ባሳለፍነው ዓመት አልፎ አልፎ በሀገሪቱ የተስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች አደብ ገዝተው ተማሪውም ወደ ትምህርት ቤት፣ መምህሩም ወደ ማስተማሩ ፣ ነጋዴው ወደ ንግዱ ፣ ገበሬውም ወደ እርሻው ሌላውም እንዲሁ ወደ ሙያው ፊቱን መልሶ የተረጋጋ ኑሮ መኖር አለበት። በ2016 ዓ.ም ያየነውንና የሰማነውን ችግር ለማስቀረት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት። ችግሮች ለምን ተፈጠሩ ላይባል ይችላል ነገር ግን የተፈጠሩ አለመግባባቶች እንዴት መፍትሄ ማግኘት አለባቸው ብሎ በሰከነ መልኩና በማስተዋል መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ችግሮችን ለመፍታት በሰለጠነ መልኩ መቀራረብ ፣መነጋገርና መግባባት ይገባል። ሰጥቶ መቀበል ለሁሉም ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ነው። ሀገር የምታድገው ፣ ልማት እና ኢንቨስትመንት የሚስፋፋው ፣ ቱሪስቱ ወደ ሀገራችን የሚጎርፈው ፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እያበበ የሚሄደው በጋራ ስለሀገርና ሕዝብ በማሰብ፣ በመተባበርና ልዩነት አጥብቦ አንድነትን በማጠናከር ነው። ለዚህ ደግሞ ለሰላማችን አብዝተን መሥራት አለብን።
የውስጥ ችግሮቻችን የሰፉና ሀገር የተዳከመች በሚመስላቸው ወቅት የሀገራችንን ዕድገት የማይመኙ የውጪ ኃይሎች ሁሉ ክንዳቸውን ሊያሳዩን ይሞክራሉ። እኛው በከፈትነው መስኮት ውስጣችንን አጮልቀው በመመልከት ሊከፋፍሉን ያስባሉ። አንዳንዶች ታሪካዊ ጠላቶች በቀጥታ አንዳንዶች ደግሞ በእጅ አዙር ሊያጠቁን ያስባሉ፤ያቅዳሉ። ትብብርና ኅብረት ይፈጥራሉ። ይሄ ከዚህ በፊትም በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ታይቷል፤ አሁንም እየታየ ነው። ይህንን የውጪ ጠላት ሀሳብና ዕቅድ ማክሸፍ የምንችለው ታዲያ በራሳችን የውስጥ ኃይላችንንና አንድነታችንን ማጠንከር ስንችል ነው። ለሰላማች ዘብ መቆም ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የምንሰጠው ሥራ መሆን አለበት። በአዲሱ ዓመት መጥፎ ሥራን በማስወገድና መልካሙን በማጠናከር የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል ያስፈልጋል። ሰፊ ቁጥር ያለው ሥራ አጥ ዜጋ የሥራ ዕድል ባለቤት የሚሆነው በሁሉም አቅጣጫ በመላ ሀገሪቱ ተንቀሳቅሶና ያለ ስጋት ሰርቶ መኖር ሲችል ነው። ለዚህ ደግሞ የሰላም ዋጋው ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ ከ90 ከመቶ በላይ የአማኒያን ሀገር መሆኗ ይታወቃል። አብዛኛው ሕዝብ እምነት ያለው እምነቱንና ሃይማኖቱን የሚያከብር ነው ። ክርስቲያን ፣ ሙስሊም ዋቄፈታ ሳይባባል ተከባብሮና ተፋቅሮ የኖረና የሚኖር ሕዝብ ነው። ያለው ለሌለው በመስጠት፣ በመጠያየቅና በመረዳዳት የኖረ ሕዝብም ነው። በችግር ወቅት፣ በሀዘንና በደስታ ሰዓት ሁሉ አለሁ ብሉ ከጎን የሚቆም፤ተካፍሎ የሚበላ ላጣ የሚመጸውት ጭምርም ነው። በየትኛው የእምነት ተቋም መረዳዳት አንዱ የሃይማኖታዊ አስተምህሮ ነው። በጎ ሥራ መሥራት በጎ አድራጎት ደግሞ ከተደረገለት ሰው በላይ ደስታን የሚሰጠው በጎ አድራጎት ላደረገው ወገን ነው። የተቸገሩ ወገኖቻችንን አለንላችሁ ብሎ ከፊት መቆም በዓላትን በደስታ አሳልፉ ብሎ ከተረፈን ላይ ሳይሆን ካለን ላይ ማካፈል ለራሳችን ከምናገኘው ሀሴት በላይ የፈጣሪን ትዕዛዝ መፈጸም ስለሆነ እርካታውም ከፍ ያለ ይሆናል።
በበዓላት ወቅት መረዳዳቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ችግረኞች መረዳት ያለባቸው እንደ ችግራቸው ስፋትና ጥልቀት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መሆን አለበት። በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ብዙዎች ተጎድተዋል። ያዘኑትን ማጽናናት የተፈናቀሉትን ደግሞ አለንላችሁ ማለት ይገባል። በአዲሱ ዓመት ከመጥፎ አስተሳሰቦች በመራቅ መልካም መልካሙን ማጠናከር ያስፈልጋል። ለሀገራችን ሰላም ተግተን መቆምም ይጠበቅብናል።
2017 ዓ.ም ሰቆቃ የማንሰማበት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት፣ የመከባበርና የመረዳዳት እንዲሁም የብልጽግና ዘመን እንዲሆንልን ሁላችንም ለሰላማችን አብዝተን ዘብ መቆም ይገባናል!
አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም