ክል አይነት ወደገበያ በመቀየር ነው የሚታወቁት። ከአርባዎቹ ምንጮች መገኛ በሆነችው አርባ ምንጭ ዙሪያ ነው እትብታቸው የተቀበረው። ወይዘሮ ፀሐይ ዴአ ይባላሉ። ትውልድና እድገታቸው በጋሞ ጎፋ ዞን ቦሮዳ አካባቢ ነው። በልጅነታቸው የገጠር አካባቢውን የቤት ውስጥ ቤተሰብ እገዛ ሥራዎች ሲያከናውቅኑ በተጓዳኝ ደግሞ ትምህርታቸውን ይከታተሉ ነበር። ቤተሰብ ከሚያዛቸው ሥራዎች በሚተራርፋቸው ጊዜያት የትምህርት ጥናታቸውን ያከናውኑ እንደነበረ ያስታውሳሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ትዳር በሩን ከፍቶ ሲመጣ በፀጋ ነው የተቀበሉት።
እናም በ16 ዓመታቸው አግብተው የቤት እመቤት ለመሆን በቁ። ይሁንና ለሩቅ ያሰቡለት ትምህርታቸው መቋረጡ አስከፍቷቸው ነበር። ምክንያቱም ልጆች በመወለዳቸው እና እነርሱን የማሳደግ በወጣትነታቸው ኃላፊነት ስለተጣለባቸው ለሁለት ዓመታት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል። ትምህርት ስምንተኛ ክፍል ላይ እንደቆመ ልጆች የማሳደግ ኃላፊነቱ ቢጣልባቸውም በጎን ግን ለኑሮ መደጎሚያ የሚሆን መጠነኛ ንግድ መሞካከራቸው አልቀረም ነበር። በተለይ ከአካባቢው ቡና አምራች ገበሬዎች የገዙትን ቡና ለመንደራቸው ነዋሪዎች እየቸረቸሩ በማቅረብ ንግዱን መለማመድ ጀምረዋል።
ከቡናው በተረፈ በወጣትነት እድሜያቸው ልጆች እያጠቡ እና የጓዳ ሥራውን እየከወኑ የእጅ ሥራዎችን በተለይም የጥልፍ ውጤቶችን እያዘጋጁ ለገበያ ያቀርቡ ነበር። ከ25 ዓመት በፊት ነው በሳምንት ያለቀውን ዳንቴል እና የአልጋ ልብስ በመጥለፍ በ100 ብር በመሸጥ ገቢ ማግኘትን የተማሩት። በወቅቱ ባለቤታቸው አዲስ አበባ ትምህርታቸውን ለመከታተል መጥተው ነበር። ባለቤታቸው ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ግን እዚያው ሥራ በማግኘታቸው ወይዘሮ ፀሐይም ልጆቻቸውን ይዘው አዲስ አበባ ገቡ።
ኑሮ በአዲስ አበባ በመከተሙ በቤት ውስጥ ሥራ ብቻ ተወስነው ሊያሳልፉ አልፈለጉም። ያቋረጡትን ትምህርት እንደገና ቀጠሉ። እስከ 12ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ የህፃናት እንክብካቤ መምህርነት እና የፊዚዎቴራፒ ሙያን በተጓዳኝ በአንድ ወቅት ይማሩ ነበር። በህፃናት መምህርነቱ ባይሠሩበትም በፊዜዎቴራፒው ገፈተውበታል። በሥራ ትጋታቸው የተማመኑ ሰዎች መማሪያ ክሊኒክ ውስጥ እንዲሠሩ ፈቀዱላቸው። በወቅቱ የሥራ ክፍያቸው በወር ስምንት መቶ ብር ብቻ ነበር።
በክሊኒኩ የሙያ እና ዕውቀት ደረጃቸው ከፍ እያለ ሲሄድ ደግሞ እስከ አስተማሪነት ደረጃ ደርሰዋል። ደሞዛቸውም አምስት ሺ ብር ሆኗል። የአጥንት ስብራት እና የስር ህመሞች ችግር የገጠማቸው ሰዎች ሲያጋጥሟቸው ምክራቸውን ይጠይቋቸዋል። በወቅቱም ሞሪንጋ የተባለው ተክል በምግብነት ቢወስዱ በውስጡ ካልሺየም እና ዚንክ የተባሉ ንጥረነገሮች ስላሉት ለጤናቸው ጠቃሚ እንደሆነ ይመክሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በጊዜው ሞሪንጋ የተባለው ቅጠል እምብዛም ባይታወቅም ወይዘሮ ፀሐይ ግን በአርባምንጭ የታወቀ ምግብ ስለሆነ ከልጅነታቸው ጀምሮ ያውቁታል። በተጨማሪ ስለቅጠሉ በዶክተሮች ተጽፎ ያገኙትን መረጃ ሲያነቡ በውስጡ ስለያዛቸው ንጥረነገሮች ግንዛቤያቸው ይጨምራል። በመሆኑም ለአጥንትና ለስር ህመሞች በቶሎ ለመዳን የሚያስችል ምግብ እንደሆነ መምከራቸውን ቀጥለዋል። ታካሚዎችም ወይዘሮ ፀሐይን ቅጠሉን እንዲያመጡላቸው መጠየቅ ጀመሩ። እርሳቸውም ለቤተሰብ ጥየቃ በሚሄዱበት ወቅት እያመጡ ለተወሰኑ ታካሚዎች በነፃ ይሰጡ ነበር። በሞሪንጋው ፈዋሽነት የተደሰቱ «ከህመማችን በቶሎ ለመዳን ረድቶናል» ያሉ ሰዎች ደግሞ «አምጡልን እያልን ከምናስቸግር በሽያጭ መልክ ይሁንልን» የሚል ጥያቄ ለወይዘሮ ፀሐይ አቀረቡላቸው። የአምስት ዓመቱ የፊዚዮቴራፒው ክሊኒክ ቆይታቸው መጨረሻ ዓመታት ላይ የሚመጡ ታካሚዎች ሃሳብ ወደ ንግዱ መራቸው። አርባምንጭ ከሚገኙ ዘመዶቻቸው ያመጡትን የሞሪንጋ እርጥብ ቅጠል በመጀመሪያው የሽያጭ ያስገቡት ገቢ ይበልጥ አነቃቅቷቸዋል። እንዲህ እንዲህ እያለ የሞሪንጋው ገበያ በመድራቱ በመምህርነታቸው ክፍያ የበለጠ ገቢ በማግኘታቸው የንግድ አለሙን መቀላቀል እንዳለባቸው ለእራሳቸው ነግረዋል።
በአንድ ወቅት በክሊኒኩ እየሠሩ በፊዚዮቴራፒ መምህርነታቸው ከሚከፈላቸው አምስት ሺ ብር በላይ ማግኘት መቻላቸው ደግሞ በፍጥነት ንግዱን እንዲቀላቀሉ ገፋፍቷቸዋል። በዶክተር ኬኬ የተዘጋጀ የማር እና ሞሪንጋ ተፈጥሯዊ መድኃኒትነት የሚገልጽ መጽሐፍ ገዝተው የበለጠ ስለሞሪንጋ ጥናት ማድረጋቸው ቀጥለዋል። ቅጠሉን ከሌሎች ምግቦች ጋር ቀላቅሎ እንዴት ለንግድ ማቅረብ ይቻላል? የሚለውንም በበሳል የንግድ አዕምሯቸው አሰላሰሉት። ሥራቸውንም ለመልቀቅ ሲወስኑ ለክሊኒኩ የሚሠሩ ወጣቶችን አሰልጥነው ተሰናበቱ።
ወይዘሮ ፀሐይ ሙሉ ትኩረታቸው ስለሞሪንጋ ምርት ንግዳቸው ማሰብ ጀምረዋል። በቤታቸው የሞሪንጋ ቅጠልን ጥቅም እያስተዋወቁ መሸጡን ተያያዙት። ይሁንና በወቅቱ ህብረተሰቡ ስለቅጠሉ ያለው ዕውቀትና ስለምግብነቱ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ንግዱ አክስሯቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ለአንድ ዓመት አልፎ አልፎ ከሚገኝ ሸማች በስተቀር ሥራው ተመናምኖ አስቸግሯቸውም ነበር። በተለይ ለማስተዋወቅ የሚያወጡት ወጪ እና ከምርት የሚያገኙት ገቢ ባለመመጣጠኑ ቀድሞ በክሊኒኩ ሲሠሩ የቆጠቧትን 20 ሺ ብር ለቤት ወጪ መጠቀማቸው አሳስቧቸው ነበር።
በወቅቱ ሞሪንጋውን ለሽያጭ ሲያቀርቡላቸው አንዳንድ ሰዎች ምን እንደሆነ ስለማያውቁ «ጌሾ ነው ወይንስ ቅጠል ነው?» በማለት ይጠይቋቸው እንደነበረ ይናገራሉ። በወቅቱ «ምነው መምህርነትን ባልለቀኩት» እስከማለት ያደረሰ ሥጋት ተፈጥሮባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። «በርትቼ ካስተዋወቅኩት ግን የተሻለ ማደግ እችላለሁ» የሚለው ሃሳባቸው በመጠንከሩ ንግዱ ውስጥ በጽናት እንዲቆዩ ረድቷቸዋል። ለንግድ የሚሆናቸውን ምቹ አቀራረብ በመፍጠር ሰዎች ወደ እርሳቸው ምርቶች ባይመጡ እንኳን እርሳቸው ምርታቸውን ህብረተሰቡ እየቀመሰ እንዲላመድ በማድረግ ንግዳቸው መሰረት እንዲይዝ አድርገዋል። ከአንድ ዓመት በኋላ ገበያው ማንሰራራት ጀመረ።
የወይዘሮ ፀሐይም ምርቶች በስፋት ተጠቃሚዎች ጋር እንዲደርስ ጥረታቸውን በእጥፍ አሳደጉ። በተለይም ምርቶቻቸውን በማድረቅ እና በመፍጨት በሻይ መልክ እና ምግብ ውስጥ ለመጨመር አመቺ በሆነ መልኩ እንዲቀርብ አደረጉ። በፕላስቲክ ማሸጊያዎች ጭምር ማዘጋጀት በመጀመራቸው ተፈላጊነታቸው ጨመረ። የገበያ አቀራረባቸው ለጥራት እንዲመች በር በመክፈቱ እና ቀድሞም ለማስተዋወቅ ሰፊ ሥራ በመሥራታቸው አሁን ላይ ምርቶቻቸው የሚገዙ ደንበኞች ተበራክተዋል።
በቤታቸው ያመርቱት የነበረው ምርት ተደራጅተው በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ እንዲያመርቱ ዕድል አግኝተዋል። በዚያም ከሞሪንጋ ቅጠል በተጨማሪ ፍሬውን እና ሥሩንም ጭምር በጥራት አዘጋጅተው እንዲሁም አሽገው ለገበያ ያቀርባሉ። በተጨማሪም ዳጣ፣ የጥቁር አዝሙድ ዘይት እና የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን ማመረት ጀምረዋል። ምርቱ ደግሞ የሚዘጋጀው አርባ ምንጭ ከሚገኘው የቤተሰብ እርሻ ቦታ ላይ ነው።
ወይዘሮ ፀሐይ እንደሚናገሩት፤ የቤተሰባቸው እርሻ ቀድሞ የተለያዩ ሰብሎች ይመረትበት ነበር። አሁን የሞሪንጋ ንግዱ ሲቀላጠፍ በማሳው ላይ ሞሪንጋ ተተክሎ በየወቅቱ እንዲሰበሰብ እየተደረገ ይገኛል። በዚህም ለቤተሰብ ቀለብ ብቻ ይውል የነበረው መሬት ተገቢውን ገቢ ወደሚያስገኝ ምርት ተቀይሯል። ለቤተሰብ ከሚሰጠው የእርሻ ምርት በተጨማሪ በሞሪንጋ ምርቱ ለአምስት ሰዎች የሠራ ዕድል ተፈጥሯል። በአዲስ አበባ ደግሞ ተዘጋጅቶ የመጣውን ምርት አሽጎ እና አቀነባብሮ ለመሸጥ ሁለት ሰዎች ተቀጥረው እየሠሩ ይገኛል። ምርቱም ለተለያዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች እየቀረበ ተጨማሪ ገቢን እያስገኘ ነው። በተለይ እስከ አስር ኩንታል በአንድ ጊዜ የሚረከብ ተቋም በመኖሩ አነስተኛ የመፍጫ መሣሪያ ገዝተው እየሠሩበት ነው።
በአራት ዓመታት የሞሪንጋ እና ተጓዳኝ ምርቶች ንግድ ለዕቃ ማመላለሻ የሚሆን ሰባት መቶ ሺ ብር የሚያወጣ አንድ ዘመናዊ ሚኒባስ ገዝተዋል። በንግዱ ገቢ ሦስት ልጆቻቸውን ዩኒቨርሲቲ እያስተማሩ የቤታቸውንም ወጪ ያለምንም ሥጋት መሸፈን ችለዋል። ሦስት አነስተኛ መፍጫ እና የጥቁር አዝሙድ መጭመቂያ መሣሪያዎችም ሥራ ላይ ናቸው። በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ሀብታቸው ሁለት ሚሊዮን እንደሚጠጋ ወይዘሮ ፀሐይ ይናገራሉ።
«ከዚህ የበለጠም መሥራትና መነገድ እችላለሁ» የሚሉት ወይዘሮዋ «የያዘኝ ችግር አለ» ይላሉ። ሦስት እና አራት ኪሎ የሚሆን የሞሪንጋ ምርታቸውን በትውውቅ ለሚመጡ የውጭ አገራት ደንበኞቻቸው በፖስታ ማድረስ ቢችሉም በቀጥታ ግን ላኪ መሆን አልቻሉም። በቀጥታ የሞሪንጋ እና የተለያዩ ምርቶቻቸውን ወደውጭ አገራት ለመላክ የሚያግዛቸው የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የሞሪንጋ ምግብነት ማረጋገጫ እንዳላገኙ ይገልፃሉ።
ችግሩ የተፈጠረው የባለስልጣኑ ሰዎች ለጉዳዩ አዲስ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ «በምን አሠራር እንስጥዎት?» ከሚል የመነጨ መሆኑን ወይዘሮ ፀሐይ ያነሳሉ። መድኃኒትነት ያለው ምግብ መሆኑ ቢረጋገጥ የሞሪንጋ ለስላሳ አምራቾች ጭምር ለመሸጥ ያስችላል። የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የተለያዩ ላቦራቶሪዎች ፍተሻ ፍቃድ ቢኖራቸውም አንዱ ማረጋገጫ ብቻ በመቅረቱ ንግዳቸው እንዳይጎዳ ሥጋት አድሮባቸዋል።
«ተስፋ አልቆርጥም» የሚሉት ወይዘሮ ፀሐይ፣ ወደፊት የሞሪንጋ ምርቶች ላኪ በመሆን ለአገር የውጭ ምንዛሬ እሰከማምጣት የሚደርስ ንግድ እንደሚኖራቸው እምነት ጥለዋል። በቀጣይ ደግሞ የሞሪንጋን ፍሬ ጨምቀው ወደ ዘይትነት መቀየር ዋነኛ እቅዳቸው ነው። የሞሪንጋ ሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ ከፍተው መሥራትም አላማቸው ነው።
በዚህ ንግድ ከምርት እስከ ማቀነባበር የደረሰ ንግድ ውስጥ ተሳትፈው እራሳቸውን ብሎም አገራቸውን ማሳደግ ፅኑ ፍላጎታቸው ነው። የእርሳቸው ገበያ ሲቀንስ በብዛት በማስተዋወቅ ወደተጠቃሚው በማድረስ ገቢያቸውን ያሳደጉበትን መንገድ ማሳያ የሚያደርጉት ወይዘሮ ፀሐይ በየጊዜው የሚከሰቱ የንግድ ችግሮች ማምለጫ መፍትሄዎችን በማዘጋጀት ትርፋማ መሆን ይቻላል ይላሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19/2011
ጌትነት ተስፋማርያም