ቀናትን ወልደው፤ቀናት በወራት ተቀምረው አዲስ ዓመት ላይ ደርሰናል። ያለፈው አሮጌ ዓመትም ቦታውን ለአዲሱ ዓመት አስረክቦ ከነክፋትና ደግነቱ ላይመለስ ተሰናብቷል። አሮጌው ዓመትም በበጎም ሆነ በክፉ አሻራውን አሳርፎ አልፏል።
አዲስ የገባው 2017 ዓ.ም ያለ2016 ዓ.ም እውን ሊሆን አይችልም። በ2016 በበጎም ሆነ በክፉ የተከሰቱ ጉዳዮች በ2017 በበጎም ሆነ በክፉ አሻራ ማሳረፋቸው አይቀሬ ነው። ስለዚህም በ2016 ዓ.ም እንደሀገር ያገኘናቸው ድሎችና ያጋጠሙን ተግዳሮቶች አዲስ በያዝነው ዓመት ላይ የራሱን አሻራ አሳርፎ አልፏል።
እንደ ሀገር የነበሩን ጥንካሬዎች ለመጪው ጊዜ እርሾ ሆነው ያበረቱናል፤ከድክመቶቻችንም ተምረን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ስንቅ ሆነው ያገለግሉናል። በአጠቃላይ ጥንካሬዎቻንን አጎልብተን፤ድክመቶቻችንን ቀርፈን የተሻለች ሀገር እንድትኖረንም በር ይከፍታል።
የሸኘነው 2016 ዓ.ም እንደሀገር በርካታ ውጤቶች ያገኘንበትና በዚያው መጠንም የተፈተንበት ዓመት ነው። በ2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ጎልታ የወጣችበት፣ በግብርና ምርት ውጤት ያመጣችበት፣ የድሆችን እንባ ያበሰችበትና ሰላምንም ለማጽናት ብዙ ርቀት የተጓዘችበት ዓመት ነው።
በ2016 ዓ.ም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግባለች። ከ300 ሚሊዮን ኩንታል ብዙም ዘሎ የማያውቀውን ዓመታዊ የምርት መጠን ወደ 600 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ ተችሏል። በቡና የውጭ ንግድ ግብይትም 1ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ የጻፈችበት ዓመት ነው። በስንዴ እና በሩዝ ምርት የተገኘው ስኬትም ለመጪው ዘመን ተስፋ የሚሰጥ ነው።
በ2016 ሀገራችን ካስመዘገበቻቸው ስኬቶች አንዱ በዓባይ ግድብ ዙሪያ የታየው አፈጻጸም ነው። በተሠራው ሥራም ተጨማሪ ሁለት ተርባይኖች ወደ ኃይል ማመንጨት ተግባር ገብተው ከሀገር አልፎ የጎረቤት ሀገራትንም በብርሃን ማድመቅ ችለዋል።
ነሐሴ 17 ቀን 2016 ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ኢትዮጵያን በአረንጓዴ አሻራ ያለበሱበት ቀን ነው። በአንድ ጀንበር ከ600 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል በጋራ ታሪክ ጽፈዋል። ይህም ስኬት 2017 አዲስ ዓመትን በተስፋ እንድንቀበለው አድርጎናል።
በኮሪደር ልማት ፣ የባህር በር፣ በዲፕሎማሲው መስክ የተገኙ ውጤቶችም የጥንካሬዎቻችን መሳሪያዎች ናቸው። ሆኖም ክእነዚሁ ጥንካሬዎቻችን ጎን ለጎን
ጦርነት፣ግጭት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ድርቅ፣ የመሳሰሉት ችግሮች ኢትዮጵያን ፈትነዋታል። አለመተማመን፣መወነጃጀል፣ጥላቻና ቂምም የፖለቲካችን አንዱ መለያ ሆኖ አብሮን ቆይቷል። ይህም ሁኔታ በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጦርነት እንዲቀሰቀስ፣ግጭት እንዲበራከት ፣ ሞትና የንብረት ውድመት እንዲከሰት አድርጓል። በዚህም በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ተሰደዋል።
ይህ ታሪክ ግን አንድ ቦታ ማብቃት አለበት። የህዳሴ ግድብን የገነቡ ክንዶች፤በአንድ ጀንበር ከ600 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን የተከሉ እጆች፤የተራቡና የታረዙ ወገኖችን የታደጉ ስብናዎች ለግጭትና ለጦርነት ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። በ2017 በቃ ልንላቸው ይገባል።
ስለዚህም የመገጫጨት፣የመጠፋፋት እና የመገዳደል ታሪካችን ሊዘጋ ይገባል። አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፣ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው። ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል። የስልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነውና። በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው።
ስለሆነም የታሪካችን አንዱ ክፋይ ሆኖ ዘመናትን የተሻገረውን ጦርነትና ግጭትን ለማስወገድና የተረጋጋች፤ ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማውረስ ሀገራዊ ምክክሩ ይዞ የመጣውን ዕድል በአዲሱ ዓመት ልንጠቀምበት ይገባል።
አዲስ ዘመን መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም