የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን በተያዘው ዓመት ከሚያካሂዳቸው ውድድሮች መካከል አንዱ አህጉር አቀፉ ከ18 እና 20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ቻምፒዮና ነው።ኮንፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም በየፊናቸው ይካሄዱ የነበሩትን እነዚህን ውድድሮች በማጣመር ማካሄድ ከጀመረ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ሲሆን፤ ከሁለት ሳምንት በኋላም ይጀመራል።የመም እና በሜዳ ተግባራት ፉክክሮችን የሚያካትተው ይህ ውድድር በርካታ ወጣት አትሌቶችን ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የማሸጋገር ከፍተኛ ሚና አለው።
ከትምህርት ቤቶችና የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ተቋማት የሰለጠኑ አትሌቶች አቅማቸውን ለመፈተሽ እንዲሁም የውድድር ልምድ እንዲያገኙ ከአገር ውስጥ ውድድሮች ባለፈ መሰል በዕድሜ ገደብ የሚደረጉ ውድድሮች ላይ ተካፋይ እንዲሆኑ ተደርጓል። አሁን ላይ ለእውቅና የበቁ አትሌቶችም መነሻቸውን ያደረጉት በእነዚህ ቻምፒዮናዎች ላይ ነው።ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከ18 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ ይከናወናል።ተተኪና ወጣት አትሌቶችን ማፍራትን ዓላማው ያደረገው ይህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ የተከናወነው ኮትዲቯር አቢጃን ላይ ከአራት ዓመት በፊት ነበር።
የሁለተኛውን ቻምፒዮና አዘጋጅነት ተራ ዛምቢያ ሲሰጣት አስቀድሞ ውድድሩን ለማድረግ የተመረጠችው ከተማ ሉሳካ ብትሆንም፤ የቦታ ለውጥ በማድረግ ከሉሳካ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ናዶላ ከተማ የቀየረ መሆኑን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።አገሪቷ ዝግጅቷን ያጠናቀቀች ሲሆን፤ በውድድሩ ላይ 50 አገራት አትሌቶቻቸውን ከ18 ዓመት በታች በ40 እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች በ44 የውድድር ዓይነቶች የሚያካፍሉም ይሆናል።ከሁለት ሳምንት በኋላ ለሚካሄደው ለዚህ ውድድርም ኢትዮጵያን ጨምሮ የኮንፌዴሬሽኑ አባል አገራት ወጣት አትሌቶቻቸውን በማዘጋጀት ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው፣ በቻምፒዮናው ኢትዮጵያን የሚወክለው የታዳጊና ወጣት ቡድን ከሳምንት አስቀድሞ ሆቴል በመግባት ልምምድ እና ዝግጅት ተጀምሯል። ከ30 የማያንሱ አትሌቶች በሁለቱም ጾታ እና የዕድሜ እርከኖች የተመረጡ ሲሆን፤ ከ800 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሜትር ድረስ ባሉ የውድድር ርቀቶች ተካፋይ ይሆናሉ።ቡድኑ ከአትሌቶች ባሻገር ከ9 አሰልጣኞችን እንዲሁም 4 የሚሆኑ የህክምና ቡድን አባላትን ያካተተ መሆኑም ታውቋል፡፡
ቡድኑ በተለያዩ ስፍራዎች ላይ ልምምዱን አጠናክሮ የቀጠለ ይሁን እንጂ፤ በአዲስ አበባም ሆነ ሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ከፍተኛ የመም እጥረት መኖሩ ዝግጅቱን አዳጋች አድርጎታል።በተለያዩ ቻምፒዮናዎች በሩጫ ውድድሮች ብቻ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመም ውድድሮች ውጤታማ መሆኑ ይታወቃል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የመም አለመኖር ለመሰል ልምምዶችም ሆነ ውድድሮች እጅግ ፈታኝ እየሆነ ይገኛል። ይህም ውጤት ላይም የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ እያደረሰ መሆኑ ተጠቁሟል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ለዚህ ችግር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮችን በመፍታት ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካው የ18 እና 20 አመት በታች የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተከታታይ የሆነ ጠንካራና ከፍተኛ ዝግጅቱን እያደረገ እንደሚገኝ በድረገጹ አስነብቧል።
በአፍሪካ የሚካሄዱ የዕድሜ ገደብ ያላቸው ውድድሮች ላይ በቀዳሚነት የሚነሳው ችግር የዕድሜ ማጭበርበር መሆኑ ይታወቃል።ኮንፌዴሬሽኑም አገራት ከ18 ዓመት በታች ውድድር ላይ እአአ በ2006 እና 2007 ወዲህ የተወለዱ እንዲሁም ከ20 ዓመት በታች እአአ ከ2004 እና 2005 ወዲህ የተወለዱ አትሌቶችን ብቻ እንደሚያሳትፍ አስታውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2015