ዛሬ ዕለቱ ፋሲካ(ትንሳኤ) ነው። የትንሳኤ በዓል ዕለቱን(እሁድ) አይለቅም እንጂ ቀኑ ይቀያየራል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ወሩን ሁሉ ሊለቅ ይችላል። ስለዚህ ሳምንቱ በታሪክን ስናስታውስ የሳምንቱ ክስተቶች የፋሲካ ሰሞን ክስተቶች ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ ለማለት ነው።
በዚህ ሳምንት እጅግ ግዙፍና በርካታ የታሪክ ክስተቶች ተከናውነዋል። ጥቂቶችን እናስታውስና አንዳንዶቹን ዘርዘር አድርገን እናያለን።
ከ11 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም አረፉ።
ከ155 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዝያ 3 ቀን 1860 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ታማኝ የጦር መሪ የነበሩት ፊታውራሪ ገብረሕይወት ጎሹ (ገብርዬ) አረፉ።
ከ113 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዝያ 3 ቀን 1903 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ታማኝ መኳንንት መካከል አንዱ የነበሩት ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው (አባ ቀማው) አረፉ።
ከአንድ ሺህ 510 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ.ም ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ርዕሰ ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድ ማህሌታይ ተወለደ። በዚህ ሳምንት እና በዚሁ ቀን ከ162 ዓመታት በፊት ሚያዝያ 5 ቀን 1853 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ ልጅ የሆነው ‹‹ባይተዋሩ መስፍን›› ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ተወለደ።
አሁንም በዚሁ ሳምንትና ቀን ከ73 ዓመታት በፊት ሚያዝያ 5 ቀን 1942 ዓ. ም ፀረ ፋሽስቱ አርበኛ ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ አረፉ።
ከ155 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ዘመነ መሳፍንትን አንኮታኩቶ በመጣል ኢትዮጵያን አንድ ያደረጉት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ አረፉ።
ከ72 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ቀን ሚያዝያ 8 ቀን 1943 ዓ.ም የ‹‹ቃኘው›› ሻለቃ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ኮሪያ ለመዝመት ከጅቡቲ ወደብ ተንቀሳቀሰ።
እነዚህ ክስተቶች በተለያዩ ዘመናት በዚህ ሳምንት የተከሰቱ ናቸው። የአንዳንዶቹ በተለያየ አጋጣሚ ብዙ የተባለለት ሲሆን የአንዳንዶቹ ግን ብዙም ያልተባለለት ነው። ስለዚህ የጀግንነታቸውን ያህል ብዙም አልተዘመረላቸውም ያልናቸውን ዘርዘር አድርገን እናስታውሳቸው።
ገብርዬ
ትውልዳቸው ጋይንት የሆነው ፊታውራሪ ገብርዬ ሙሉ ስማቸው ገብረሕይወት ጎሹ ነው። በጀግንነታቸውና በጦር አመራራቸው እጅግ የተደነቁ ጀግና ነበሩ። ለዚህም ነው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ‹‹ይዋጓል እንደ ገብርዬ፤ ይማሯል እንደ አካልዬ›› ብለው የተናገሩት። ‹‹አካልዬ›› ያሏቸው ‹‹ባለአራት ዓይን›› የሚባሉትን ሊቀ ሊቃውንት አካለወልድ ሰርፀወልድን ነው።
ገብርዬ ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የሽፍትነት ጊዜ ጀምሮ ታማኝ አጋራቸው ነበሩ። ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በመጨረሻው ዘመናቸው ብዙ ሠራዊታቸው እየከዳቸው የወታደራቸው ቁጥር እጅግ ተመናምኖ ነበር።
32 ሺህ ዘመናዊ የእንግሊዝ ጦር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ንጉሠ ነገሥቱን ሊወጋ ዝግጅት ሲያደርግ ፊታውራሪ ገብርዬ 5000 ጦር ብቻ ይዘው እንዲገጥሙ ታዘዙ። ሚያዝያ 3 ቀን 1860 ዓ.ም በዕለተ ዓርብ፣ በስቅለት ቀን እሮጌ ሜዳ ላይ እየተዋጉ ሳለ ሞቱ።
ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስም የረጅም ጊዜ ታማኝ አጋራቸውንና ጀግና የጦር መሪያቸውን አጡ። ሞታቸውን ሲሰሙም ‹‹የእናቴ ልጅ ጓዴ›› ብለው አለቀሱ። ከሦስት ቀናት በኋላም (ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም) ዳግማዊ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ገብርዬን ተከተሏቸው።
ራስ ተሰማ ናደው
ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ.ም የዙፋናቸው ወራሽ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል እንደሆነ ሲያሳውቁ ራስ ተሰማ ናደውን ሞግዚትና እንደራሴ አድርገው ሾሟቸው። ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ሐምሌ 18 ቀን 1901 ዓ.ም ለራስ ተሰማ ናደው ‹‹ራስ ቢትወደድ›› የሚል ማዕረግ ተጨመረላቸው።
ራስ ተሰማ ናደው በንጉሥ ምኒልክ አገር የማቅናት ዘመቻ ወቅት ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ሰው ናቸው። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ እንደፃፉት፣ ራስ ተሰማ ከኢሉባቦር ጀምሮ እስከ ነጭ ዓባይ ድረስ ያለውን ግዛት አቅንተዋል። በዓድዋ ጦርነት ወቅትም ትልቅ የጀግንነት ታሪክ ፈፅመዋል።
ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በሕመም ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን ባለመቻላቸው የሥልጣን ሽሚያው የከረረ ሆኖ ነበር። እቴጌ ጣይቱ ብጡል የባለቤታቸውን ሥልጣን በመጠቀም አድራጊ ፈጣሪ መሆን ሲጀምሩ እቴጌይቱ ከመንግሥት የፖለቲካ ሥራ እንዲገለሉ ካደረጉት መኳንንት መካከል ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ዋናው ነበሩ።
ልጅ ኢያሱ በአያታቸው ዙፋን ተቀምጠው አገር የማስተዳደሩን ሥራ በጀመሩበት ወቅት ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው ከጎናቸው ሆነው የእንደራሴነቱንና የማማከሩን ሥራ ያከናውኑ ነበር።
ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ታማኝ የነበሩና ከደጃዝማችነት ተነስተው ራስ ቢትወድ ማዕረግ ላይ የደረሱ ሰው ነበሩ።
የልጅ ኢያሱ ሚካኤል እንደራሴ ሆነው ‹‹ራስ ቢትወደድ›› ከተባሉ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ሚያዝያ 3 ቀን 1903 ዓ.ም በድንገት አርፈው ሥርዓተ ቀብራቸው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተፈፅሟል። የሞታቸው ምክንያት ከሐሜት ያለፈ የጠራ መረጃ የለውም።
ቅዱስ ያሬድ
ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ርዕሰ ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድ ማህሌታይ የተወለደው ከ1510 ዓመታት በፊት ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ.ም ነበር።
ቅዱስ ያሬድ ከአባቱ አብዩድ (ይስሃቅ) እና ከእናቱ ተውክልያ (ክርስቲና) ታላቋ አክሱም ከተማ ውስጥ ተወለደ። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ ከአጎቱ ከአባ ጌዴዎን ዘንድ ትምህርት ሊማር ቢሔድም ለበርካታ ዓመታት ትምህርት ሊገባው አልቻለም ነበር። በዚህም የተነሳ መምህሩ ይገርፉትና ይገሥፁት ነበር። እርሱም ከትምህርቱ ክብደት ባለፈ የመምህሩ ተግሣፅ ሲበረታበት ጊዜ ከአባ ጌዴዎን ቤት ወጥቶ በመሸሽ ላይ ሳለ ደክሞት ከአንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠ።
ከዛፉ ሥር ተጠልሎ ሳለ አንዲት ትል ፍሬውን ለመመገብ ወደ ዛፉ ስትወጣ፤ ነገር ግን መውጣት ስለተሳናት በተደጋጋሚ ስትወድቅ ቆይታ ከብዙ ሙከራ በኋላ ከዛፉ ላይ ወጥታ ፍሬውንም ስትመገብ ይመለከታል። ቅዱስ ያሬድ የትሏን ትጋት ካየ በኋላ እርሱም በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግ የከበደው ምሥጢር እንደሚገለጽለት በማመን ወደ መምህሩ ተመልሶ ይቅርታ በመጠየቅ ትምህርቱን እንደገና መቀጠል ጀመረ።
እግዚአብሔርን በጸሎት እየተማጸነ ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜን አጠናቆ መዓርገ ዲቁና ተቀበለ። ከመምህሩ ከአባ ጌዴዎን በተማረው መሠረት የእብራይስጥና የግሪክ ቋንቋዎችን ደህና አድርጎ ያውቅ ነበር ይባላል።
በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ከዓመት እስከ ዓመት ድረስ በየክፍለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ፣ በመጸውና በጸደይ፣ በአጽዋማትና በሰንበታት፣ እንዲሁም በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በደናግል በዓላት የሚደረስ ቃለ እግዚአብሔር በሦስት ዜማዎች ማለትም በግእዝ፣ በዕዝልና በአራራይ ደረሰ። የሰው ንግግር፣ የአዕዋፍ፣ የእንስሳትና የአራዊት ጩኸት ሁሉ ከነዚህ ከሦስቱ ዜማዎች እንደማይወጡ መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል።
ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ዝማሬ፣ መሥዋዕትና ምዕራፍ በቅዱስ ያሬድ የተደረት የዜማ መጻሕፍት ናቸው። በአንዲት ዕለት ቅዱስ ያሬድ ከብሉይና ከሐዲስ፣ እንደዚሁም ከሊቃውንትና ከመነኮሳት የተውጣጣውን መንፈሳዊ ድርሰቱን በዘመኑ ከነበረው ንጉሥ ከአፄ ገብረ መስቀል ፊት ቆሞ ሲዘምር ንጉሡ በድምፁ በመማረኩ የተነሣ ልቡናው በተመስጦ ተሠውሮበት (የሚያደርገውን ባለማወቁ) የቅዱስ ያሬድን እግር በጦር ወጋው። ከቅዱስ ያሬድ እግር ደምና ውኃ ቢፈስስም ነገር ግን ማኅሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ሕመሙ አልተሰማውም ነበር።
ንጉሡም ያደረገውን ሁሉ ባወቀ ጊዜ ደነገጠ፤ ጦሩንም ከእግሩ ነቅሎ ‹‹ስለፈሰሰው ደምህ ዋጋ የምትፈልገውን ሁል ለምነኝ›› እያለ ተማጸነው። ቅዱስ ያሬድም ‹‹ላትከለክለኝ ማልልኝ›› ብሎ ቃል ካስገባው በኋላ፣ ወደ ገዳም ሔዶ ይመነኩስ ዘንድ እንዲፈቅድለትና እንዲያሰናብተው ለመነው። ንጉሡም ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ፤ ተከዘ። ከእርሱ እንዲለይ ባይፈልግም ነገር ግን መሐላውን ማፍረስ ስለከበደው እያዘነ አሰናበተው።
ከዚያም ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ጽዮን ቤተ መቅደስ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ‹‹ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዐርገ ሕይወት … ፈጽሞ የከበርሽና የተመሰገንሽ፣ ከፍ ከፍም ያልሽ፣ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የሆንሽ›› እያለ አንቀጸ ብርሃን የተባለውን የእመቤታችንን ምስጋና እስከ መጨረሻው ድረስ ደረሰ።
ከዚህ በኋላ ከአክሱም በስተደቡብ አቅጣጫ ሄዶ በሰሜን ተራሮች አካባቢ በጾም በጸሎት ተወስኖ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያው ፈጸመ። እግዚአብሔርም ስሙን ለሚጠራ፣ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው።
ርዕሰ ሊቃውንት ቅዱስ ያሬድ ማህሌታይ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ልዩና ብቸኛ የሚያደርጓትን ሀብቶች(መለያዎች) ባለቤት ያደረገ ታላቅ ሊቅ ነው።
ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ
ፀረ ፋሽስት አርበኛው ደጃዝማች መንገሻ ጀምበሬ የተወለዱት ግንቦት 13 ቀን 1884 ዓ.ም ጎጃም ውስጥ፣ ሜጫ፣ ጉታ አውራጃ አካባቢ ነው። አባታቸው ደጃዝማች ጀምበሬ እምሩ የሜጫ፣ የዴንሳ፣ የጉታና የአገው ምድር ባላባት በመሆን ለብዙ ዓመታት አካባቢውን አስተዳድረዋል። ደጃዝማች ጀምበሬን ጨምሮ አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው ሁሉ የደጃዝማች ማዕረግ ነበራቸው። መንገሻ ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ብልህና አስተዋይ እንዲሁም በአልሞ ተኳሽነታቸው ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው፤ በበገና ድርደራ እና በፈረስ ግልቢያም የሚታወቁ ነበሩ። ለአደንና ለውሃ ዋናም ልዩ ፍቅር ያላቸው ጀግና ነበሩ። በተለያየ የጀግንነት ተሳትፎ ውስጥ ያለፉት መንገሻ በ32 ዓመታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ በማግኘታቸው የቡሬ ዳሞት አውራጃንና የሰከላ አካባቢዎችን ማስተዳደር ጀመሩ።
የተለያዩ አስተዳደራዊ ሥራዎችን እየሠሩ በ1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን ወረረ። ደጃዝማች መንገሻ በግዛታቸው ማለትም በሜጫ አውራጃ አካባቢ የሚገኘውን ጦር አስከትለው ከራስ እምሩ ጋር በትግራይ በኩል በመዝመት ለአገራቸው በጀግንነት ተዋጉ። ከማይጨው ውጊያ በኋላ የኢትዮጵያ አርበኞችም ወደ ኋላ በማፈግፈግና እንደገና በየአካባቢው የሚገኘውን የጎበዝ አለቃ እያስተባበሩ ጠንካራ ውጊያ ለማድረግ ሲዘጋጁ ደጃዝማች መንገሻም የአገው ምድር፣ ሠከላ፣ ሜጫ፣ ጉታ፣ አቸፈር፣ አለፋ ጣቁሳ አካባቢ አርበኞችን በማስተባበር ከወራሪው ጋር መፋለም ጀመሩ።
በ1929 ዓ.ም የመጀመሪያ ወር ላይ የጎንደርና የጎጃም አካባቢ የፋሺስት ጦር የበላይ አዛዥ የደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬን መጠናከርና በየአካባቢው የጦር አለቆችን መመደባቸውን ሲሰማ እጅግ ደነገጠ። ይህን የአርበኞችን መጠናከር ሊቋቋምልኝ ይችላል ብሎ ያሰበውን የጦር አዛዥ ሹም ሽር በማድረግና በርካታ ሰራዊት በመመደብ ጦሩ በከተሞች ተወስኖ ምሽግ ይዞ፣ ኃይሉን አጠናክሮ እንዲከላከል አዘዘ።
ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ቢቸናን፣ ራስ ኃይሉ ደብረ ማርቆስንና ሞጣን እንዲሁም ራስ በዛብህ ደግሞ ዳሞት አካባቢን በማካለል የጠላትን ጦር እረፍት ነሱት። ደጃዝማች መንገሻ ጀምበሬ ከደጃዝማች በላይ ዘለቀና ከሌሎች የውስጥ አርበኞች ጋር በመሆን በከፍተኛ መናበብና መቀናጀት እየተፋለሙ ቀጠሉ።
ደጃዝማች መንገሻ አስደናቂ የጦርና የደህንነት መረጃ አመራር ችሎታም ነበራቸው። የጠላትን እንቅስቃሴ ከውስጥ የሚያወጡና ከውጭ የሚጠቁሙ የመረጃ ሰዎች የሚገናኙባቸው ምስጢራዊ የግንኙነት መዋቅር ዘርግተውም ከመሪ አርበኞች ጋር ይገናኙ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ጉታ ገበርማ›› በተባለው ቦታ ከጠላት እጅ የተማረኩ መገናኛዎችንና የመልዕክት ማስተላለፊያ መስመሮችን አገናኝተው አቶ ጊላ ወልደ ጊዮርጊስ (በኋላ ደጃዝማች ) በሚባል ብልህ ሰው የሚመራ የስለላና የፕሮፖጋንዳ ኮሚቴ አቋቁመው ነበር፡። በነዚህ የመገናኛ መሣሪያዎችም የጠላትን እንቅስቃሴ ማዳመጥና የጠላትን የምልክት መገናኛ ኮዶችን መጥለፍ ተችሎ ነበር።
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን አርበኞች ትግል ክፉኛ ተዳክሞ በነበረበት ወቅት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከሱዳን ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እንደጀመሩ የጠላት ኃይል በቡሬ ከተማ በተጠናከረ ሁኔታ ምሽግ ሠርቶ ጠበቃቸው። ይህ የጠላት ኃይል መወገድ ነበረበትና ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬ ከዳሞቱ መስፍን ደጃዝማች ነጋሽ በዛብህ ጋር ተቀናጅተው በማጥቃት የጠላት ጦር ቡሬን ለቅቆ እንዲወጣ አደረጉት። በመቀጠልም የፋሺስት ኃይል ሙሉ ጎጃምን ለቅቆ ለመውጣት ተገደደ። ንጉሰ ነገሥቱም በደብረ ማርቆስ በኩል አድርገው ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ።
ደጃዝማች መንገሻ ጀንበሬም በቢትወደድነት ማዕረግ በጎጃም እንደራሴነት በማገልገል ላይ ሳሉ በ1937 ዓ.ም ወደ ሸዋ፣ አዲስ አበባ ተዛውረው በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት እንደራሴነት እስከ 1938 ዓ.ም ድረስ ካገለገሉ በኋላ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ።
ደጃዝማች ቢትወደድ መንገሻ የወለጋ ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው በማገልገል ላይ ሳሉ በሰሜኑ ግንባር በሽሬው ጦርነት በቦንብ ፍንጣሪ የቆሰለው አካላቸው ቁስሉ እያመረቀዘ ሲያሰቃያቸዉ ቆይቶ በእረፍት እጦት ምክንያት በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው በ1942 ዓ.ም አረፉ። ሥርዓተ ቀብራቸውም በከፍተኛ ክብር በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስተ ማርያም ካቴድራል ተፈፅሟል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም