በተያዘው ዓመት ህዳር ወር ላይ እንዲህ የሚል ዜና ከገቢዎች ሚኒስቴር ተደመጠ፤ “በኢትዮጵያ ህገ ወጥ የገንዘብ አዘዋዋሪን በቁጥጥር ስር ለማዋል ለ3 ሰዓታት የበረረ አውሮፕላን ተመልሶ እንዲያርፍ ከተደረገ በኋላ ግለሰቧ በቁጥጥር ስር ዋለች፤…የአየር መንገዱ የፍተሻ እና የጉምሩክ ሠራተኞቹ በጋራ ሻንጣውን ሲፈትሹም በውስጡ 6 ሺ 170 ፓውንድ፤ 33 ሺ 115 ዩሮ እና 1 ሚሊዮን 264 ሺ 975 የኢትዮጵያ ብር አግኝተዋል።” ይህ ክስተት መንግሥት ህገ ወጥ ገንዘብንና አዘዋዋሪዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርገው አንዱ ጥረት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በተጨማሪም በየኬላው እና በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በየጊዜው በቁጥጥር ስር የሚውለው ገንዘብ እየጨመረ መምጣቱን አሁንም በየጊዜው ከገቢዎች ሚኒስቴር ከሚሰጡ መግለጫዎች መረዳት ይቻላል። በዚህ ወንጀለኛን አሳዶ በመያዝ ጥረት መንግሥትን አለማመስገን አለማድነቅም አይቻልም። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአደንዛዥ ዕጾች እና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቢሮ መረጃ መሰረት፤ በዓለም ላይ በዓመት 1 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ዶላር ገንዘብ በህገወጥ መንገድ ይንቀሳቀሳል።
በአገር ውስጥ እየተካሄደ ያለው ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርም የዚህ አካል አይደለም ማለት ስህተት ይሆናል። ይህንን ዓለም አቀፍ ወንጀል መከላከል የሚቻለው ደግሞ፤ ዓለም አቀፍ መረጃን እና ማስረጃን እንዲሁም ከወንጀለኞቹ እኩል የሚገዳደር ብልሀትና መረብ በመዘርጋት ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት። አንድ ቦሌ አሊያም ኬላዎች ላይ ብቻ ፖሊስ በማቆም ወንጀሉን ለመከላከል መሞከር ከሰፊው ባህር ዓሣን በመንጠቆ ለማጥመድ የመሞከር ያህል ነውና።
የህገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ምንጩ በአንድም በሌላም ዝርፊያ ነው። ግለሰቦች በተለያየ መንገድ በህገ ወጥ መንገድ ያካበቱትን ገንዘብ በውጭ አገር ገንዘቦች ከጥቁር ገበያ በመቀየር ከአገር ለማሸሽ በርትተው ይሠራሉ፤ ይህ ደግሞ በትላልቅ አስመጪዎችና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀር የሚከወን ነው። በአንድ ወቅት በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት የመንግሥት ባለስልጣን መኖሪያ ቤት የተገኘው 26ሺ የአሜሪካ ዶላር እና 19ሺ ዩሮ የአውሮፓ ሕብረት የመገበያያ ገንዘብ፤ በተመሳሳይም የመሬት አስተዳደር ሠራተኛ በሆነች ግለሰብ ቤት የውሃ ታንከር ውስጥ የተገኘው ረብጣ ገንዘብ ጥሩ ማሳያዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
ስለሆነም የመንግሥት ዓይኖች ከኬላዎችም ተሻግሮ መፈተሽ ያለባቸውን ጓዳዎች ሁሉ ሊፈትሽ ይገባል። አዲስ ዘመን ቅዳሜ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ባገኘችው መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ከተሞች የሚስተዋለው የውጭ ሀገራት ገንዘብ ህገወጥ ምንዛሬ በትላልቅ አስመጪዎች እና በባንክ ማናጀሮች ዋነኛ ተዋናይነት የሚመራ መሆኑን አረጋግጣለች። ይሄ ከድህነት አረንቋ ለመውጣት እየጣረ ላለ አገር እና ህዝብ ትልቅ መርዶ ነው። በተለይ በሶማሌ ክልል ቶጎ ውጫሌ የሚገኙ 16ቱም ባንኮች በህገወጥ የዶላር ምንዛሬ ውስጥ እንደሚሳተፉ መረጃ አለኝ ብሏል ፖሊስ። በዚህ ደረጃ የሚታወቅ ወንጀልን ከስር ነቅሎ ለመጣል መንግሥት ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት ሊሠራ ይገባዋል።
በኢትዮጵያ ማንኛውም የውጭ አገር ገንዘብ የመመንዘር ኃላፊነት ያለው ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ውክልና የተሰጣቸው ባንኮች ብቻ እንደሆኑ በባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000ተደንግጓል። አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ከ10 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ሕግ ያዛል። ይሁን እንጂ ይሄን ተላልፎ የተገኙ ግለሰቦች ስለመቀጣታቸውና ቅጣቱን ግልጽ አድርጎ ለማስተማሪነት ሲውልም አይታይም። በዚህም ምክንያት ጭምር ይመስላል ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ በመንግሥት መዋቅር እና ባንኮች ድረስ ሊዘልቅ ችሏል። ስለሆነም ስለ ችግር ብቻ እየተወራ መፍትሔ ዘላቂ መፍትሔ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር አንዱ መነሻው ጥቁር ገበያ ነው።
የጥቁ ገበያ ተዋንያን ደግሞ ከላይ እስከ ታች ያሉ ናቸው ብሏል ፖሊስ። ስለሆነም የታቹን ብቻ ማሳደድ ዋጋ የለውም። እሱም ቢሆን አንድ ሰሞን ዘመቻ በማድረግ ጥቁር ገበያን አጠፋለሁ፤ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እገታለሁ ማለት ዘበት ነው። መንግሥት በህገ ወጥ መንገድ ካገር የወጣን ገንዘብ ለማስመለስ አገራት ቃል እንደገቡለት ይፋ ያደረገው ጉዳይም የት እንደደረሰ የሚታወቅ ነገር የለም።
ይህ ግን ከዳር ቢደርስ ኖሮ የወንጀለኞችን መዳረሻ ማክሰም ስለሚሆን ጭምር ለወንጀሉ አንድ መፍትሔ ይሆን ነበር። ይህ ባለመሆኑ ግን ዛሬም ድረስ ለአገራችን አንድ ዓይን የሆነውን የውጭ ምንዛሬ በማንኪያ እየለመንን ጭምር እያመጣን በጆንያ ማሸሹ ቀጥሏል። ስለሆነም መንግሥት የወንጀሉን ተዋንያንና ገበያውን ያውቃል፤ የቀረው ዕርምጃውን ከአንጀት ማድረግ ነውና ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት ይሥራ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011