ጤና ይስጥልን አንባቢዎቻችን እንደምን ከረማችሁ? መንትዮቹ የዘመን ሀኪሞች ነን። ለዛሬ በአዲስ ዘመን ቅዳሜ ያዘጋጀነውን የጤና መረጃ እናካፍላችኋለን። እንደተለመደው ለዛሬ በጨጓራ ህመምና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ እናተኩራለን።
የጨጓራ ህመም (መግቢያ)
ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ደጋግመው ከሚጠቁበት ወይም በተደጋጋሚ ከሚያሳዩት የህመም ምልክቶች መካከል የጨጓራ ህመም ይጠቀሳል። የጨጓራ ህመም እድሜን፣ ፆታን እንዲሁም ዘርን ሳይለይ የሚከሰት የህመም አይነት ነው። እርግጥ ነው አንዳንድ ለጨጓራ ህመም መንስኤ የሆኑ ህመሞች ወይንም ሁኔታዎች ከቦታ ቦታ ወይም ከእድሜ እድሜ ይለያያሉ። በአጠቃላይ ግን የጨጓራ ህመም በዓለማችን እንዲሁም በሀገራችን በስፋት ሰዎች ወደ ጤና ተቋም እንዲሄዱ ከሚያደርጋቸው ህመሞች ወይንም ምልክቶች አንዱ እና ዋነኛው ነው።
የጨጓራ ህመም እና ምልክቶች የጨጓራ ህመም የብዙ ምልክቶች ጥርቅም ወይም ስብስብ ነው።የጨጓራ ህመምን ለመግለፅ ከምንጠቀምባቸው ምልክቶች ውስጥ፡- Ø የምግብ ያለመፈጨት ስሜት Ø የሆድ የላይኛው ክፍል መነፋት እንዲሁም የህመም ስሜት Ø የማቅለሽለሽ ስሜት መኖር እንዲሁም አልፎ አልፎ ማስታወክ Ø ከምግብ በኋላ የሚኖር ያልተለመደ ግሳት Ø የማቃር ስሜት ( የመቃጠል ስሜት ) ናቸው።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ብዙውን ጊዜ ምግብ ከበላን በኋላ የሚከሰቱ ናቸው። በአንዳ ንድ የህመም አይነቶች የሚከሰቱ የጨጓራ ህመም ምልክቶች ምግብ በምንወስድበት ጊዜ የሚሻሻሉ ይኖራሉ። የጨጓራ ህመም መምጫ ምክንያቶች የጨጓራ ህመም ወደ 25በመቶ የሚሆነው መምጫው የሚታወቅ ሲሆን የተቀረው 75በመቶ የሚሆነው ምክንያቱ የማይታወቅ ነው። ምክንያታቸው ከሚታወቁ፤ የጨጓራ ህመምን ከሚያመጡ ችግሮች ( የህመም አይነቶች መካከል ) እነዚህ ይጠቀሳሉ።
- የጨጓራ ቁስለት (Peptic Ulcer Disease) ፡- አንዱ ነው።የዚህ ቁስለት በመጀመሪያው የአንጀት ክፍል ወይም በእራሱ በጨጓራ ግድግዳ ላይ የሚፈጥር ቁስለት ወይም መላጥ ነው። የዚህ ህመም መገለጫዎች መካከል በመሀለኛው የሆድ ክፍል የሚኖር ህመም፤ የቅባታማ ምግቦች አለመስማመት፤ የሆድ መነፋት፤ የምግብ አለመፈጨት፤ አልፎ አልፎ የሚኖር የማቅለሽለሽ እና የማስታወክ ስሜት ናቸው። ለጨጓራ ቁስለት መፈጠር በዋነኝነት ከሚጠቀሱት መካከል የጨጓራ ባክቴርያ ይጠቀሳል። ሌሎች ለህመም ማስታገሻ ብለን የምንወስዳቸው መድሀኒቶች ለምሳሌ ዳይክሎፌናክ፤ አይቡፕሮፊን (በተለምዶ አድቪል ተብሎ የሚጠራው)፤ እንደሜታሲን፤ አስፕሪን የተሰኙ መድሀኒቶች የጨጓራ ቁስለትን ከሚያመጡ መድሀኒቶች ይጠቀሳሉ።
- የጨጓራ እና የምግብ ቱቦ መውረጃ ካንሰር፡- የጨጓራ ህመም ወይም ምልክቶችን ከሚያመጡ ህመሞች ውስጥ ይመደባሉ። ምንም እንኳን ያልተለመደ እና በብዛት ባይኖሩም እነዚህ የካንሰር አይነቶች ረዘም ላለ ጊዜ የጨጓራ ህመም እና ምልክት ቢኖር ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት አስፈላጊውን ምርመራ እና ክትትል ማድረግ ይኖርብናል።
- ሌሎች ህመም፡- እንደ የቆየ የቆሽት ህመም፤ የጉበት ህመም፤ የሀሞት ከረጢት ህመም፤ የስኳር ህመም፤ቋሚ የሆነ የኩላሊት ስንፈት፤ የጨጓራን ህመም ምልክትን ከሚያሳዩ እንዲሁም ሊያመጡ ከሚችሉ ህመሞች ውስጥ ይገኛሉ። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የጨጓራን ህመም ወይም ምልክት ከሚያመጡ መካከል 75በመቶ የሚሆነው ምክንያቱ ያልታወቀ (Functional Dyspepsia) የምንለው ነው። ይህን የምንለው ደግሞ የሚከተሉትን ምልክቶች ለሶስት ወይም ከዚያ በላይ የቆየ እንደሆነ ነው። ከምግብ በኋላ የሚኖር የመንፋት ስፋት፤ ቶሎ የመመገብ ስሜት፤ የሆድ የላይኛው ክፍል ህመም ወይም የማቃጠል ስሜት መኖር ናቸው። ከነዚህም በተጨማሪ ምንም አይነት የጨጓራ አካላዊ ጉዳት የሚያሳይ መሆን አለበት።ይህ ካልሆነ (Functional Dyspepsia) በማለት አስፈላጊውን ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል የበዓል ምግብ እና ጨጓራ ህመም ምልክቶች እንደሚታወቀው በሀገራችን በዓላትን አስከትለን የምናዘጋጃቸው ምግቦች ከወትሮው የቅባት መጠናቸው እንዲሁም የቅመም መጠናቸው ከፍ ያለ ነው።
- እነዚህ የምግብ አይነቶች ካላቸው ከፍተኛ የሆነ የቅባት እና የፕሮቲን መጠን የተነሳ በሰውነታችን የምግብ የመፈጨት ሂደት ላይ ከፍተኛ እክል ይፈጥራሉ። በተለይ የፆም ወራት ሰውነታችን ከእነዚህ የምግብ አይነቶች በመራቁ እና በአንፃሩ ቀለል ያሉ እና በቶሎ ተፈጭተው እና ልመው በቀላሉ ወደ ሰውነት የሚዋሀዱ ናቸው። እነዚህ የምግብ አይነቶች ረዘም ላለ ጊዜ በምንመገብበት ጊዜ ሰውነታችን ይህንን የአመጋገብ ስርአት የተለመደ ሲሆን፤ ፆም ተፈቶ ወደ ቅባታማ እና የፕሮቲን ይዘቱ ከፍተኛ ወደሆነ ምግብ በምንሸጋገርበት ጊዜ ከላይ በጨጓራ ህመም ምልክቶች ውስጥ የተጠቀሱትን ምልክቶች እናሳያለን። ለዚህም መፍትሔ የሚሆነው የአመጋገብ ስርአታችን ወደዚህ ስርአት ቀስ በቀስ መላመድ ይሆናል። ይህንንም ለማድረግ የምንመገብበትን መጠን መቀነስ ያስፈልጋል። የጨጓራ ህመም ህክምና እና ቅድመ ጥንቃቄ የጨጓራ ህመም ራሱን ችሎ ወይንም የሌላ በሽታ መገለጫ ሆኖ ሊከሰት እንደሚችል ተመልክተናል። ከዚህ በመነሳት የጨጓራ ህመም ወይም ምልክትን በምንታከምበት ወቅት ሁለት አበይት ነገሮችን ማሰብ ያስፈልጋል። እነዚህም የጨጓራ ህመም ያመጣውን በሽታ (Underlying Cause) ማከም በመቀጠልም የጨጓራ ህመም ምልክቶችን ማከም ያስፈልጋል። ምልክቶቹን ለማከም ከሚረዱ የመድሀኒት ዘርፎች የአሲድ መጠንን የሚቀንሱ የተለያዩ የመድሀኒት ዘርፎች ያሉ ሲሆን፤ ምልክቱን ለማጥፋት ( ለመቀነስ ) ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ሌሎች የጨጓራን ግድግዳ በመሸፈን ከአሲድ አደጋ የሚከላከሉም የመድሀኒት ዘርፎችም ይኖራሉ። ከመድሀኒቶቹ ያልተናነሰ ምልክቶችን ከማጥፋት አንስቶ እስከ መከላከል (እንዳይባባስም ጭምር) ከሚደረጉ ቅድመ ጥንቃቄዎች መካከል የማይስማማን ምግብ ማስወገድ፤ ሲጋራ እና አልኮልን ማቆም፤ ምግብን ሰአትን ጠብቆ መውሰድ፤ ከበሉ በኋላ አለመተኛት፤ የሰውነት ክብደት መቆጣጠር፤ የመሳሰሉት ናቸው።