የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪዎችና ጸሐፍት እንደሚያስረዱት፣ በአንድ አገር አስተማማኝና ዘላቂ ሠላም እንዲሁም ልማት እንዲረጋገጥ ከተፈለገ ለውጥ እጅጉን ወሳኝ ነው:: ለውጥ ሁልጊዜም ውጤት አለው። ለውጥ ግን ውጤት የሚኖረው ለውጡ ሲጀመር ነው፤ የተጀመረ ለውጥ ደግሞ ሂደት ውስጥ ይገባል። እናም ለውጥ ወደ ውጤት እንዲቀየር የለውጥ ጅማሮ እና የለውጥ ሂደቶች በጊዜያቸው መታየት ይኖርባቸዋል:: ምክንያቱም ውጤት ከጅማሬና ከሂደት በኋላ የሚገኝ ነው።
በዚህ የመጀመር እና የማድረግ የለውጥ ሂደት ውስጥ ታዲያ ለውጡን የሚያስተናግዱ ሰዎች እጅጉን ወሳኝ ናቸው:: ለውጥ ላይ አተኩረው ጥናት የሚያካሂዱ ባለሙያዎች እንደሚነግሩን፤ ለውጥ በሚፈጠርበት ጊዜ ሦስት ዓይነት ቡድኖች ይኖራሉ:: እነዚህም የለውጡ አራማጆች፣ የለውጡ ታዛቢዎች እና የለውጡ ተቃዋሚዎች ናቸው። በመሆኑም ማንኛውም ለውጥ ሲታይ እንዲህ ዓይነት ሦስት ሰውኛ ቡድኖችን መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
እዚህጋ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ግን በለውጥ ውስጥ የሚገኝ መልካም ውጤት ለሕዝቦች የመኖር ተስፋ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ፤ ለውጡ በአግባቡ ካልተያዘ፣ ካልተመራ እና የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በጎ አስተዋጽኦ ካልታከለበት ውጤቱ አሉታዊ ሊሆን ይችላል። የለውጥ ውጤት ደግሞ እንዲህ በአሉታዊ መልኩ ሲገለጽ ደግሞ ለውጥ የመኖር ተስፋ ከመሆኑ ባሻገር የሕልውና ሥጋት ይሆናል::
ከዚህ አንጻር አሁን በአገራችን የታየው ለውጥ ታሪካዊና እንደ አገር የመኖራችንን ተስፋ ያናረ ነው። ምንም እንኳን ለውጡ እውን ከሆነ ጊዜው አጭር ቢሆንም፤ በስፋቱና በጥልቀቱ ግን በአገራችን ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው መሠረታዊ የአመራርና የአሠራር የሪፎርም ማሻሻያዎች ከማድረግ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል:: በዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና ሌሎችም የለውጡ አመራር አባላት የተጀመረው ይህ የለውጥ እንቅስቃሴም፤ ኢትዮጵያ ከቀደሙት ዓመታትና ካለፉት ወራት በተሻለ ቁመና ላይ ትገኛለች::
ይህ ውጤት የተገኘው ግን በተደላደለ የለውጥ ሂደት ውስጥ አልነበረም:: ይልቁንም ከውስጥም ከውጭም ለውጥ ጠል አካላት የተቀናጀና የተናበበ ፈተናን ደቅነው እያለ ነው:: ሆኖም ፈተናን ወደ ጥንካሬ፣ ተግዳሮትን ወደ መልካም ዕድል የሚያሸጋግር ዝግጁነትና ፈጣን ምላሽ የሰጠ አመራር በመፈጠሩና ሕዝቡን ከጎን ማሰለፍ በመቻሉ አገርንና ሕዝብን የማዳንና የማበልፀግ አኩሪ ተግባር መፈፀም ተችሏል::
ባለፉት አምስት አመታትም በኢትዮጵያ በተደረገው ለውጥ፤ ድል፣ ፈተናና ተስፋ ተፈራርቀዋል:: ለምሳሌ፣ በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች በሕዝብና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ዜጎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል። ከዚህ በተጓዳኝ የለውጡን ውጤት «ዛሬና አሁኑኑ ካላየሁ» በሚል ልጓም አልባ ስሜታዊነትና ተግባር ብዙዎች በራሳቸው መንገድ ሲጓዙም ታይተዋል:: በዚህ እንደ አገር ብዙ ፈተና ደርሷል፤ ዋጋም ተከፍሏል::
አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታም ዜጎች የለውጡን ጅማሬ ቀመሱ እንጂ ሙሉ በሙሉ አጣጣሙ ለማለት አያስደፍርም:: ለውጡን ያማረ ነው ወይስ የመረረ ነው ለማለት በደንብ ማጣጣም ግድ ይላል:: ከዚህ አንጻር ሲታይ አሁን ላይ በለውጥ መንገድ ላይ እንደሆንን ለሁላችንም ግልጽ ነው:: በአንድ ጀንበርም ለውጥ የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም:: መረጋጋትን ይጠይቃል:: ጅማሬውን ስንመለከተው ግን የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ እንዲሉ ነው:: ለውጡ ተስፋ የሚጭር እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም::
ይሁንና የለውጡን ፍሬ ይበልጥ ለማጣጣም በጉጉትና በናፍቆት የሚጠብቁ የመኖራቸውን ያህል በለውጡ የሚናጡና የሚደናገጡ በርካቶች ይስተዋላሉ:: የለውጡን ፍጥነትና ስኬታማነት በየደረጃው በመረዳትና በመገምገም ተገቢውን ተሳትፎ ከማድረግና ሂሳዊ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ «እኛ ከሌለንበት» የሚሉ ከአፈርኩ አይመልሰኝ ልክፍት የፖለቲካ ሰብዕና ሰለባ የሆኑ፤ ግላዊ የልዩ ፍጡርነት ስሜት (false or wrong self-perception) ሰለባዎች ዛሬም አሉ።
በተለይ በኢትዮጵያ እድገት የሚከስሩ፣ በውድቀቷ የሚያተርፉ የዘመናት የሕዝቦች ጥያቄና ፍላጎት የሆነውን ዴሞክራሲን የመትከልና የማጽናት ትግልን ለመቀልበስ ሲጥሩ ቆይተዋል፤ አሁንም እየጣሩ ይገኛሉ:: ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እገዛ ከማድረግ ይልቅ ከውስጥም ከውጭም በባዕዳን ነዋይ ተደልለው በገዛ አገራቸው ኢትዮጵያ ላይ የጸረ አንድነት መፈክር በማሰማት ሕዝብ የሚፈልገውን አገራዊ ዕድገት የሚያስተጓጉሉ ከንቱዎች አሁንም አልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግላቸውን ቀጥለዋል::
ለውጡ የመጣላቸው ሳይሆን የመጣባቸው «ለምን እየሰረቅንና እየዘረፍን አንኖርም?» የሚል ትልቅ ሀፍረትና ህሊና ቢስ ጥያቄና ሙግት የሚገጥሙ፣ ኢትዮጵያን ለመዝረፍ፣ ለማስለቀስ፣ የድህነት መስቀል ላይ ቸንክረው ለማሰቃየት የሚተጉም በርካቶች ናቸው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለያይቶ እንዲያስብና ተግባብቶ እንዳይኖር ፅኑ ፍላጎት ያላቸው መንደርተኞች አሉ:: ፍላጎታቸውም የሚመኙትን ስልጣን ለመቆናጠጥ ሲሆን፤ ለዚህም በሕዝብ መካከል የገዢነትና የተገዢነት እሳቤን በመዝራት፣ ይሄንን ስሜት በማጋጋልና በማነሳሳት ንዴት ማስታጠቅና እንዳሻቸው ሕዝቡን እየዘረፉ ሀብት ማከማቸት ነው።
ፖለቲካዊ ሀሳብና መፍትሄ ከማመንጨት ይልቅ ስልጣን ለመያዝ በመናፈቅ በጎሳና በጎጥ ተደራጅተው በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች ፀብ በመዝራት ጥላቻን በመስበክ ማበጣበጥና የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ ዛሬም መንደራዊ ሹማምንቶች አሉ:: እነኚህ ኃይሎች በድብቅ በሚያስተላልፉት መልዕክትም ሆነ በማህበራዊ ድረ ገፆች ዕለት በዕለት በሚፅፉት ጽሑፍ ሕዝብን በማናቆር ድርና ማግ ሆነን የተሰፋበትንና የተቆራኘንበትን የአንድነት ሰንሰለት ለመበጣጠስ ሲሆን፤ ከተሳካላቸውም አገሪቱን ማፍረስ ነው።
በእርግጥ እነዚህ ለውጥ አናዋጮች በአሁኑ ወቅት በለውጡ ማዕበል እያታመሱ፣ አንዳዶቹም እየሠመጡ ናቸው:: እንደ ሕዝብም የእነዚህ የእፍኝት ልጆች ተልዕኮ ለብዙዎች ግልፅ እየሆነ ይገኛል:: ይህ ማለት ግን ሁሉም ሰጥመዋል ማለት አይደለም:: እውቀቱና ብልጠቱ የሌላቸው እና በቀላሉ በውዥንብር የሚታለሉም ለውጡን በመጠራጠር ለማናወጥ የሚታትሩም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም::
ይሁንና ችግሮች በተከሰቱና ውዥንብሮች በተናፈሱ ቁጥር ቶሎ ብሎ ለውጡን ወደ መጠራጠር የምንሄድ ከሆነ በመሠረቱ ትክክል አይደለም:: ዋናው ጉዳይ ለውጡ ይዞት የተነሳው ትልቅ ራእይና አላማ መረዳት ያስፈልጋል:: ችኮላ አደገኛ መሆኑን መገንዘብና የምንፈልገው ነገር ዛሬውኑ ካልተደረገልን ሙግት ማስወገድ የግድ ይለናል።
ውጤቱን «ዛሬና አሁኑኑ ካላየሁ» ከሚል ልጓም አልባ ስሜታዊነት ወጥተን ገንቢ በሆነ ሂሳዊ አመለካከት ‹‹critical and constructive way of thinking›› የመነሻችን፣ የሂደታችንና የመዳረሻችን ምንነትና እንዴትነት በአግባቡ መረዳት ግድ ይለናል።
አብዛኛውን ጊዜ እንዲለወጥ የምንፈልገው ይኖራል እንጂ እኛ ራሳችን መለወጥ እንዳለብን ብዙም አናስተውልም:: ሳንለወጥ የማይለወጡ ነገሮች እንዳሉ መረዳት ይኖርብናል:: የሚለወጥ ነገር መኖሩን ለመቃኘት የምንናፍቅና የምንታትረውን ያህል እኛም ቢያንስ በአስተሳሰብ ልንለውጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ጎልተው ሊታዩን ይገባል:: ስመጥሩ የቀድሞ የሕንድ መሪ ማህተመ ጋንዲ እንዳሉትም እንዲሆን የምንፈልገውን ለውጥ መጀመሪያ እኛው እንሁነው::
ማንኛውም ትልም በተናጠል ጉዞ አይሳካም:: የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚረጋገጠው አንድ ሆነን ነጋችንን ታሳቢ በማድረግ በምንጽፈው ታሪክ፤ በምንወረውራት እያንዳንዷ ጠጠር ነው:: በእርስ በእርስ ትስስር፣ መተማመን፣ መግባባትና ወንድማማችነት ከሁሉም በላይ የአገር ባለቤትነት ስሜት ነው::
ከተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ ሰዓት ሳንቆጥር፣ ድካማችንን ሳናስተዋል፣ ልዩነቶቻችን ለአገር ልማት እንቅፋት ሳይሆን ካለፈው ታሪካችን ተምረን ለትውልድ የምናወርሰው ሥራ ለመሥራትና ለዚሁ የሚሆን መሠረት ለማስቀመጥ እጅ ለእጅ መያያዝ ይኖርብናል:: ተመካክረንና ተደማምጠን ከሠራን፣ ተወያይተንና ተከራክረን ከተጓዝን፣ ተባብረንና ተጋግዘን፣ ተቻችለንና ተፈቃቅረን ወደፊት ከገሰገስን ኢትዮጵያን ከፈተና ወደ ልዕልና ከፍ ማድረግ ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ይሆናል።
እስከዛሬ በመጣንበት መንገድ እየተባላን እየተናከስን በጎሳ እየተቧደንን ከተጓዝን ያው ጨለማ ውስጥ እንዳክራለን። ይህ እንዳይሆን ዙፋናዊ ጥማታቸውን ለማርካት ፀብን እየዘሩ ጥላቻን እያጎረሱ የሚኖሩ መንደርተኞች ልንታገላቸው ይገባል:: ጨለማው እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው በመረዳት የእኩይ ተልዕኳቸው ማስፈፀሚያ እንዳንሆን ማስተዋልና ጥንቃቄን መታጠቅ ግድ ይላል።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መሆኑ ከታመነ፣ ወደዚያ የሚያደርሰውን ውስብስብና አባጣ ጎርባጣ የበዛበትን መንገድ በጋራ ማስተካከል የግድ ይላል:: ለውጡ በሚፈለገው ፍጥነት ተጉዞ ግቡን መምታት የሚቻለው፣ የተለያዩ አጀንዳዎችን የሰነቁ የዴሞክራሲ ኃይሎች ጥርጊያውን ለማመቻቸት በጋራ ሲጥሩ ነው:: ከምንም ጉዳይ በፊት ቅድሚያ ለሰላምና ለመረጋጋት መስጠት ይገባል:: በየቦታው የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን ተባብሮ ማስቆምና አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብም ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው::
በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አማካይነት በሐሰተኛ ማንነቶችና በግላጭ የሚፈበረኩ ሐሰተኛ መረጃዎችንና ለብጥብጥ የሚጋብዙ ቅስቀሳዎችን ማስቆም ይገባል:: ከምክንያታዊነት ይልቅ ለስሜታዊነት የተጋለጡ ወጣቶችን ደም እያንተከተኩ ወደ ጥፋት መንዳት በፍጥነት ካልተገታ ለውጡ ለቀልባሾች ይመቻቻል:: በስንት መስዋዕትነት የተገኘ አጋጣሚ መክኖ ለፀፀት ከመዳረግና አገርን ቀውስ ውስጥ ከመክተት በፊት ቆም ብሎ ማሰብ አስፈላጊ ነው::
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ይጠብቃል:: ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስህተቶችን እያመነዠኩ በሌላ መንገድ እነሱን ለመድገም መሞከር ትርፉ ውድቀት ነው:: በሠለጠነ መንገድ መቀራረብ፣ መነጋገርና መደራደር የሚጠቅመው የተሻሉ ሐሳቦች እንዳይባክኑ ነው:: የላቀ ሐሳብ ተጨምቆ የሚወጣውና አሸናፊ የሚሆነውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው:: የሐሳብ እጥረት ያለበት ሌላውን አደናቅፎ አገርን ከሚያተራምስ ወደ ውስጡ ቢመለከት ይበጀዋል::
መንግሥትም በኢትዮጵያ ለውጥን እውን በማድረግ ሂደት ከአዲስ የለውጥ አስተሳሰብ ጋር ለማራመድ አቅምና ፍላጎት የጎደላቸው አመራሮችን መለማመጥና መታገስ አይገባውም:: አዲሱን አስተሳሰብ ለማራመድ አቅምና ፍላጎት የጎደላቸው ተቋማት፣ መዋቅሮችና አሠራሮች ማደስ አሊያም መተካት የግድ ይላል::
የፓርቲ አባልና አመራሮችም ኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የተቃና ለማድረግ የሚችል ዝግጁነት አቅምና ቆራጥነት እንዲሁም ከፍተኛ የማስፈጸም ብቃት ያላቸው፤ ከሁሉም በላይ የሕዝብ ምሬት መነሾ ከሆነው ሌብነት የጸዱ መሆናቸውን በየጊዜው ማረጋገጥ ግድ ይለዋል:: ፓርቲው የተሻለች ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት ዜጎቹን የሚያከብር፣ ዝቅ ብሎ የሚያገለግል፣ አድሎአዊ አሠራርን የሚጸየፍና ሁሉንም በእኩል መመልከት የሚችል አመራር መፍጠርና ማስተዋወቅም እንዲሁ::
በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው ከሕዝብ ደኅንነትና ከአገር ህልውና የሚቀድም የለም:: ይህ እንደመሆኑም የዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ በሰላም የመኖር፣ የመሥራትና የመንቀሳቀስ መብት በተጨባጭ ማረጋገጥ ይገባል:: ግጭት ጠንሳሽና ጠማቂዎች በፈጠሯቸው ችግሮች የተጎዱና የተፈናቀሉ ሕዝቦችን የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በሚያጠናክር መንገድ በዘላቂነት ዳግም የሚቋቋሙበትና ከችግር ወጥተው ወደቀድሞ ሕይወታቸው የሚመለሱበት መንገድ መዘርጋት ያስፈልጋል:: የሰማዕታቱን ቤተሰቦችም በቋሚነት በማገዝ ጉዳታቸውን መካፈል ያስፈልጋል::
ኢኮኖሚ ለሁሉም ነገር መሠረት ነው:: ኢኮኖሚ ካደገ ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል:: ሥራ አጥነት ይቀንሳል:: ፖለቲካዊ መረጋጋት ይመጣል:: የውጭ ጣልቃ ገብነት ይቀንሳል:: ከውጭ ተጽእኖ መላቀቅና ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን መፍጠር የሚቻለው ኢኮኖሚን ማሳደግ ሲቻል ነው:: ጠላት የሚፈታተነን የኢኮኖሚያዊ አቅማችን የደከመና የእርስ በእርስ ትስስራችን መድከሙን ሲታዘብ ነው:: ስለሆነም በሁለንተናዊ መልኩ የኢኮኖሚ አቅማችን ማሳደግ ለነገ የማይባል ተግባር መሆን አለበት::
ምንም እንኳን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ቢኖረውም በተለይ ሕዝቡን ያለ ልዩነት ቀስፈው በመያዝ እያሰቃዩ የሚገኙ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ ዕድል መጥበብ፣ የዋጋ ግሽበት፣ የመሠረታዊ ሸቀጦች ዕጥረት ከአጭር ጊዜ አኳያም ቢሆን ፈጣን መፍትሄ መስጠት የግድ ይላል::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም