቃተ ሕሊናቸውን እንዲያዳብሩ፣ የመወዳደር ፍላጎትን ባሕል የሚያደርጉም ናቸው።ትምህርት ቤቶቹ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ተግባራዊ የሚደረጉባቸው፤ ወደ ነፃነት ልምምድ ውስጥ የሚገቡባቸው የእውቀት ደብሮች ስለሆኑ በሁሉም የተመረጡ ናቸው።
ትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎች የነፃነት ስሜትን እንዲያገኙ፣ አዲስ ጓደኝነትን እንዲፈጥሩና በዙሪያቸው ካሉት ጋር ማኅበራዊነትን እንዲመሠርቱ ዕድል የሚሰጡ ናቸው።
አዳሪ ትምህርት ቤቶች ሌላ ቦታ የማይገኙ የትምህርት እድሎችን የሚሰጡም ናቸው።ተማሪዎች በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ተግባርን እንዲከውኑም ያበረታታሉ።እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች ያሏቸው በመሆናቸውም እንደሀገር አሁን ላይ ካሉት በተጨማሪ 50 ዘመናዊ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታስቧል።የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፤ እነዚህን ትምህርት ቤቶች መገንባት እንደሀገር በርካታ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል።በመሆኑም የግንባታ ፕሮጀክት ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።ዘመኑን የጠበቀ ሥራ ለማከናወን በማሰብም ከዲዛይን ዝግጅት ጀምሮ የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ተሳትፎበታል።
በኢትዮጵያ 48ሺህ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም 98 በመቶው ከደረጃ በታች እንደሆኑ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ደረጃቸውን የጠበቁ የአካልና የአዕምሮ ማበልጸጊያ ትምህርት ቤቶች ያስፈልጓታል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የማበልፀጊያ ማዕከል መወሰድ ይኖርባቸዋል።ያሉትን ማሳደጉ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ በአዲስ መልኩ ዘመናዊ የሆኑ አዳዲስ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ሥራ በሀገር አቀፍ ደረጃ እቅድ ቢያዝም በክልል ደረጃም መሠራት እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል።በዚህም በርካቶች ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ ነው።ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የልማት ማኅበራት ሚና አስፈላጊ ነው። መንግሥት ብቻ ሥራውን መውሰድ የለበትም።
በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ላይ የልማት ማኅበራት ባለመኖራቸው ይህንን ማድረግ አልተቻለም።ስለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነቱን ወስዶ መሥራት እንደሚኖርበት ይጠበቃል።በዚህም ነባር ትምህርት ቤቶችን ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በመቀየር፣ ተማሪዎችን በጾታ ከፍሎና እስከ 62 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እንዲሠራ ሆኗል፡፡
ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የወንዶች አዳሪ ትምህርት “ገላን ልዩ የወንዶች ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት” ነው። ትምህርት ቤቱ የተመሠረተው ከዛሬ አራት ዓመት በፊት በ2012 ዓ.ም ነው።
አዳሪ ትምህርት ቤቱን በርዕሰ መምህርነት የሚያገለግሉ አቶ ካሳሁን መርጋ እንደሚናገሩት፤ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው እንደ ሀገር ጥቅም አለው።አንዱና ዋነኛው ጥቅም ደግሞ የነገ ሀገር አስቀጣይ ትውልዶችን በብቃት ማፍራት ነው።ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታየ የመጣው የትምህርት ጥራት ጉዳይ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ብቻ የሚቀጥል ከሆነ ብዙ ነገር ያሳጣናል።እናም አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ልምድ መቀመሪያ ማድረግ መቻል ብዙ ነገሮችን ይለውጣል።
መንግሥት ከትምህርት ሽፋንና ተደራሽነት አንጻር እስከዛሬ ብዙ ሠርቷል።ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ገብተዋል።ሆኖም የጥራቱ ነገር አሁንም አንገብጋቢ ነው።እናም ትኩረቱን ወደዚህ በማዞር የተለያዩ መንገዶችን እየተከተለ የሚገኝ ሲሆን፤ አንዱም አቅም እያላቸው የተሻለ የትምህርት ዕድል ላላገኙ ተማሪዎች ዕድል በመስጠት፤ በመንግሥት ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎችን በተለየ አቅማቸው መልምሎ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በማስገባትና ልዩ ድጋፍ በማድረግ ማብቃት ነው።
የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የተመረጡ መምህራን ሳይቀር ይቀጠራሉ።የገላን ልዩ የወንዶች ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት መምህራንም በዚህ መልክ የመጡ ናቸው።በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ፈተና ውስጥ አልፈው የተማሪዎችን አቅም እየገነቡም ይገኛሉ።እየወረደ ያለውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ካሉት አማራጮች መካከል አንዱ ይህ እንደሆነ አያጠያይቅም የሚሉት አቶ ካሳሁን፤ አቅሙ ኖሯቸው የሚያግዛቸው ቤተሰብ የሌላቸውን ልጆች ከማስተማርና የነገ ተስፋዎች እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ እነዚህን የመሰሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው።በተጨማሪም ትምህርት ቤቶቹ የማቋረጥ ምጣኔን ከመቀነስ፤ ልዩ ተሰጥዖን ከማውጣት፤ አዳዲስ ነገሮችን ለሀገር ከማበርከት አኳያ የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል።
የገላን አዳሪ ትምህርት ቤት በዚህ አይነት መልኩ መደራጀቱና ድጋፍ እየተደረገለት መቀጠሉ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ምንም ተማሪ ሳይወድቅ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማስገባት ችሏል።በተጨማሪም ተማሪዎች የውጪ እድል አግኝተው የነገ ተስፋቸውን እንዲያለመልሙ አግዟል።አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከሌሎች ለየት የሚያደርገው በርካታ መለያዎች ያሉት እንደሆነ የሚያነሱት ርዕሰ መምህሩ፤ አንዱ የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት መሆኑን ይጠቅሳሉ።እንደ ሀገርም ብቸኛ መሆኑን ያብራራሉ።
ትምህርት ቤቱ በአደረጃጀቱም ልዩ ነው።ለምሳሌ፡- በዋና ርዕሰ መምህር ብቻ ሳይሆን በሦስት ምክትል ርዕሰ መምህራን ጭምር የሚመራ ሲሆን፣ ሌሎች ጋር ያሉት ምክትል ርዕሰ መምህራን እንደሚሠሩት አይነት ሥራም አይደለም የሚሠሩት።ልክ እንደ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉም የሚመሩት ዘርፍ አላቸው። የተማሪዎች አገልግሎት፣ ፋይናንስና አስተዳደር እንዲሁም አካዳሚክ ዘርፍ በሚል የተከፋፈሉ ሚናዎች አላቸው።
ትምህርት ቤቱ “ዜሮ ክላስ” የሚባል ትምህርት አለው።ክፍል መግባት ከመጀመሩ በፊት የሚሰጥ የትምህርት አይነት ነው።በዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑት ደግሞ 12ኛ ክፍልና የተወሰኑት 11ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው።በተጨማሪም ከመደበኛው ክፍለ ጊዜ ውጪ፣ ከሰዓት በኋላም ሁለት ክፍለ ጊዜ የትምህርት መስጪያ ተደርጎ ይሠራል።የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና ብቁ እንዲሆኑ መምህራን በራሳቸው ተነሳሽነት የብቃት መለኪያ ጥያቄዎችን ያዘጋጃሉ። ይህም ዘወትር ቅዳሜ የሚከናወን ነው።ተማሪዎች በሌሎች ዓለማት ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑም በትምህርት ቤቱ ፈረንሳይኛና አረብኛ ትምህርትም ይሰጣል።
ገላን ትምህርት ቤትን ከሌላው የሚለየው እንደ ትምህርት ቤት ቅዳሜ ሙሉ ቀን የሥራ ቀን አድርጎ መሥራቱ ነው።በአቅም ደከም ያሉትን ተቀብሎም ያስተምራል።ይህ ማለት እንደ ሌሎቹ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ያመጡትን ብቻ አይደለም ማለት ነው። የመቀበል አቅሙ እስኪሞላ ድረስ መጠነኛ ውጤት ያመጡትንም ያስተናግዳል።ምክንያቱም ለብዙዎች እድል መስጠት የሚቻለውና የትምህርት ቤቱ ብቃት የሚለካው ደከም ያሉትንም መያዝና ማብቃት ሲቻል ነው ብሎ ያምናል።በዚህም ከመምህራን እስከ አስተዳደር ሠራተኞች ድረስ ዋጋ እየከፈሉ ተማሪዎችን ያግዛሉ፤ ያበቃሉም።
እንደ ሀገርም ይሁን እንደ ከተማ አስተዳደር በመንግሥት የሚደገፍ ትምህርት ተቋም ቢኖር አንደኛው ይህ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው።በዚህም እንደ ሌሎች ተቋማት በዓመት የሚከፍለውን አሠራር ዘርግቶ ያከናውናል።ከእነዚህ መካከል ለተማሪዎች የሚሰጠው የዱቤ ሕክምና አገልግሎት አንዱ ነው።
ትምህርት ቤቱ የመቀበል አቅሙ 500 ተማሪ ሲሆን፤ በየዓመቱ ደግሞ ዘጠነኛ ክፍል የሚገቡ 100 ተማሪዎችን ይመለምላል።ለየት የሚያደርገውም አንድ መሠረታዊ ነገር ይህ ነው።በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከትምህርት ቢሮ በወረደለት አቅጣጫ መሠረት በአዲስ አበባ ያሉትን ትምህርት ቤቶች (የግሎችን ጨምሮ) በሙሉ በማወዳደር ተቀብሏል።ቁጥራቸው ደግሞ ከተቀበላቸው 100 ተማሪዎች ውስጥ 20 ተማሪዎች የግል ናቸው።ይህ መሆኑም የግልና የመንግሥቱ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ልምድ ይቀሳሰማሉ በሚል ታስቦበት መሆኑን አቶ ካሳሁን ይናገራሉ፡፡
አቶ ካሳሁን እንደሚናገሩት፣ በገላን አዳሪ ትምህርት ቤት ለተማሪዎች ፈተና ከመቶ ከ70 በታች ማምጣት የተከለከለ ነው።ነገር ግን በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ይህንን ውጤት ያመጡ ካሉ ተለይተው እንዲታገዙ ይደረጋሉ።ለዚህም አንድ መምህር 13 ተማሪዎች ተመድቦለት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያማክራል።በዚሁ መሰረትም፣ በቅርቡ 34 ተማሪዎች ተለይተው የማብቃት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የአዳሪ ትምህርት ቤት መኖር በርካታ ነገሮችን የሚቀይር እንደሆነ የሚናገሩት ርዕሰ መምህሩ፤ ተሞክሯቸውን ሲያጋሩ ተማሪዎች ከትምህርት በኋላ ባላቸው ሕይወት ሳይቀር የሚቀየሩበት ነው።ለምሳሌ በአመለካከት፣ በክህሎት፣ በእውቀትና ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆኑበት ነው።የትምህርት ስብራት የሆነውን መጠነ መድገም፣ ማቋረጥ የሚሉትን ሀሳቦች የሚቀንስም ነው።
በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በልዩ ክትትልና እንክብካቤ ያድጋሉ።አቅም ባለው መምህር ይታገዛሉ።ሙሉ የትምህርት ቤት መገልገያዎችን ሩቅ ሳይሄዱ በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ቤተመጻሕፍት፣ቤተ ሙከራ፣ ኮምፒውተሮችንና መምህራኖችን በቀላሉ የሚያገኙበት አጋጣሚ ለአብነት ይጠቀሳል። የመማሪያ አካባቢ ምቹነትም እንዲሁ እንደልባቸው የሚያገኙበትን እድል ይሰጣቸዋል።
ተማሪዎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው እኩዮቻቸው ጋር እንዲገናኙ ያስችሏቸዋልም።ይህ ደግሞ ተደጋግፎ በመሥራት የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያስችላቸዋል።በተጨማሪም አቅም የሌላቸው ልጆች የወላጆቻቸውን ችግር እያዩ እንዳይሰቃዩ የሚያደርግም ነው።ይህ ደግሞ ለተማሪዎች የባሕሪ ለውጥ እጅግ አስፈላጊ ሲሆን፤ ለወላጆችም ቢሆን እፎይታን ይሰጣል።
ተማሪዎች ለሕግና መመሪያ ተገዢ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋልም።ከፍተኛው ቦታ ላይ ተወዳድሮ የማሸነፍን ልምድ እንዲቀዳጁ መሰል ትምህርት ቤቶች ወሳኝ ናቸው። ከዚያ ባሻገር ጠንክሮ መሥራት፣ እውነት፣ ራስን መግዛት፣ ሰዓት አክባሪነት፣ መቻቻልን የመሳሰሉ ምርጥ ሰብዓዊ ባህሪያትን እና አመለካከትን ያዳብሩበታል።
አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በቡድን የመሥራት ባህልን የሚያዳብሩበት፤ ጥቅሙንም የሚረዱበት፣ እኩል ነፃነትን የሚተገብሩበት፣ ሥራዎችን ጀምሮ መጨረስን ባሕል የሚያደርጉበትም ነው።ባሕላዊ እውቀታቸውን የሚያዳብሩበት፣ መግባባትን የሚያመጡበት (የተግባቦት ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት)፣ ዓለም አቀፍ ጓደኝነትን የሚፈጥሩበት ልዩ ዕድል የሚሰጥም ነው።
እንደ ዋና ርዕሰ መምህሩ ገለፃ፣ አዳሪ ት/ቤት ከሁሉም በላይ እንደሀገር ተወስነው እንዳይቀመጡ የሚያስችል ነው።ለምሳሌ ኮርሶቹ የዓለም አቀፍ ተማሪን የማናገር፣ የማንበብ እና የመፃፍ ችሎታዎችን ያሻሽሉላቸዋል።በዚህ ደግሞ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ጭምር ሄደው መማር ይችላሉ።ውጤታማነታቸውም በዚያው ልክ ያድጋል።
የአካቶ ትምህርትን በተመለከተም ሁሉንም ጥቅሞች በአካቶ መማር ሲቻል የሚመጡና የበለጠ የሚዳብሩ እንደሚሆኑ ዋና ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል።በእርሳቸው እምነት ጊዜው የሚፈልገው የአካቶ ትምህርትን ነው የሚል ነው።ጥናቶችም የሚሉት አካታች ትምህርት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ነው።ስለሆነም ትምህርት ቢሮም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ ያስብበታል የሚል ተስፋ አላቸው።
በአካቶ መማር ብዙ ጥቅሞች አሉት።አንዱ በሕይወት ዘመናቸው ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ፈተና ከአሁኑ አውቀውት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያግዛል።ትዳር መሥርቶ ለመኖርም ብዙ ልምዶችን ያስቀስማል።መግባባት ባሕል እንዲሆን ያደርጋል።ማኅበራዊ መስተጋብርን ያጠናክራል።በተጨማሪም በአመለካከት የዳበሩና ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ይፈጥራል።ይህ ሲባል ግን ችግሮቹ መለየትና በሕግ መያዝ ይኖርባቸዋል።በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሲማሩ ምን ድረስ መቀራረብ እንዳለባቸውም መወሰን ያስፈልጋል ባይ ናቸው።
በተፈጥሮ ደካማ የሆነ ሰው የለም።በዚህም ልጆች ላይ የምንሠራው ሥራ ከልብ ከሆነ እንደሀገር ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚሉት አቶ ካሳሁን፤ ትምህርት ቤቱ የትንሽ ዓመታት ቆይታ ያለው ቢሆንም ብዙዎችን ቀይሯል፤ የተሻለ መንገድንም አሳይቷል።በተቻለ መጠን ስኬታማ የሚያደርገውን ተግባርም አከናውኗል።ያም ሆኖ የፈለግነው ላይ ደርሰናል ብለን አናስብም ይላሉ።‹‹ተቋማችን ተስፋ ያላቸው መጠነኛ ተግባራትን ቢፈፅምም ብዙ ነገሮች ግን ይጎሉታል።ጅምር ላይ ያለ ነው።ነገር ግን፣ ተማሪዎቻችን ተስፈኞች ናቸውና ለብዙ ስለሚታጩ ያንን ለማሳካት እንጥራለን›› ሲሉም ጉዟቸው ምን ያህል ሀላፊነት የተሞላው እንደሆነ አብራርተዋል።
የስኬት መለኪያው ዓመት ሳይሆን ሥራ እንደ መሆኑ መጠን የ“ገላን ልዩ የወንዶች ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት” ተሞክሮ ለብዙዎች ትምህርት ይሰጣልና ሌሎችም ቢከተሉት መልካም ይሆናል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም