እያንዳንዱ ዜጋ የራሱንም ሆነ ያለበትን ማኅበረሰብ ፤ ከዚያም ባለፈ የሀገሩን ሰላም የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት ። ይህ ኃላፊነቱ የሚመነጨው ዛሬዎቹን ጭምር ነገዎቹ በሰላም ላይ የቆሙና ያለ ሰላም የተሟላ ትርጉም የሌላቸው በመሆኑ ነው።
የራሱን ሰላም በአግባቡ መጠበቅ ያልቻለ ዜጋ ፤ለማኅበረሰቡም ሆነ ለሀገሩ የሰላም ምንጭ ሊሆን ይችላል ተብሎ አይታመንም ፤ ከዛ ይልቅ ለሚኖርበት ማኅበረሰብም ሆነ ሀገር የሰላም ጠንቅ ሊሆን የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ይህ ደግሞ በእለት ተእለት ሕይወታችን ተደጋግሞ የሚያጋጥመንና አብዝተን የምናስተውለው እውነት ነው።
በተለይም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ ሀገር አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት እያደረግነው ባለው ጥረት ውስጥ ፤ ለራሳቸው ሰላም ያጡ ግለሰቦች በተለያየ መንገድ የኔ የሚሉትን ማኅበረሰብ ጨምሮ ሀገርን ሰላም ለማሳጣት እየሄዱበት ያለው የጥፋት መንገድ ከላይ የተገለጸውን እውነታ በተጨባጭ የሚያመላክት ነው።
ሰላም በማጣት የተመሰቃቀለ ማንነታቸው ለፈጠረው የጥፋት ስብዕናቸው መሸፈኛ የተለያዩ ስያሜዎችን ለራሳቸው በመስጠት ሕዝባችንን በፈጠራ ወሬዎች እና ትርክቶች ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል፣ ዛሬም በዚህ ስብዕናቸው የሕዝባችንን ዛሬዎች ብቻ ሳይሆን ነገዎች ላይ ጥላ ሊያጥሉ በሚችሉ የጥፋት ተልዕኮዎች ተጠምደው ይታያሉ።
ዛሬ የሚሉትን ነገ የማይደግሙ፣ ትናንት ካሏቸው ጋር ዛሬ በአደባባይ የሚጋጩ ፣ ለዚህም ምክንያታዊ በመሆን ራሳቸውን ከተያዙበት የማንነት ምስቅልቅል ለመታደግ የሚሞክሩ፤ በሂደቱም ያገኙትን ሁሉ በመፈረጅ ራሳቸውን ጤነኛ አድርገው ለማቆም የሚጥሩ ናቸው።
ስለ ሀገር አንድነት ተሟጋች ነን እያሉ ፤መሽቶ እስኪነጋ ሀገርን በሚያፈርስ ሴራ ተጠምደው የሚውሉ ፤ የሆነ ብሔር ተቆርቋሪ ነን እያሉ ፤ የዚያን ብሔር መልካም እሴቶችን በማጥፋት፣ አይደለም ከሌሎች ከራሱ ጋር ተስማምቶ እንዳይኖር የአስተሳሰብ መዛነፍ ለመፍጠር ሌት ተቀን የሚጥሩ ናቸው።
ይህ ከባሕሪያቸው የሚመነጭና ራስን በአግባቡ ቆም ብሎ ካለመመልከት እያደገ የሚሄድ የስብዕና መዛነፍ ፤ የፖለቲካ ካባ ለብሶ ሲገለጥ የቱን ያህል ለአንድ ማኅበረሰብም ሆነ ሀገር የአደጋ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል እንደ ሃገር ብዙ ዋጋ በመክፈል አይተነዋል፤ እያየነውም ነው።
ለውጡን ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ ሀገር ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በነዚህ ግለሰቦችም ሆነ የነሱ ስብስቦች/ቡድኖች/ ስንቴ እንደፈረሰች ለመቁጠር ያዳግታል፤ ከየአንዳንዷ የጥፋት ትርክታቸው ማግስት በእነርሱ አዕምሮ ሃገር ፈርሳ አድራለች ።
ከያንዳንዷ የግጭት ትርክታቸው ማግስት ሕዝብ በሕዝብ ላይ ተነስቶ፣ሀገር በደም ጎርፍ ተጥለቅልቃ፤በጣርና ሲቃ ፤በለቅሶና በዋይታ ተሞልታ መሽቶ የሚነጋ ይመስላቸዋል። ይህ ስለሀገርና ሕዝብ ያላቸው መሻትና የተልእኳቸው አልፋና ኦሜጋ ነው።
እነዚህ ግለሰቦች ከግጭት የሚያተርፉ ይመስላቸዋልና ያላቸውን ዕውቀት፣ጊዜና አቅም ሁሉ ለዚህ እኩይ ተልእኮ ያውላሉ ፤ ቆም ብለው ምን እየሠሩ እንደሆነ ለማየት ፈቃደኛ አይደሉም፤ ለራሳቸው ያላቸው የተሳሳተ ግምት የገዛ ጠላታቸው ሆኖባቸዋል። ስለሆነም በዚህ ክፉ ርግማን ውስጥ ሲዳክሩ መሽቶ ይነጋላቸዋል።
አንዳንዶች ለእነዚህ በሰላም እጦት በተመሰቃቃለ ማንነት ለሚሰቃዩ ግለሰቦች እና ቡድኖች የጥፋት እና የግጭት ትርክት ጆሯቸውን በመስጠት የገዛ ሰላማቸውን ፣ ከዚያም ባለፈ የማኅበረሰባቸውንና የሀገራቸውን ሰላም በሚፈታተን መንገድ ላይ ቆመው መገኘታቸው ነው።
ማንኛውም ለሀገሪ ተቋርቋሪ የሆነ ዜጋ የራሱን ሰላም ከዚያም ባለፈ የሚኖርበትን ማኅበረሰብና የሀገሪቱን ሰላም ለመጠበቅ ከእነዚህ ግለሰቦች እና ቡድኖች የጥፋት እና የግጭት ትርክቶች ጆሮዎቹን ማራቅ ይጠበቅበታል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም