የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት በከተሞች የድህነትንና የሥራ አጥነትን ምጣኔ በመቀነስ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ ዜጎችን በአነስተኛ ካፒታል አነስተኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ቀስ በቀስ ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅምን እንዲፈጥሩ የሚያስችል ስርዓት የተዘረጋበት ነው። ኢትዮጵያን በመሰሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ባላቸው አገራት ድህነትንና ስራ አጥነትን ለመቀነስ በሚደረገው ርብርብ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ፡፡
ዘርፉ የሚያበረክተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከግምት ያስገባ ሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተሳፉበት ሁለተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር “ተወዳዳሪ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማፍራት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ እናፋጥናለን” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን እና ባዛር በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በዕደ ጥበብ ስራዎች፣ በፈጠራና እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ አምራች ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 180 ኢንተርፕራይዞች፣10 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችና ተሳታፊዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡ ከተሳታፊዎች ውስጥ 50 በመቶ ያህሉ በሴቶች ባለቤትነት የሚተዳደሩት ናቸው፡፡ አምስት በአካል ጉዳተኛ የሚመሩ ኢንተርፕራይዞች የተሳተፉ ሲሆን ይህም አካል ጉዳተኞች ሶስት በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ከአዲስ አባባ ነጋዴ ሴቶችና ከኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበራት ከእያንዳንዳቸው ሶስት በድምሩ ስድስት፣ ከሴቶች ኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም /WEDP/ አምስት፣ ከኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ማዕከል /EDC/ አምስት በድምሩ ከአጋር አካላት የተመለመሉ 32 ኢንተርፕራይዞችም ተሳትፈዋል፡፡
በተጨማሪም በኤግዚብሽንና ባዛሩ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋሟት የተወጣጡ ስድስት ኮሌጆችናየኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት አቅራቢ የልማት ድርጅት እንዲሁም ኦሮሚያ እና አዲስ ብድርና ቁጠባ አክስዮን ማህበራትና አዲስ የካፒታል ዕቃ አቅራቢ ተቋም ተሳትፈዋል፡፡ በቦታው ተገኝተው ኤግዚቢሽንና ባዛሩን በይፋ የከፈቱት የዕለቱ የክብር እንግዳ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ልማትና ከተማ ልማት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ በአገሪቷ ድህነትንና ስራ አጥነትን ለመቀነስ በሚደረገው ርብርብ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራዞች በድህነት ውስጥ ከሚኖረው ህብረተሰብ ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው ያሉት አማካሪ ሚኒስትሩ በሀገሪቷ የተጀመረውን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማሳካት እየተሰሩ ካሉ ስራዎች መሀል ግንባር ቀደሙ የስራ እድል ፈጠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለተለያዩ ዜጎች የስራ እድሎችን በመፍጠር በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች ሀብት መፍጠር ተችሏል ያሉት አቶ ጃንጥራር፤ በቀጣይም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራዞችን በሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች ማለትም በማዕድን፣ በቤቶች ልማት፣ በስኳር እና መሰል ስራዎች ላይ ተሳታፊ ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ በበኩላቸው፤ “በዓመት ሁለት ጊዜ በምናዘጋጀው እንዲህ አይነቱ አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር በርካታ በማምረት ላይ የተሰማሩ የአገራችን ሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ አምራች ኢንትርፕራይዞች ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅና በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡”
ብለዋል፡፡ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ በርካታ ጠቀሜታዎች የሚኖሩት ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ምርት ወይም አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ ሰፊ እውቅና ማስገኘት፤ አምራቾች ምርቶቻቸውን ወይም አገልግሎታቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚዎች በመሸጥ ተጠቃሚ ማድረግ፤ እስከ ንዑስ ተቋራጭነት የሚያደርስ የገበያ ትስስር መፍጠር፤ የተሞክሮ ልውውጥና የወደፊት ደንበኞችን በአካል ማግኘትንና ፍላጎታቸውን መለየት ማስቻል እና ለዕይታ በሚቀርቡ ምርቶችና አገልግሎቶች እንዲሁም ማስታወቂያዎች ህብረተሰቡ በዘርፉ ላይ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ይገኙበታል፡፡ ወጣት ገነት ተስፋዬ ከድሬዳዋ የመጣች ተሳታፊ ናት፡፡ ከአልሙኒየም የተሰሩ የተለያዩ የመኪናመለዋወጫዎችንና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን በማምረት ለገበያ የሚያቀርብ አነስተኛ ድርጅት ባለቤት ናት፡፡
ተመሳሳይ በሆኑ መድረኮች በተደጋጋሚ መሳተፏን የምትገልጸው ገነት፤ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ እንዲህ ባሉ መድረኮች መሳተፏ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳስገኘላት ትናግራለች፡፡ ለገበያ ይዛ ያቀረበቻቸውን ድስቶች፣ መጥበሻዎች፣ የፉል ሰሃኖችና ሙቀጫዎች እና ሌሎችም ምርቶች የአመራረት ሂደትና የገበያ ሁኔታ ስትገልጽም “ የምንሰራው አልሙኒየም ከገበያ ላይ በመግዛት ቤት ውስጥ ባሉ አነስተኛ የኤሌክትሪክ ማሽነሪዎች በመታገዝ በእጃችን አቅልጠን ነው፡፡›› ትላለች፡፡ በተጨማሪ የባጃጅ መለዋወጫዎች፣ የጎማ ጌጦችና ሌሎችም የመኪና መለዋወጫዎች በማምረት ለቸርቻሪ መለዋወጫ ሱቆች የሚያቀርቡ መሆኑን ጠቁማ፤ የሚሸጡበት ዋጋም ገበያ ላይ ካሉት የቻይና ምርቶች የቀነሰ መሆኑን ትናገራለች። ‹‹በምርቶቻችን ድሬዳዋ ላይ በጣም ታዋቂ ነን።
በተደጋጋሚ ባገኘነው የኤግዚቢሽንና ባዛር ተሳትፎ ዕድል ምክንያት አሁን አዲስ አበባ ላይም እየታወቅን ነው” ብላለች፡፡ ወደፊት የምታመርተውን ምርት በመጠንና በጥራት በማሳደግ በፋብሪካ ደረጃ የማምረት ዕቅድ እንዳላት የምትናገረው ገነት፤ በቅርቡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሰጣት ቦታ ላይ ግንባታ በማካሄድ ምርቷን በፋብሪካ ደረጃ ለማምረት ዝግጅት እያደረገች መሆኗን ገልጻለች፡፡ ሌላዋ የኤግዚቢሽንና ባዛሩ ተሳታፊ ወጣት ትንሳኤ መስፍን በእናቷ ባለቤትነት የሚተዳደረው “በላይነሽ ታረቀኝ የባህል አልባሳት” ያመረታቸውን የባህል ልብሶች ይዛ ቀርባለች፡፡ ትንሳኤ በእናቷ ፊት አውራሪነትና በተጨማሪ ሰራተኞች በቤት ውስጥ የባህል ልብሶችን በማምረት ለገበያ እንደሚያቀርቡ ትናገራለች፡፡
በአገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር ሲሳተፉ ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑን የምትገልጸው ትንሳዔ፤ በሌሎች ኤግዚቢሽኖች ላይ በመሳተፍ ተሞክሮ እንዳላቸው ትገልጻለች፡፡ አያይዛም እናቷ ስራውን የጀመሩት በ2008 ዓ.ም መሆኑን ትናገራለች፡፡ “ኤግዚብሽንና ባዛሩ እንደኛ ላሉ አምራቾች ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ማምረቻ ቦታና ሱቅ ስለሌለን በቤታችን ውስጥ ሰርተን የምንሸጠው ፈልገውን ለሚመጡ ሰዎች ነው፡፡ እንዲህ አይነት መድረክ ሲፈጠር ምርቶቻችን ይታዩልናል፤ በተጨማሪምሰፋፊ ትእዛዞች የሚያቀርቡልን አዳዲስ ደንበኞችም እንድንተዋወቅ በር ይከፍትልናል›› ብላለች፡፡
‹‹በወር ውስጥ እስከ ሁለት መቶ የባህል ልብሶችን የማምረት አቅም አለን፡፡›› የምትለው ትንሳኤ፤ ምርታቸውን ማከፋፈል እንዳልጀመሩና በመኖሪያ ቤት ውስጥና በተመሳሳይ ባዛሮች ላይ ራሳቸው እንደሚሸጡ ገልጻለች፡፡ ይዛ ስለቀረበቻቸው የባህል አልባሳት ሰትገልጽ “ምርቶቻቸን ጥራት ያላቸውና ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ዋጋችንም ተመጣጣኝ ነው፡፡ ምርቶቻችን ዋስትና አላቸው፡፡
እኛ የምንሰራው ደንበኞቻችን ተመልሰው እንዲመጡ እንጂ በዚያው እንዲቀሩ አይደለም፡፡ ›› ብላለች፡፡ የፌዴራል የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከአዲስ አበባ መስተዳድር በቅርቡ ቋሚ የኤግዚቢሽንና ባዛር መገበያያ ስፍራን ለመገንባት በተረከበው ጀሞ ቁጥር አንድ አደባባይ አካባቢ እየተካሄደ ያለው ኤግዚቢሽንና ባዛር ከሚያዚያ 14 እስከ ሚያዚያ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ቆይታ ያደርጋል፡፡ በቆይታውም ከ17,000 በላይ በሆኑ ጎብኚዎች እንደሚጎበኝና የ4 ነጥብ 65 ሚሊዮን ብር ሽያጭና የገበያ ትስስር ይፈጠርበታል ተብሎ ተጠብቋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2011
የትናየት ፈሩ