ጠቅላይ ሚኒስትራችን በቅርቡ እንዳሉን ኢትዮጵያችን በብዙ እየተለወጠች ትገኛለች:: ብዙም ርቀን ሳንሄድ ተቋም እንገንባ ብለን የተነሳንበት ሀሳብ የደረሰበትን ደረጃ ብናይ ጥሩ እመርታን እያሳየን ነው:: አሁን ላይ ከለውጡ ዓመታት በፊት በድክመት እየፈረጅን ስንገመግማቸው የነበሩ ተቋሞቻችን እንደገና በመዋቀር በሪፎርም ማለፋቸው ከላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጀምሮ ታች እስከ ወረዳ ድረስ የውጫዊና የውስጣዊ አካል ግንባታቸው ብቻ ሳይሆን አሠራራቸው በእጅጉ ዘምኗል፤ በቴክኖሎጂም ተቃኝቷል::
ለአብነት ያህል የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ)ን ብንወስድ መረጃንና ኮምፒዩተርን መሠረት ያደረጉ የቁልፍ መሠረተ ልማቶችን ደህንነት የተመለከተ ኃላፊነቱን በመወጣት ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል:: በተመረጡ ድንበር ዘለል የብሔራዊ ደህንነት ስጋት እንቅስቃሴዎች ዙሪያ መረጃ የመሰብሰብ፣ የመተንተን እና ለሚመለከተው አካል የማቅረብ ተግባሩን እንዲሁም የብሔራዊ መረጃ አሰጣጥ፤ አያያዝና አሰባሰብ አሠራርን እንደ አገር ማዘመን ችሏል::
የሳይበር ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር ሂደት ለፖሊስ እና ሌሎች በሕግ ስልጣን ለተሰጣቸው አካላት ትብብር በማድረግ እና ድጋፍ በመስጠቱ ረገድም ብዙ መራመድ ችሏል:: ተቋሙ ኢትዮጵያን የሚመጥን እንዲሆን ከማስቻል ጀምሮ ባለሙያዎችን ከልጅነታቸው ጀምሮ በብቃት ለማፍራት እያደረገ ያለው ጥረት ቀላል አይደለም:: ቢያንስ ዘመናዊ አሠራርን መሠረት ያደረገ ርዕይ ያላቸውን ትውልዶች ኮትኩቶ በማሳደግ አገሪቱ የተሻለች የምትሆንበትን አቅጣጫ አመላክቷል::
ኢንሳ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋምና የሰው ኃይል ለመፍጠርም የራሱን መሠረት የሚጥል ተግባር መከወን ችሏል:: በቴክኖሎጂ መስክ ማሳያ እንጨምር ከተባለ ብዙ ምሬትና እሮሮ ሲሰማባቸው የነበሩት ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች አሠራራቸውን በማዘመን ሕዝቡን ሆድ እያስባሰ ቅሬታ እንዲያመነጭ ከሚገፋ የማኑዋል አሠራራቸው ተላቀው ዲጂታል መታወቂያ አዘጋጅቶ እስከማቅረብ የደረሰ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችልና መልካም ደረጃ ላይ መድረሳቸውን መጥቀስ ይቻላል/በአፈጻጸም ያሉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ::
እንደ አገር ብዙ በቴክኖሎጂ የዘመኑ የአሠራር ለውጦች አሉ:: ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ መፍታቷም አንዱና ትልቁ ለውጥ ነው:: አገራችን በዚህ አካሄዷ አሁን ላይ የእርስ በእርስ አለመግባባት የወለደው ግጭትና ጦርነት ለሕዝቦቿ በፍፁም ስጋት እንደማይሆን በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል ማረጋገጥ ችላለች:: የገጽታ ግንባታን ተንተርሳ ሳታሰልስ በመሥራቷ በውጭው ዓለም ያላት ተደማጭነት እንዲጨምር፤ እይታው ሚዛናዊ እንዲሆን ለማድረግም በቅታለች::
ይህም ሆኖ ግን ለውጧ ለአንዳንዶቻችን ዜጎቿ ፈፅሞ የታየን አይመስልም:: ለምን እና እንዴት? ቢባል እየተለወጠች ባለች አገር ውስጥ ቁጭ ብለን መለወጧን ለማድነቅ የግድ የተለወጠ አስተሳሰብ ስለሚያስፈልገን ይመስለኛል:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅትም ይሄንኑ ነው ጠቆም አድርገው ለማለፍ የሞከሩት::
በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት እኔ ካልመራኋት ትፈርሳለች ብሎ ለሚያስብ ኃይል ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፤ ፈርሳለችም። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በውስጡ ያለ ሰው እንደ አገር ያሉ ተቋማት እንደተባለው በጥረትም በቴክኖሎጂም ያመጡትና እያመጡት ያለ ለውጥ መኖሩ፤ ለውጡ ዜጎች በሰፊው ከማድነቅ አልፈው ከአህጉረ አፍሪካ የሚቀናበት መሆኑ መቼም ባይታየው አይገርምም::
ሌላው ቀርቶ በራሱ በተቋማቱ ቁጥር መበራከት ባያምንም ቀድሞውንም አስተሳሰቡ አእምሮውን ዕውነታውን እንዳያምን አድርጎ ስለዘጋው ብዙም የሚያስደንቅ አይሆንም:: ወደ በጎ የሚመራውን ቀና ቀናውን መንገድ ወደ ጎን እየተው ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ ቢያስጉዘውም ምንም ላይመስል ይችላል:: ጉዞው ራሱን በሥጋት ቢንጠውና ዓይኑን ዕውነታውን ከማየት ቢጋርደውም አስተሳሰቡ እየተለወጠች ካለችው አገሩ ጋር መለወጥ አልቻለምና የሚጠበቅ እንጂ አዲስ ጉዳይ አይሆንም::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከአሮጌው አስተሳሰብ ወጥቶ አገሩ ወዳለችበት ወደ አዲስ አስተሳሰብ ቅኝት መሸጋገር ያልቻለ ሰው የምትበለፅግ፣ የምትፀና፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የምታልፍ፣ ይበልጥ የምትቀራረብ ኢትዮጵያ ዕውን በመሆኗ አስተሳሰብ ላይስማማ አስተሳሰቡም ሊጎረብጠው ይችላል:: ያልተለወጠው አስተሳሰባቸው፤ ሌሎች ሊለወጡ የሚችሉ በርካታ ሰዎችን አስተሳሰብ ስለሚበርዝ የግድ አስተሳሰባቸውን መለወጥ መቻል አለባቸው::
ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተለወጠች ካለችው አገራቸው ጋር አስተሳሰባቸው ያልተለወጠ አንዳንድ ሰዎችን አፍንጫን የሚሰነፍጥ ሽታ በባህርይው በጣም በርቀት ሄዶ መረበሽ ከሚችል እና መልካም መዓዛ ያለው ቀረብ ካላሉት በስተቀር ካለመሽተቱ ምሳሌ፤ እንዲሁም በብርጭቆ ውሃ ከተሞላና ካልተሞላ ፊዚክስ ቀመር ጋር በማመሳሰል የገለፁት::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሳሌውን የመሰሉት መልካም መልካሙን አይቶ እንዳላዩ በማለፍ ክፉ ክፉን እያስተዋሉ ለሚያሰፉት እና ‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ› እንደሚሉት ተረት አሁኑ ካለው መንግሥት የላቀ አስተሳሰብ ያለው በሌለበት/በምርጫ አሸንፎ ወደ ስልጣን የመጣው የተሻለ አስተሳሰብ ለሕዝብ ሸጦ ስለሆነ/ ሁኔታ የመንግሥት ለውጥ ለሚናፍቁና አገራቸው እያመጣችው ባለው ለውጥ አስተሳሰባቸውን መለወጥ ላልቻሉም አንዳንድ ወገኖች ነው:: በእርግጥም እንዲህ ዓይነት ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት መስከንና ነገሮችን በማስተዋል ማየት ይኖርባቸዋል::
የኑሮ ውድነቱ፤ ብር የመግዛት አቅሙ መድከሙ፤ የሰላም እጦቱ፤ ሌላው ሌላውና በሂደት እንጂ በአንድ ጊዜ ልንሻገረው የማንችለው ችግሮች ናቸው፤ እነዚህ ዓይኖቻችንን ጋርደው፤ ጉሮሯችንንም ሰቅዞ ይዘው ለውጧን እንዳናስተውልና እንዳንናገር ካላደረን በቀር እድገቷን መካድ አይቻለንም:: በእርግጥ እድገቷ በነፍስ ወከፍ ለሁላችንም ሲካፈል ድርሻችንን ላናገኝ እንችል ይሆናል:: ሆኖም እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ እየተለወጠች ላለች አገር የተለወጠ አስተሳሰብ ሊኖረን ግድ ነውና አስተሳሰባችንን እንለውጥ።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም