ታደሰ አለሙና ፋሲካ በሚገርም መልኩ ተቆራኝተዋል።ምን አቆራኛቸው ከተባለ ደግሞ ሙዚቃ፤ ከሙዚቃም ደግሞ የማይረሳና የማይዘነጋ ትዝታና የጥበብ ጥላ ያረፈበት ሚሻሚሾ የተሰኘ ሙዚቃ ነው።ሚሻሚሾ በጥኡም ቃና የተጠመቀም የፋሲካ በአል ማድመቂያ የተከሸነ ወይን ነው ቢባል አልተጋነነም።የትንሳኤ በአልና ድምፃዊ ታደሰ የተቆራኙበት ገመድም ከአመት አመት ላይበጠስ ወርቃማና ፈርጣማ በሆነ የጥበብ ሰንሰለት ተሳስረው በየፋሲካው ሁሌም አዲስ ሆነው ይመጣሉ።
በፋሲካ በአል ሚሻሚሾ ሁሌም በአዲስ ቃና ይደመጣል። በየበአላቱ አዳዲስም ሆነ ቆየት ያሉ ሙዚቃዎችን መስማት የተለመደ ነው። ነገር ግን እንደዚህ ሙዚቃ ከበአል ጋር መሶብ ከነአፎቱ መስሎ የተሰካካ ሙዚቃ ፈልጎ ማግኘት በጨረቃ ብርሃን ከመሬት ላይ ጤፍ እንደመልቀም ይቆጠራል። በሚሻሚሾ ሙዚቃው ውስጥ ባህልና ሃይማኖት በሚገርም መልኩ ተዋህደዋል።ፋሲካ ሃይማኖታዊ በአል ቢሆንም፣ በበአሉ ያሉትን ሃይማኖታዊ ይዘቶች ከኢትዮጵያ የባህል ቅኝት ጋር ደህና አድርጎ በመከሸን ሁለቱ ያላቸውን ትስስር አጉልቶ ለማውጣት ተችሎታል።ሚሻሚሾ ድምጻዊው ስለበአል የሰራው የመጀመሪያ ሰራው አይደለም።ከዚያ ቀደም “አውዳመት” የሚል ሌላ ሥራም ነበረው፤ ይሁን እንጂ ሙዚቃው እንደአብዛኛዎቹ የበአል ሙዚቃዎች በአሉን ከማድመቅ ባለፈ የተለየ የትርጉም ይዘት አልነበረውም።ሚሻሚሾ የተሰኘው ሙዚቃ ተወዳጅ እንዲሆንና ድምጻዊውም ገኖ እንዲወጣ ያደረገው ነገር ቢኖር በዜማና ግጥም ታሽተው ከጆሮ ቁልቁል የሚፈሱት የታሪክ ፍሰቶች ናቸው።
ለመሆኑ ሚሻሚሾ ሲባል ምን ማለት ይሆን? ትርጓሜው ከስቃይ፣ ከመከራና ከብዙ ችግር በኋላ የሚገኝ ደሰታ እንደማለት ነው።በአገው አካባቢ የሚዘወተር ባህላዊ የወጣቶች ጨዋታም ነው።ይህን ሙዚቃ እንድንወደውና እንድናደንቀው የሚያደርገን አንደኛው ምክንያት እዚህ ጋር ይገናኛል፡፡
ታደሰ ይህንን ባህላዊ ጨዋታ መነሻ በማድረግ ጥበባዊ ለዛ በፈሰሰበት መልኩ የፋሲካን ክዋኔዎችና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን በመቀላቀል ለጆሮ ጥኡምና ማራኪ እንዲሆን አድርጎታል።በበአለ ሥርዓቱ ውስጥ በፋሲካው ሰሞን ያሉትን በልዩነት የሚከበሩትን ዕለታት በመጥቀስም ያላቸውን ገጽታ ቁልጭ አድርጎ ያስመለክተናል።ካነሳነው አይቀርም የሚሻሚሾ ሙዚቃ ግጥም እንዲሁም በበአልና ባህል መሃከል የተሰደሩበትን መንገድ እንቃኛቸው፡፡
ገጥምና ዜማውን በደፈናው ስንመለከት በሙዚቃው የመጀመሪያ ምዕራፍ ወይንም “በቀራኒዮ ላይ ታየ” የጌታችን የመድኃኒታችን የእየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሳኤን ይተርካል።ያሳለፋቸውን መከራና ስቃይ በሙሉ ሃይማኖታዊ ይዘታቸውን እንደጠበቁ ተቀምጠዋል።በስተመጨረሻም ስቃይና ሞትን ድል አድርጎ ሲነሳ የሙዚቃው ዳራም እንዲሁ ይቀየራል።ከረሃብና ጥም ወደ ጥጋብና በረከት፣ ከኀዘንና መከራ ወደ ደስታና ፍሰሃ ሲሸጋገር ሙዚቃው የተገነባበት ግጥምና ዜማም ግሩም በሆነ የሽግግር ሂደት እንዲሁ መሰረቱን ቀይሮ ከባህላዊው ጨዋታ ጋር ያዋዛዋል።ከእየሩሳሌም ወደ አገው ምድር የተደረገ የተሳካለት ምናባዊ ጉዞ!
በሙዚቃ ሥራው ላይ እንደምንመለከተው የሙዚቃ ስልቱ በብዛት በአገው አካባቢ የሚዘወተር ሲሆን ከአሸንዳ ጭፈራ ጋርም የሚያመሳስል ነገር አለው። እስቲ ይህን ሙዚቃ ለሁለት ከፍለን እንመለከተው። የመጀመሪያው
በቀራኒዮ ላይ ታየ
ታየ ታየ
በጎልጎታ ላይ ታየ
ታየ ታዬ
የዓለም መድኃኒት የጌታ ትንሳኤ
የጌታ ትንሳኤ
በለተ ፋሲካ በጌታ ትንሳኤ
በጌታ ትንሳኤ
……….
አርባ ቀን አርባ መአልት ገዳመ ቆሮንጦስ ጌታ
ተፈትኖ
ለፈጠረው ፍጡር ተወግሮ ተሰቅሎ የዓለም ቤዛ
ሆኖ
ክርስቶስ ታጅቦ እየበተኑለት የዘንባባ ለምለም
ሆሳዕና በአርያም በአህያ ውርንጫ ገባ እየሩሳሌም
ከደቀ መዝሙራት በ30 ዲናር ይሁዳ ሽጦት
በፀሎተ ሐሙስ ስጋ ደሙን ሰጠን ለኛ ድህነት
……..
በእነዚህ ግጥሞች ውስጥ ፈጣሪ የሰውን ልጅ ወዶ በሰው ልጆች ሀጢያት ምክንያት የከፈለውን ታላቅ መስዋዕትነት እያነሳ ይዘክራል። በስቅለቱ ዋዜማ የነበረውንም ሁኔታ ከታላቁ መጽሐፍ እየቀነጨበ ስዕላዊና ገላጭ በሆነ መልኩ ይተርከዋል። እንገዲህ በአንዲት የስድስት ደቂቃዎች ገደማ ርዝመት ባላት የሙዚቃ ሥራ ውስጥ ይህንን የሚያህል ግዙፍ ታሪክ ቁልጭ አድርጎ ከማሳየቱም ባሻገር ግጥምና ዜማው ከድምጹ ጋር ተዋህዶ የቀረበበት መንገድ የታደሰ አለሙን የሙዚቃ ጥበብ የሚያንጸባርቅም ጭምር ነው። በዚህ የታደሰ አለሙ ዘመን አይሽሬ ሙዚቃ ውስጥ ከላይ ለማሳየት ከሞከርነው ግጥምና ዜማ ቀጥሎ የሙዚቃው የጀርባ አጥንት የሆነው ሁለተኛውና በማበቂያው ላይ የምናገኘው የመጨረሻው ክፍል ነው። መጠሪያውም የተቀዳው ከዚሁ ክፍል ነው። የዜማ ቅኝቱን ለወጥ በማድረግም ኦ ሚሻሚሾ ሲል ስሜትን ቀስቀስ በሚያደርግ መልኩ ይጀምረዋል።
ኦ ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ከብረሽ ቆይኝ ከብረሃ በ30 ጠምደሃ
ከብረሽ ቆይኝ ከብረሽ በ30 ጠምደሽ
የጌታዬ ሰቀላ ተሸልሟል በአለላ
የእመቤቴ አዳራሽ ተሸልሟል በሻሽ
ኦ ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
እምዬ ይነሱ ይንበሳበሱ
እማ ከድፎው ቢሰጡኝ ቢቆርሰው
እማ ከጉልባኑ ይዝገኑ ይዝገኑ
እማ ከዱቄቱ ትንሽ በወጭቱ
ማጣፈጫ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
መሰልቀጫ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ትንሽ ቅቤ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ለወገቤ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ትንሽ ጨው
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ቆንጥረው
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ከቅመሙም
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ጣል አርገው
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
በርበሬውን
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ቀላቅለው
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ማጣፈጫ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
መሰልቀጫ
ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ
ሙዚቃውን አስተውለን ከተመለከትነው አብዛኛውን ባህል ነክ የሆኑ ሃሳቦችና የባህል ጭፈራ ስልትን እናገኝበታለን። የሥነ ግጥም ቅኝቱም ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እናቶች ጓዳ የተቀዳ ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻውም። እማ ከድፎው…እማ ከጉልባኑ..ትንሽ በውጭቱ…ትንሽ ቅቤ..መሰልቀጫ..ለወገቤ..ከቅመሙ..ማጣፈጫ..ጣል አድርገው…እያለ ጣል ያደረጋቸው የዜማው ማጣፈጫዎች በእጅጉ የተዋቡ ቃላቶች ናቸው። የማህበረሰባችን ባህልና በአላዊ ትውፊቶች ምን ያህል ከሃይማኖት ሥርዓት ጋር የተቆራኙ እንደሆኑ ያመላክተናል።
በበአለ ፋሲካው የተከናወኑትን ሁነቶች የሚዳስስና የሚገልፅ ነው።ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ እየሩሳሌም መሄዱን ፣ በሃዋርያው ይሁዳ በ 30 ዲናር መሸጡን ፣ በዕለተ ሐሙስ ወይንም ደግሞ በፀሎተ ሐሙስ ይህ “ነገ የሚፈሰው ደሜ ነው…ይህም ነገ የሚቆረሰው ስጋዬ ነው” በማለት ክርስቶስ የተናገረውን ቃል በመጽሐፉ ፣ እንደተጻፈው ከዚህ በሚስማማ መልኩ ታደሰም ….. በፀሎተ ሐሙስ ስጋ ደሙን ሰጠን ለኛ ድህነት…በማለት ገልጾታል። ከዕለተ ስቅለቱ ከአርብ እስከ ዕለተ ትንሳኤው እሁድ ድረስ ያሉትን ሃይማኖታዊ እውነታዎች በመግለጽ “እንኳን ደስ አላችሁ ሞትን ድል አድርጎ”፤ የጌታችን ሞትን ድል አድርጎ የመነሳትን ብስራት እያበሰረን ይጨርሳል። እንግዲህ ድምጻዊው ለፋሲካችን ማደመቂያ ይሆን ዘንድ ያበረከተልን ይህ ውብ ሙዚቃ እንደሙዚቃነቱ ብቻ አድምጠነው የምናልፍ ከሆነ ተሳስተናል። ሙዚቃውን አድምጠንና መርምረን አጭቆ የያዘውን ሌላኛውን የሙዚቃውን ወበት ከአዕምሮአችን እንዲሁም ከልባችን ልናኖረው ይገባል። በነገራችን ላይ በዚህ የሙዚቃ ሥራ ውስጥ ሁለት የተለያዩ የዜማ ቅኝቶች እንዳሉ መርሳት የለብንም። እነዚህ ሁለት ዜማዎች አንደኛው የድምጻዊው ታደሰ አለሙ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሕዝብ ዜማ ነው። በዚህ የሕዝብ ዜማ ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ ግጥሞችም በድሮው ጊዜ እንደባህላዊ ባሉ ጨዋታዎች መሀል የሚዘወተሩ ናቸው። ድምጻዊው ልናደንቀው የሚገባው ሁለተኛው ምክንያትም የቀደመውን ቱባ ባህል በሚያምር መልኩ ስላሳየን እንዲሁም ስላስተዋወቀንም ጭምር ነው።
ከዚህ የአውዳመት ስጦታ ባሻገር ታደሰ አለሙ በብዛት የሚታወቀበት ሌላም ልዩ መታወቂያ አለው።መቼም ይህንን ልዩ ስጦታውን በወግ ማዕረግ ተጋበቶ ወዳጅ፣ ቤተዘመዱን ጠርቶ የተጨፈረላቸው ሙሽሮችም ሆኑ የጨፈሩ አጃቢና ሚዜዎች በደንብ ያስታውሱታል።ያለእርሱ ሙዚቃዎች ሠርጉም ሠርግ፣ ድግሱም ድግስ አይመስልም።ከእያንዳንዱ ሠርግ ቤት የሚወጣው ይህ የሙዚቃ ቃና በልዩ ጸአዳ የተከሸነ ልዩ መአዛ አለው።ከበስተጀርባው ደግሞ ታደሰ አለሙ አለ።
የሰሞንኛውን የፋሲካ በአል ሙዚቃን ጨምሮ በርካታ የሠርግና የባህል ማራኪ የሙዚቃ ሥራዎችን ዘመን የማይሽራቸው አድርጎ በመስራት ያስረከበን ይህ ታላቅ የኢትዮጵያ ልጅ የተገኘው ከወለጋ ምድር ሲሆን አገራችን ካፈራቻቸው አይረሴ ድምጻውያን አንዱ ነበር። በ80ዎቹና 90ዎቹ የነበረ ትውልድም በሚገባ ያስታውሰዋል። በእርሱ ሙዚቃዎች ያልደመቁ በአላትና ሠርጎችም አልነበሩም። ታላቁ የጥበብ ሰው በሙዚቃ መንገድ ብዙ አመታትን ተጉዞ በመጨረሻም 1999 ዓ.ም የሕይወቱ ማብቂያ ነበረች።ብዙ ነገሮቹ በነበር የቀሩ የታሪክ ትዝታዎች ሆነዋል። የእርሱ ስም ገኖ ከወጣበት ዘመንና በተለያዩ ምክንያቶች የዝነኝነቱን ያህል የሕይወት ታሪኩ በአግባቡ ተጽፎ ከታላላቆች የሕይወት ባህረ መዝገብ ሳይሰደር አልፏል። ድምጻዊ ታደሰ ለሚዲያ ከበቁ ሥራዎቹ ባልተናነሰ ሁኔታ በውስጥ ለውስጥና መድረኮች ላይ የሠራቸው ሥራዎች ብዙ ናቸው። በዚህ የፋሲካ በአል አበርክቶልን የሄደውን ሙዚቃ እንደ አዲስ እያጣጣምን እርሱንም እናስታውሰዋለን።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም