
እርሷ የወርቅ ምድሯ ሻኪሶ ልጅ ናት። ወርቁ እንዴት ዲዛይን እንደሚደረግ በልጅነቷ ምክንያት ባትረዳም ልዩ አርክቴክት መሆንን ትሻ ነበር። ያ ፍላጎቷ ደግሞ በተወለደችበት ቀዬ ውስጥ በተለያየ መልኩ ልምምድ ይደረግበታል። አንዱ እንደ ልጅነቷ ‹‹እቃቃ›› ለመጫወት በምታደርገው ግብግብ ላይ የሚገለጥ ነው። ሌላው ደግሞ እድሜ ለትምህርት ቤቷ ልዩ ተሰጥኦዋን የበለጠ እንድትሠራበት እድል ሰጥቷታል። በተለይም የተለያዩ ቅርጻቅርጾችን እንዲሠሩ ሲታዘዙ የእርሷን ያህል የሚሠራ አልነበረም። ይህ ሁኔታ ደግሞ ገና በልጅነቷ ጀምሮ የራሷን ገቢ የምታገኝ ልጅ እንድትሆን አስችሏታል። ለውድድር ሲባል ሌሎች ተማሪዎች እንደእርሷ አድርጋ እንድትሠራላቸው ይከፍሏት ነበርና።
በትምህርቷም ሆነ በቤት ውስጥ ሥራዋ ጎበዝና ተወዳጅ የሆነችውን ባለታሪካችንን ቤተሰቦቿ በብዙ መልኩ የሚኮሩባትና የሚደሰቱባት በመሆናቸው ‹‹ኩራት›› የሚል ስያሜን የያዘውን ስሟን አውጥተውላታል። ይህም በኦሮምኛ ‹‹ቦንቱ›› የሚለው ነው። ቦንቱ በዚህ ስያሜ መጠራቷ እጅጉን ያስደስታታል። በዚህም ዘወትር እንደስሟ የቤተሰቦቿ ኩራት ለመሆን ትተጋለች።
ቦንቱ በቃና ከወርቅ ምድሯ ሻኪሶ ጀምራ እስከ ሱልልታ በተማረችባቸው የግል ትምህርት ቤቶች ሁሌም ከሁሉም ተማሪ አንደኛ ነው የምትወጣው። በትምህርቷ ጎበዝ መሆኗ ደግሞ በተማሪዎችና መምህሮቿ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ማህበረሰብ ጭምር አስወድዷታል። በእርግጥ ለዚህ እድል ያበቋት ቤተሰቦቿ እንደሆኑ ታነሳለች። የተማሩና የመንግሥት ሠራተኛ በመሆናቸው ነጻነቷን ሰጥተው፣ የምትፈልገውን እያሟሉ አሳድገዋታል። በተለይም የአባቷ ነገር መቼም አይረሳትም። ፍላጎቷን ከዳር እንድታደርስ በብዙ ደግፈዋታል። ከእቃቃ ጨዋታ ጀምሮ አብረዋት እየሆኑ የተሻለች እንደሆነች በመንገር አበረታተዋታል።
በእናቷም በኩል ብዙ ነገሮች ተደርገውላታል። በተለይም ሴት ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ሊገጥሟት የሚችሉ ነገሮች በሚገባ ተነግረዋታል። ችግሮችን እንዴት መፍታት እንዳለባትም የሁልጊዜ አማካሪዋ በመሆንም ለእያንዳንዱ ፈተናዎቿ እልባት ይሰጣታል። ይህ በወኔና በነጻነት የተገነባ ማንነቷ ሁሌም የድልና የመፍትሄ ሰው እንድትሆንም አስችሏታል።
ቦንቱ ቤተሰብ በነጻነት አሳደገም አላሳደገም የሴት ልጅ ፈተና ፈርጀ ብዙ እንደሆነ ታምናለች። ለአብነትም እርሷ የገጠማትን ሃሳብ ታነሳለች። ሻኪሶን ለቀው ሱልልታ ሲገቡ ማህበረሰቡን በቀላሉ ለመልመድ ቸግሯት ነበር። ለዚህ ምክንያቱ ሴት መሆኗ እንጂ ሌላ አልነበረም። አለባበሷ ከተማ ቀመሱን የተከተለ በመሆኑ የሁሉም ሰው ዓይን ትስባለች፣ ወንዶች ሊያሳልፏት አይፈልጉም። ጾታዊ ትንኮሳውም በቀላሉ የምትጋፈጠው አልነበረም።
አንዳንዶች ደግሞ ወጣ ያለች ልጅ መሆኗን ይናገሩ ነበር። በዚህም ማህበረሰቡን መምሰል ስላለባት አለባበሷን ሙሉ ለሙሉ እንድትቀይር ሆናለች። ይህ ብቻ ግን በቀላሉ ጾታዊ ትንኮሳውን ሊያስቆመው አልቻለም። እናም መጋፈጥ ግዴታዋ ነውና በብዙ መንገዶች ባህሪዋ እንደሆነ ወደማሳመኑ ገብታለች። በተለይ ግን ረድቶኛል የምትለው በጣም ጎበዝ ተማሪ መሆኗን ነው።
ቦንቱ ‹‹ሴት ልጅ በገባችበት ሁሉ አሸናፊ መሆን ከቻለች አለቆቿን ትቀንሳለች፣ የሚያስጨንቃትንም ነገር ታስቀራለች። ማንም ሰው ጫና ሊያሳርፍባትም አይችልም›› የሚል አቋም አላት። ምክንያቱም እርሷ የደረጃ ተማሪ በመሆኗ ማንም እንዳናይገራት አድርጋለችና። በወቅቱም ‹‹እርሷ እኮ የዋህ ነች፣ በአለባበሷ አትመዝኗት›› የሚባልላት ሆና ነበር። እርሷ የነካችው ሁሉ ትክክል ነው እስከመባልም ደርሳለች።
የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክት የተመረቀችው ቦንቱ፣ በሃዋሳ እያለችም ከሴትነቷ ጋር ተያይዞ ችግሮች ገጥመዋት ያውቃሉ። አንዱ ከትምህርት ምርጫዋ ጋር ተያይዞ የገጠማት ነው። ብዙ ጊዜ የኢንጅነሪንግ ሙያን ሴቶች አይቀላቀሉምና እርሷና መሰሎቿ ሲገቡ በብዙ ተፈትነዋል። በርካቶችም ተባረዋል። ወንዶች ቢባረሩም ብዛት ያላቸው ግን ሴቶቹ ነበሩ። ከሁሉም የሚልቀው ደግሞ ከወንዶቹ የተሻለ ውጤት ኖሯቸው ሴቶቹ በብዛት ሲባረሩ ሲመለከቱ በፍራቻ ትምህርቱን ያቋረጡ ሴቶች መበራከታቸው ነው። ይህ ነገር በእርሷም ላይ ጫና ፈጥሮ እንደነበር አትዘነጋውም። ግን ነጻነቷና የተሰጣትን ‹‹እችላለሁ›› ባይነት በውስጧ ነበርና ትምህርቷን ከማቋረጥ ገድቧታል።
‹‹አንዳንዴ ጎበዝና ካጠቃላይ ክፍሎች አንደኛ እየወጡ ሄደው በሌሎች መበለጥን መመልከት እጅጉን ያማል። ‹‹አልችልም›› ባይነትን ያስከትላል። ፍራቻው ውስጥ ከቶም ተስፋ ያስቆርጣል›› የምትለው አርክቴክት ቦንቱ፣ እርሷ በዚህ ፍራቻ ውስጥ ወድቃ እንደነበር ታስታውሳለች። በተለይም ኮመን ኮርሶችን ወስደው የተለየውን የትምህርት ምርጫቸውን ተወዳድረው ከአለፉ በኋላ የገጠማት ነገር በቀላሉ የምትቋቋመው አልነበረም። የመረጠችው የትምህርት መስክ የልጅነት ሕልሟ ቢሆንም በትምህርቱ ዓለም ያገኘችው ግን የተለየ መልክ ይዞ ነው። ትናንት የተሻለች እንደሆነች እየተነገራት የሠራችው የዲዛይን ሥራ አይደለም ዛሬ ላይ የቀጠለው። ትምህርቱ በጣም ከባድ ልዩ ተመስጦን የሚፈልግና የለመደቻቸውን ብዙ ነገሮች የሚያስቀርባት ነው።
ከሰዎች ጋር እንደ ልብ ሻይ ቡና ለማለት አይቻልበትም። ሳይተኙ ማደርን ይፈልጋል። ግን በቀላሉ ነገሮችን ለማድረግ ስለተቸገረች መጀመሪያ ዓመት ላይ ያልጠበቀችውንና ያለመደችውን ውጤት አገኘች። በብዙዎችም ተበለጠች። ይህን ጊዜ የማይሆን ውሳኔ እስከመወሰን ደረሰች። የልጅነት ሕልሟን ትታ ሌላ ትምህርት መማር እንደምትፈልግና ከቤተሰቦቿ ጋር መሆን እንደምትሻ ተናገረች። ቤተሰቦቿም ‹‹እንደፈለገሽ›› አሏት። እርሷም ውሳኔዋን አጽንታ ፈተናዋን አጠናቃ ለእረፍት ቤተሰቦቿ ጋር መጣች። ስለሁኔታውም ተመካከረችበት። ይህ ምክክር ደግሞ ሃሳቧን አስቀየራትና ወደ ትምህርቷ መለሳት።
ቦንቱ ወደ አርክቲክትነት ትምህርቷ ስትመለስ ልታስወግዳቸው የምትፈልጋቸው በርካታ ነገሮችን ይዛ ነበር። አንዱ ዓላማዋ ትምህርትና ትምህርት በመሆኑ የትምህርት መስኩ የሚፈልገውን ነገር ለማሟላት በሁሉም ነገር መጣር ነው። ሌላው በእረፍት ጊዜዋ ራሷን ነጻ በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ መጠመድ ነው። በተጨማሪም ሕጻናት ተማሪዎችን ማስጠናት አከለችበት። ምንም እንኳን የዳበረ እውቀት ባይኖራትም ቀለል የሚሉ የዲዛይን ሥራዎችን በሰው በሰው እየተቀበለች መሥራት ነው። ይህ ደግሞ ከትምህርቱ ባሻገር ሙያውን በተግባር እንድታውቀው በብዙ መልኩ አግዟታል። ውጤቷ ላይም ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። ስትመረቅ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት መካከልም አንዷ ሆናለች።
ቦንቱ ከምረቃ በኋላ ወደ ቤተሰቦቿ አልተመለሰችም። የልጅነት ሕልሟ በሆነው የአርክቴክት ሙያ ብዙዎች ያውቋት ነበርና በሃዋሳ ከተማ በግሏ በመሥራት ወራትን አስቆጥራለች። የውስጥ ሕንጻ ሥራዎች ላይ ማማከር፣ የፎቅ ዲዛይኖችን መሥራትና ፕላን መንደፍ 3ዲ ላይ ሠርታለች። ይህ አቅሟ ደግሞ ቤተሰቧ ጋር ሆና ብትሠራበት የት ላይ እንደሚያደርሳት ታውቃለችና ወደ ሱልልታ አመራች። መጀመሪያ አካባቢ ተቀባይነት ባይኖራትም እያደር ብቃቷ እየታወቀ ሲመጣ ጥሩ የሚባሉ የውስጥና የውጪ ዲዛይኖችን፣ የፕላን ሥራዎችን ማከናወኑን ተያያዘችው።
ውሎ አድሮ ሥራዋን አስፍታ ስትሄድ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ዘለቀች። በግል ተቋም ውስጥ ተቀጥራ መሥራት ጀመረች። ግን ተቀጥሮ መሥራቱ እምብዛም እንደማያሠራት በማመኗ በግሏ ተሯሩጣ መሥራት ቀጠለች። ሙያው ትንንሽ ዲዛይኖች ካልሆኑ በስተቀር ቶሎ ውጤቱን የሚያሳይ አይደለም። የሚገለጥበትም ሁኔታ ከወራት እስከ ዓመታት ይወስዳል። ስለዚህም የኢንጅነሪንግ ሙያውንም በሚገባ ተምራዋለችና በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ላይ ለመሥራት ፈለገች። በዚህም የኢትዮያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለመሥራት አመለከተች። ከአምስት ወር ቆይታ በኋላም ተጠራችና ሥራ ጀመረች። አሁን በኮርፖሬሽኑ ውስጥ ፊውቸር ፕሮጀክት ማናጀርና ጁኒዬር አርክቴክት ነች። በተጨማሪም ተቋሙ ሥራ ከማሰማራቱ በፊት ስልጠና በሚገባ መስጠትን ይፈልጋልና ፕሮጀክት ማኔጅመንት እየሰለጠነች ትገኛለች።
ቦንቱ ከነበራትና ካለፈችበት የሥራና የትምህርት ሕይወቷ ለሴቶች የምትመክረው በርካታ ሃሳቦች አሏት። የመጀመሪያው ቤተሰብ ጫና ሳያበዛ ሴትን ልጅ የቤት ውስጥ ሙያን ማስተማር ይገባዋል የሚል ነው። በተለይ ዛሬ ላይ ‹‹ልጄን አቅብጬ ነው ያሳደኳት›› የሚባልበት እይታ የተዛባ ሃሳብን የያዘ ነው። ምንም አይነት የቤት ውስጥ ሙያ ሳይኖራቸው ብቻቸውን ሲሆኑ በብዙ እንዲቸገሩ ይሆናሉ። ይህ ችግራቸው ደግሞ ጤናቸውን በብዙ መልኩ ያዛባዋል። ምክንያቱም አሁን ላይ ውጪ መብላት በከፍተኛ ዋጋ ጤናችንን የሚጎዱ ነገሮችን መግዛት ነው። ጊዜያችንንም ቢሆን በአልባሌ ነገር ማጥፋት ይሆናል። ሙያው ኖሮን ግን በቤት ውስጥ ሠርተን ብንመገብ ጤናችንን፣ ወጨያችንን፣ ጊዜያችንንም እናተርፋለን ትላለች።
ሴቶችን አብዛኛው ማህበረሰባችን ሲሠራን በትንሽ ነገር እንድንደናገጥ አድርጎ ነው። በዚህም ምንም እንኳን ወንዶችን ብንበልጣቸውም፣ የተሻለ አቅም እንዳለን ብናምንም ያለንን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመን የተሻለውን ለመምረጥ በብዙ መልኩ እንቸገራለን። ይህ ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለናል። እናም ሁሌም መቻላችንን መቀበል አለብን። በተገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ አቅማችንን ማሳየት ይኖርብናል። ‹‹ለእንትና ይገባዋል›› ሳይሆን ‹‹ለእኔ ይገባኛል፣ አሳካዋለሁ›› የምንል መሆን አለብን። ያን ጊዜ የሚቀበለንና ተሳታፊ የሚያደርገንን ሰው እናበራክታለን። ወደፊት መጥተንም ሀገራችንን የማገልገሉን እድል እንጎናጸፋለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ እኛን ተከትለው ብዙ ሴቶች እንዲመጡ እናደርጋለን ስትል ትመክራለች።
ሴቶች በምንም መልኩ ስኬታቸውን ወደ ኋላ ሊጎትትባቸው የሚችልን ነገር መቀበል የለባቸውም። አንዱ ደግሞ ረጅም ሰዓትን ከማይመስሉንና ከማይጠቅሙን ሰዎች ጋር ማሳለፍ ነው። ህልም ከሌላቸውና መለወጥን ከማይሹ ጓደኞች መራቅ የግድ ይኖርባቸዋል። ‹‹አትችይም›› ከሚሉ አሳቢዎች ጋርም መቀጠል የለባቸውም። የሚሠሩ፣ የሚለፉና ለነገ ስኬታቸው ዛሬ ላይ ሆነው አርቀው የሚመለከቱ ሰዎችን ምርጫቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሁሉን ነገር በልክና እነርሱን በማይጎዳ መልኩ መተግበር እንዳለባቸውም ትመክራለች።
‹‹ጥሩ መሆን ከውጤታማነት ጋር መያያዝ አለበት›› ብላ የምታምነው ቦንቱ፣ በአንዳንዶች ዘንድ ጥሩ መሆን የስንፍና ምልክት፣ ጥሩ መሆን ያለመቻል ሁኔታ አድርገው ይወስዱታል። ይህንን እንዲያስቡ ያደረጋቸው ደግሞ ብዙዎች በጥሩ መምሰል ውስጥ አለመቻልን ስለሚያንጸባርቁ ነው። እናም ሴቶች ጥሩነታቸው መገለጥ ያለበት በመቻላቸውና በመሻላቸው ውስጥ መሆን ይገባዋል ትላለች። ችሎ ማሳየት ሲቻል ጥሩነቶች ብቻ ሳይሆኑ መጥፎ ስህተቶችም ከመታረም ይልቅ ትክክል ተደርገው ይወሰዳሉ። ስህተቶች ስንፈጽም እንኳን የሚናገረን አይኖርም። እናም ቀድሞ መምጣት ያለበት መቻልና በተሰማራንበት የሙያ መስክ ውጤታማ መሆን ነው። ከዚያ ጥሩነትን ማስከተል፣ ስህተቶችን መቀነስ ይመጣል ። በመሆኑም ሴቶች ይህንን መርህ ቢከተሉ የተሻሉ ስኬቶች ላይ መድረስ እንደሚችሉ ትናገራለች። አክላም ከወንዶች እኩል ተወዳዳሪ ለመሆን የሚገጥሟቸው በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም ያንን ተጋፍጦ የተሻለውን ለማግኘት መታተር እንዳለባቸውም ታስገነዝባለች።
‹‹እኛ የተነገረንና እያየን ያደግነው ሕይወት ውጤቶች ነን›› የምትለው ቦንቱ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚሰጠን ግምትና በቤተሰቦቻችን ውስጥ ያደግንበት ሁኔታ በተለይ የሥራ አማራጮችንና እድሎችን ከማግኘት አንጻር ብዙ ጊዜ ወደ ኋላ ይጎትቱናል። እንደ ወንዶቹ ሁሉ ሻይ ቡና ብለን የራሳችንን እድል እንዳናመቻችም እንቅፋት ይሆኑናል። ስለዚህም ሴቶች ከዚህ አንጻር ሰው ምን ይለኛል የሚለውን የተዛባ አመለካከት ከውስጣቸው ማስወገድ አለባቸው ትላለች። ምክንያቱም ወንዶች የሥራ እድሎችን የሚያገኙት ለሚሠሩት ሥራ ትኩረት ሰጥተው ብቻ ሳይሆን የሥራ አማራጮች የሚገኙበትን ሁኔታ ሁሉ መጠቀም መቻላቸው ነው። እናም የሴቶች ጫና ከወንዶች የከፋ ቢሆንም ራሳቸውን መጠበቅ እስከቻሉ ድረስ መስመር አበጅተው ለስኬታቸው መፋጠን ይገባቸዋል ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች።
በመጨረሻ ቦንቱ ያነሳችው ነገር ቴክኖሎጂን የመጠቀም ሁኔታን ነው። ሴቶች የአስተውሎት መጠናቸው፣ ምስጢርን የመግለጥ አቅማቸው ከወንዶች የላቀ ነው። አንድ ነገር ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገሮች አይተው የተሻለውን መርጠው መተግበር ይችላሉ። ዛሬ ደግሞ ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ለእነርሱ ጥሩ እድልን ያጎናጽፋቸዋል። ቤታቸው ቁጭ ብለው ዓለምን የመያዝና በቂ ገቢን የማመንጨት እድልን ያገኛሉ። ሀገርንም ሆነ ራሳቸውን የሚጠቅም የፈጠራ ሥራን ማከናወንም ይችላሉ።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የትኛው ዘርፍ ያዋጣኛል የሚለውን ለመለየት የሚችሉበትን መንገድ ይቀይሳሉ። ሆኖም እንደ እኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ለሴት ተብለው የተሠሩ ሙያዎች እንዳሉ በሚመስል መልኩ የታጠሩባቸው በርካታ መንገዶች ስላሉ ያንን መስበር እስካልቻሉ ድረስ ካሰቡት አይደርሱም። በዚህ አጋጣሚ ማለት የምችለው ሁሉም ሙያ ከሴቶች በላይ አይደለም። ሁሉም ሥራም ከእነርሱ አቅም የሚበልጥ አይሆንም። ማድረግ ያለባቸው መማርና ሁኔታውን መገንዘብ ብቻ ነው።
በጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም