ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሉዓላዊነታቸውን አስጠብቅውና አስከብረው ዘመናትን ካስቆጠሩ ጥቂት የዓለም ሀገራት አንዷ ነች። ሉዓላዊነታችንን በማስከበር ሂደትም ከፍተኛ መስዋእትነት የጠየቁ አውደ ትግሎችን በየዘመኑ አካሂደናል። በየአውደ ወጊያው ባለድል የሆንበት አይበገሬ የጀግንነት መንፈስም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ አሁን ላይ የነጻነት ተምሳሌት አድርጓታል።
ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘው ከአትንኩኝ ባይነት የሚመነጨው የነጻነት ገድል ትርክቷ፤ በየዘመኑ ለሚመጡ ትውልዶች የማንነት እና የብሄራዊ ክብር፤ ከመሆን ባለፈ ስለ ነጻነት ለተደረጉና እየተደረጉ ላሉ ሕዝባዊ ትግሎች መንፈሳዊ መነቃቃት እና የአሸናፊነት ሥነልቦና በመሆን እያገለገለ ነው።
ይህም ሆኖ ግን እንደሀገር የመጣንበት ፤ የድህነት እና የኋላ ቀርነት ጉዞ በብዙ ተጋድሎ ያገኘነውን ነጻነት እና ከነጻነታችን የሚመነጨውን ብሔራዊ ክብራችንን እና ማንነታችንን አጉድሎት ቆይቷል። በዓለም አቀፍ አደባባይ አንገታችንን ከማስደፋት ባለፈ ተመጽዋች /ጠባቂ አድርጎንም ቆይቷል።
ድህነት እና ኋላ ቀርነት ለብሔራዊ ክብር ትልቅ ችግር በሆነበት፤ ጠባቂነት እና ተመጽዋችነት ብሔራዊ ክብርን በሁለንተናዊ መንገድ በሚፈታተንበት በዚህ ዘመን፤ ድህነታችን እና ኋላ ቀርነታችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ትናንቶችቻን ብቻ ሳይሆን ዛሬን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እንድናልፍ ፤ በነገዎቻችንን እርግጠኛ እንዳንሆን አድርጎናል።
ዛሬ ላይ፤ ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን በሚል ሀገራዊ መነቃቃት ከዚህ ብሔራዊ ክብርን ከሚያጠለሽ ሀገራዊ ፈተና ለመውጣት እና የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር ሰፋፊ ጥረቶች እያደርን፤ በተስፋ የተሞሉ ስኬቶችን እያስመዘገብን ነው። በዚህም ነገዎቻችንን ከትናንት ይልቅ ብሩህ እና በተስፋ ተጠባቂ እየሆኑ ነው።
የእስካሁን የልማት ጉዟችን ፤ ትናንት ለነጻነታችን በቁርጠኝነት ተንቀሳቀስን ፤ ነጻነታችንን ማስከበር እና የነጻነት ተምሳሌት መሆን እንደቻልነው ሁሉ ፤ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ መንቀሳቀስ ከቻልን ለዘመናት ብዙ ዋጋ ያስከፈለን ድህነት እና ኋላቀርነት ከኛ አቅም በላይ ሊሆኑ እንደማይችል በተጨባጭ ማየት እንድንችል ዓይናችንን የከፈተ ነው።
ለዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለፉት ሦስት ዓመታት እውቅና ያገኘንባቸው በተለይም በግብርናው ዘርፍ የበጋ የመስኖ የስንዴ ልማትን ጨምሮ በሩዝ ልማት ፤ በሌማት ትሩፋት እና በኩታ ገጠም እርሻ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች፤ በተለይም በምግብ እህል ያለብንን ጠባቂነት መሻገር የሚያስችል ጅማሬ ላይ ስለመሆናችን ማሳያ ነው።
የአንድነታችንና ብሔራዊ ክብራችን አንዱ መገለጫ የሆነውን የዓባይን ግድብ፤ ከውስጥ እና ከውጪ ፈተናዎች ታድገን ለፍጻሜ ያደረስንበት ቁርጠኝነት ፤ በቱሪዝም ዘርፍ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ያሉ እና የተገነቡ ፕሮጀክቶች ፤ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማነቃቃት ኢትዮጵያ ታምርት በሚል መሪ ቃል እየሄድንበት ያለው የመነቃቃት ጉዞ፤ በልማት ብሔራዊ ክብራችንን ሙሉ ለማድረግ የጀመርነው ጥረት ስኬት ማሳያ ናቸው።
ባለንበት ዘመን ድህነትን እና ኋላቀርነትን ተሸክሞ፤ እነሱ በሚፈጥሩት ፈተና ጎብጦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነትን በመፍጠር ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የሚቻል አይደለም። ብሄራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በኢኮኖሚ አቅም መግዘፍ እና ከጠባቂነት መውጣት፤ ለዚህ የሚሆን ብሔራዊ መነቃቃት መፍጠር የግድ ነው።
በርግጥ ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ድህነት እና ኋላ ቀርነት የብሔራዊ ክብራችን ተግዳሮት እንደሆነ ተረድቶ ይኸንን ለመሻገር ከፍ ባለ መነቃቃት እየተንቀሳቀስን ያለበት ወቅት ነው ። ለዚህም ሀገራችን በብዙ አስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥ በነበረችባቸው ወቅቶች ሳይቀር ያስመዘገበችው እና እያስመዘገበች ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ተጨባጭ ማሳያ ነው።
አሁናዊ የልማት መነቃቃታችን እንደሀገር ብሔራዊ ክብራችንን ሙሉ ከማድረግ ባለፈ ከህልውናችን ጋር የተያያዘ ነው፤ የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄም ነው። ድህነት እና ኋላቀርነት ሊፈጥሩት ከሚችሉት ጫና እና ጫናው እንደሀገር ሊያመጣ ከሚችለው ውስብስብ ችግሮች ራስን የማሻገር ወይም በችግሮቹ ተጠላልፎ የመውደቅ ምርጫ ነው።
ለዚህም ነው በዘመናት መካከል ውድቀታችን የሚሹ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ ሌሎች ኃይሎች ልማታችንን ለማስተጓጎል ሌት ተቀን የሚሠሩት፤ ያላቸውን አቅም በሙሉ ተጠቅመው ከልማት ጉዟችን ሊያስተጓጉሉን እየተጉ ያሉት። እኛም ከልማታችን ላይ ዓይናችንን ሳናናሳ ሴራቸውን እና የጥፋት ተልእኳቸውን ለማክሸፍ በቁርጠኝነት የምንሠራው!
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም