ኢትዮጵያውያን ዘመናትን የተሻገረና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፈ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት እና የመቻቻል ባህል ባለቤቶች ነን። ያለው ለሌለው ማካፈል፤ የተቸገረን አይቶ አለማለፍ፤ የታመመ መጠየቅ ወዘተ እንደ ማኅበረሰብ ዘመናትን በፍቅርና በአንድነት ተሻግረን ዛሬ ላይ እንድንገኝ ያስቻሉንና ነገንም እንደሚያሻግሩን ተስፋ የምንጥልባቸው አኩሪ እሴቶቻችን ናቸው።
እነዚህ ለዘመናት አብረውን ከተጓዙ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴቶቻችን የመነጩ፤ ትውልዶች በየዘመኑ በብዙ ማስተዋልና መረዳት ተቀብለው እየተንከባከቡ፤ በተጨባጭም የሕይወታቸው መርህ አድርገው እየተገበሯቸው ፤ ከፍ ያለ መንፈሳዊ እርካታ፣ የሞራል ልእልና እና የሰውነት ልክ የተጎናጸፉባቸው ናቸው።
እነዚህ እሴቶቻችን ዘመኑ ባመጣው ራስ ወዳድነትና ራስ ወዳድነት በፈጠረው ፈተና ዛሬ ላይ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ቢሆኑም፣ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ግን ከልባችን ጓዳ ተጠርገው ያልወጡና በዕለት ተዕለት ሕይወታቸን አብዝተን የምናዳምጣቸው፤ የትናንት ያህል የማንነታችን መገለጫ፤ የሰውነታችን ማሳያ አሻራዎቻችን ናቸው።
ዛሬእንደ አገር የኑሮ ፈተና ውስጥ ባለንበት በዚህ ወቅት እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያን እራበኝ ለሚል ወንድማችን ከጉድለታችን ለማካፈል፤ ተቸገርኩ ለሚለው ወገናችን ካለችን ከፍለን ለመስጠት፣ የታመመ ጎረቤታችን ባለችን አቅም ለመጎብኘት፣ እግዚአብሔር ይማርህ ብለን የውስጣችንን በጎ መሻት ለመግለፅ አሁንም እየተተገበረ ያለ ማንነት አለን።
እንደ ሕዝብ የመጣንባቸው ውጣ ውረዶች እና ያስከፈሉን መራራ ዋጋ እነዚህን ማህበራዊ እሴቶቻችን የመሸርሸር አቅም አልነበራቸውም፤ ከዚህ ይልቅ በእያንዳንዱ ፈተና እየጠሩ አሁን ላይ ላለንበት ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር አቅም ሆነውናል። አገርም እንደ አገር በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ጠንክራ እንድትቆም ረድተውናል።
እነዚህን ከፍ ያሉ ማኅበራዊ እሴቶቻችን እንደቀደመው ትውልድ በተሻለ ማስተዋልና መረዳት ልንቀበላቸውና ተጨባጭ የሕይወት መርህ አድርገን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ልንተገብራቸው ይገባል። በተለይም አሁን እንዳለንበት ወቅት ሕዝባችን በፈተናዎች ለማለፍ ሲገደድ፤ ፈተናዎችን አልፎ ለመሻገር እነዚህን እሴቶቻችንን አቅም አድርገን መሰለፍ ይጠበቅብናል።
አባቶቻችን ትናንት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈው ዛሬ ላይ ያለችውን አገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፉልንን ማህበራዊ እሴቶችን ጠብቀው አቆይተውልናል፤ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን አሁን ያለንበት የሕይወት ፈተና እነዚህ እሴቶቻችን እንዲደበዝዙ ምክንያት ሊሆኑ አይገባም፤ እኛም ልንፈቅድ አይገባም።
እነዚህ እሴቶቻችን እንዲደበዝዙና መፍቀድ ማለት በመጪው ትውልድና በአገር ላይ ጥፋት እንደመፈጸም ማለት ነው። ትውልዱ በሕይወት ዘመኑ መንፈሳዊ እርካታ እና የሞራል ልእልና እንዳይኖረው ማድረግ፤ አሁን ዓለምን ክፉና እየተገዳደራት ላለው ራስ ወዳድነት አሳልፎ መስጠት ነው። ይህ ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ዛሬ ላይ ራስ ወዳድነት እያስከፈለን ካለው አገራዊ ዋጋ ብዙም ለመረዳት የሚከብደን አይደለም።
ዛሬ ላይ እኛን ያጋጠመን ፈተና ትናንት ላይ አባቶቻችን ካጋጠሟቸው ፈተናዎች የበለጡ የከበዱ አይደሉም ፤ እያንዳንዱ ትውልድ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ወደፊት ለመሄድ ባለው መሻት መጠን ፈተናዎች ያጋጥሙታል፤ አንዱ ከአንዱ የሚለየው የፈተናዎችን ምንነት ተረድቶ በሚኖረው ዝግጁነት ነው።
ይህ ዝግጁነት ውጤታማ የሚሆነው ከሁሉም በላይ ትውልድን እንደ ትውልድ የሚያሻግሩ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶቻችን ዘመንን እንዲዋጁ የሚያስችላቸውን፤ ማኅበረሰባዊ መስተጋብሮች በተሻለና በዳበረ መልኩ መቀጠል የሚችሉበትን አቅም ማጎናጸፍ ሲቻል ነው። ይህ ደግሞ ለዛሬውና ለነገው ትውልድ ስንል ያለማወላወል ልንተገበረው የሚገባ ዓቢይ ጉዳይ ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም