ትንሳዔን በይቅርታና በፍቅር
በመላ ክርስቲያን ወገኖቻችን በከፍተኛ ሃይማኖታዊ ሥርዓትና ሞቅ ደመቅ ባለ የበዓል ድባብ የሚከበረው የትንሳዔ በዓል የፊታችን ዕሁድ ይከበራል። ክርስቲያን ወገኖቻችን በዓሉን በተድላና በደስታ ለማክበርም ሽር ጉድ ማለቱን ተያይዘውታል። ሾላ፣ መገናኛ፣ 4 ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ፣ አዲሱ ገበያና የአፍሪካ ትልቁ የገበያ ስፍራ መርካቶ ሞቅ ደመቅ ብለው በሸማች ተጨናንቀዋል። ከበዓሉ ድባብ ጋር ተያይዞ ከአሁኑ መንገዶች እየተጨናነቁ ነው። የኤግዚቢሽን ማዕከልና ሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄዱ ባዛሮችም ሞቅ ደመቅ ብለው ሸማችና ሻጭን እያገበያዩ ይገኛሉ።
የኅብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅም ፖሊስና የጸጥታ ኃይሎች ከወትሮው በተለየ ዝግጅት ጥበቃቸውን አጠናክረው ይታያሉ። ወደ ክፍለ ሀገር በመጓዝ በዓሉን ከዘመድ ቤተሰብ ጋር ለማክበር በርካታ ተጓዥ ወደክልሎች በመትመም ላይ ነው። ቃሊቲ መርካቶም ሆነ ላም በረት የሚገኙ የአውቶቡስ መናኸሪያዎች መጨናነቅም ይህንኑ ያሳያል። ምዕመኑ በጾምና በጸሎት ሁለት ወር ያህል ጊዜ አሳልፈዋልና በዓሉን በደስታናበተድላ ማክበራቸው ይበል የሚሰኝ ነው። ይሁንና ከተድላና ከደስታው በሻገር ይህን ታላቅ በዓል ስናከበር ልናስተውላቸው የሚገቡ ታላላቅ ጉዳዮች እንዳሉ ግን ይሰማኛል። እንደሚታወቀው ክርስቲያኖች የትንሳዔ በዓልን የሚያከብሩት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ከዘላለም ቅጣት ለመታደግ ሲል ወደ ምድር ወርዶ፣ ተምሳሌታዊ ኑሮ ኖሮ፣ በመጨረሻም መከራ ተቀብሎ፣ ተተፍቶበት፣ ተሰድቦና ተዋርዶ በመስቀል ላይ ሞትን ሞቶ በሾስተኛውም ቀን ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን ምክንያት በማድረግ ነው።
በእኔ እምነት ጌታ ኢየሱስ በትንሳዔው ለሰው ልጆች ህይወት መመሪያ የሚሆኑ ሦስት ታላላቅ ተግባራትን አከናውኗል። እነዚህም፡-1ኛ. ፍቅር ከትንሳዔ በዓል የምንማረው ቀዳሚ ነገር ፍቅርን ነው። ምክንያታም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ላይ እንዲሞት እንዲዘበትበትና እንዲሰቃይ የሆነው ለሰው ልጆች ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ነውና! ስለሆነም ከዚህ ተምረን የትንሳዔውን በዓል ስናከብር ለወገኖቻችን ፍቅርን በማሳየትና ለራስ ብቻ ከመኖር ወጥተን ለአገርና ለህዝብ መኖርን በተግባር በማሳየት መሆን ይኖርበታል። ፍቅር በተግባር የሚገለጽ ነገር ነውና!
2ኛ. ይቅርታ ከትንሳዔ በዓል የምንማረው ሌላው ትልቅ ቁም ነገር ይቅርታ ማድረግን ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለገፈተሩት፣ ላንገላቱትና ለሰቀሉት በመጨረሻ የተናገረው ነገር ቢኖር የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው የሚል ነው። ከዚህ መማር ያለብን ትልቅ ነገር ይቅርታን የህይወታችን መመሪያ ማድረግን ነው። በግለሰብ፣ በቡድንም ሆነ በአገርና በህዝብ ደረጃ የጥላቻ ትርክቶችና የኋላ ጥፋቶችን በመምዘዝ መናቆሩ አሳልፎ ለበላተኛ ይሰጠን ይሆናል እንጂ ምንም አያተርፍልንም። የሚበጀውና የሚሻለው ነገር ከትንሳዔው ተምረን በደል ቢኖርም እንኳን በይቅረታ በመዝጋት መጪውን ጊዜያችንን ብሩህ ማድረጉ ነው። ከበቀልና ከቂም ያተረፈ ማንም የለምና!
3ኛ መስዋዕትነት ለእውነተኛ ዓላማና ለህዝቦች ድህንነት ሲባል መስዋዕትነትን መክፈል ከትንሳዔ በዓል የምንማረው ሌላ ትልቅና አስፈላጊ ነገር ነው። ጌታ ኢየሱስ የሰው ልጆችን የማዳን ትልቅ ዓላማን ይዞ ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ መስቀል ሞት ድረስ መስዋዕትነትን ከፍሏል። ይህን ተምሳሌታዊ ድርጊት በመመልከትም እኛም ለአገራችን ሉዓላዊነት፣ ዕድገትና ለህዝባችን ደህንነት የጊዜ፣ የሀብትና አስፈላጊም ሲሆን እሰከ አካልና ህይወት የሚደርስ መስዋዕትነት መክፈል ግዴ ታችን መሆኑን መገንዘብ ያሻል።
አገር መውደድ የሚገለጸው በመልካም ሥራና አስፈላጊ ሲሆን በሚከፈል መስዋዕትነት ነውና። በአጠቃላይ መላ ክርስቲያኖች በድምቀት ልናከብረው እየተዘጋጀን ባለው የ2011 የትንሳዔ በዓል ፍቅርንና ይቅርታን መላበስ እንዲሁም ለሀገርና ለህዝብ ደህንነትና ብልጽግና የሚፈለግብንን መወጣትን ከትንሳዔ በዓል በመማር ሊሆን ይገባል እላለሁ! መልካም የትንሳዔ በዓል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011
ኤዶሚያስ ከካንዛቺስ