በየትኛውም ወቅትና ሁኔታ ጀግና ይፈጠራል። በጦር አውድማ የተዋደቀውም፣ ለመልካም ተግባር የተጋውም፣ ለሰው ልጆች ወይም ለሌሎች ፍጥረታት ሲል ዋጋ የከፈለውም፣ በስፖርት መድረክ አገሩን ያስጠራም በየመስኩ ጀግና ነው። የአንዳንድ ጀግኖች ገድል ግን ለየት ያለና ሁሌም የሚታወስ ይሆናል። ከእንዲህ ዓይነት አይረሴ ጀግኖች መካከል ከስፖርት የታሪክ ማህደር ውስጥ አንዱን እንመልከት።
ሙሉ ስሙ ቴራንስ ስታንሊ ፎክስ ይባላል። በተለየ የሚታወቀው ቴሪ ፎክስ በሚል አጭር መጠሪያው ነው። ይህ ሰው ካናዳዊ ነው፤ በ1958 ይህቺን ዓለም ሲቀላቀል ቤተሰቦቹ ከሌሎች ሰዎች የተለየ ባህሪ እንዳለው ገና በሕፃንነቱ ነበር የተረዱት። እጅግ የበዛ የተወዳዳሪነት (የተፎካካሪነት) ስሜት ሲኖረው፤ መሸነፍ ደግሞ ሞቱ ነው።
ስኬት ፊቱን እስኪያበራለት ከመታገል ወደኋላ የማይለው ፎክስ በቅድሚያ የተቀላቀለው በትምህርት ቤቱ የሚገኝ የቅርጫት ኳስ ስፖርት ቡድንን ነበር። ትክለሰውነቱን የተመለከቱት አሰልጣኝ ደግሞ አትሌቲክስን እንዲሞክር ምክረሃሳብ ሰጡት። በመጀመሪያ አሰልጣኙን ለማስደሰት ሲል እንደተባለው ሩጫን ቢጀምርም የኋላ ኋላ እጅግ ስለወደደው ሁለቱን ስፖርቶች ጎን ለጎን ማስኬድ ጀመረ። የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ሲያጠቃልልም የዓመቱ ምርጥ አትሌት ተብሎ ለሽልማት በቅቶ ነበር።
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በመግባትም ከስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍሎች አንዱን ካጠና በኋላ የስፖርት መምህር ሆነ። ስፖርትን የሕይወቱ አካል ያደረገው ፎክስ ከመምህርነት ሥራው ጎን ለጎን በአገሩ የሚገኙ ቅርጫት ኳስ ቡድንን በመቀላቀል በውድድሮች ላይ ይካፈል ነበር። እአአ በ1976 ግን ቀድሞ በደረሰበት የመኪና አደጋ ምክንያት ችላ ያለው የጉልበቱ ጉዳት ማገርሸት መጀመሩን ተከትሎ የሕይወቱ መስመር ተቀየረ። እየባሰ በሄደው ህመሙ ምክንያት ሃኪም ቤት የተገኘው ፎክስ፤ ህመሙ ወደ ካንሰርነት እየተለወጠ በመሆኑ ሕይወቱን ለማትረፍ ሲባል እግሩ መቆረጥ እንዳለበት ተነገረው። ብርቱው ወጣት ከከባዱ ህመም አገግሞ በሰው ሰራሽ እግር ወደ ቀደመ ሕይወቱ ለመመለስ ጥቂት ወራት ብቻ ነበር የፈጀበት።
ፎክስ የአካል ጉዳቱን ተከትሎ ከካናዳ ዊልቸር ስፖርቶች ማህበር ጋር በቅርበት መስራት ሲጀምር፤ ከዊልቸር ቅርጫት ኳስ ስፖርት ቡድን ደግሞ እንዲቀላቀላቸው ጥሪ ቀረበለት። ፈጣኑ ፎክስ ስለ ስፖርቱ ተገንዝቦ ተወዳዳሪ ለመሆን የፈጀበት ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ብቻ ነበር። ከቡድኑ ጋር በካናዳ በሚካሄዱ ቻምፒዮናዎች ላይ በመካፈልም ሶስት ጊዜ አሸናፊ መሆን ሲችል፤ በሰሜን አሜሪካ ቅርጫት ኳስ ማህበርም እአአ በ1980 ምርጥ ተጫዋች በሚል ሊሰየም ችሏል። በልጅነት የተጀመረው የስፖርት ሕይወቱ በአካል ጉዳት የቀጠለ ይሁን እንጂ፤ የዘወትር ህልሙ ማራቶንን መሮጥ ነበር። በእርግጥ ነገሩ የማይሆን ይምሰል እንጂ፤ ማነሳሻ የሆነው ግን እሱን በመሰለ የአካል ጉዳት ማራቶንን ሮጦ ያጠናቀቀ ሰው ታሪክ ነበር።
ይህን ሃሳብ ቤተሰቡን ጨምሮ በርካቶች ቢቃወሙትም ለ14 ወራት ዝግጅት ካደረገ በኋላ፤ ዓላማው ከሩጫ ባለፈ የገቢ ማሰባሰቢያ እንደሚሆንና ይኸውም ለካንሰር ህክምና እና ምርምር እንደሚውል አሳወቀ። ‹‹የተስፋ ማራቶን›› ሲል የሰየመው ይህ የግሉ ሩጫም ከገቢ ማሰባሰቡ ጎን ለጎን ስለ ካንሰር ግንዛቤ የማስጨበጥ ዓላማንም ያነገበ ነበር።
ሩጫው በአንድ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ እግር በመሆኑ እጅግ ፈታኝ መሆኑ አያጠራጥርም። ነገር ግን ጽናት መለያው የሆነው ፎክስ በቅድሚያ 1 ሚሊዮን ዶላር ቀጥሎ 10 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ቻለ። ይህ ዓላማው በመላው ካናዳውያን ዘንድ እውቅና በማግኘቱም በትልልቅ ውድድሮች ላይ እስከመጋበዝ ደረሰ፤ በመላው ዓለምም ለበርካቶች ተምሳሌት ሆኗል። በገቢ ማሰባሰቢያውም ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ አግኝቷል።
በመጨረሻ ግን የካንሰር ህመሙ ተቀስቅሶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ በሃኪሞች አስገዳጅነት ሩጫውን አቁሞ ህክምናውን ጀመረ። አስከፊ ከሆነው የወራት የካንሰር ትግል በኋላ ግን ተሸነፈ፤ እአአ በ1981 ሕይወቱ አለፈ። ይህንን ተከትሎም በአገሩ ብሔራዊ ጀግና ተሰኘ። እሱን የሚያስታውሱ ሐውልቶች ቆሙለት፣ መንገዶችም በስሙ ተሰየሙለት። የእሱ የሕይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥኑ ፊልሞችም የተሠሩ ሲሆን፤ ቤተሰቦቹም በርካታ ሽልማቶችን ከህልፈቱ በኋላ ተበርክቶላቸዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2015