
ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሲቪል አቭየሽን ባለስልጣን ዳይሬክቶሬት ጄኔራል የነበሩት አቶ ተፈራ መኮንን የአፍሪካ ሲቪል አቭየሽን ዋና ጸሀፊ በመሆን ተመረጡ፡፡
ድርጅቱን ለመምራት አገራችን ያቀረበችው ዕጩ መመረጡ ለቀጠናው የሚኖረው ፋይዳ ቀላል አይሆንም፡፡
ድርጅቱ ትናንት ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም በዛምቢያ ሊቪንግስተን ውስጥ ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ በዕጩነት ያቀረበቻቸውን አቶ ተፈራ መኮንን በመምረጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደስታውን ይገልጻል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ኢትዮጵያዊው ተፈራ መኮንን እንዲመረጡ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፤ በዚህ መሰረት በቅርቡ በተጠናቀቀው 11ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ልዩ ጉባኤ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ገዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከአፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር በመገናኘት ግለሰቡ ብቸኛ ተመራጭ እንዲሆኑ የማግባባት ሰፊ ስራ ሰርተዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ፣ አፍሪካውያን ወገኖቻችን ለኢትዮጵያ ላሳዩት የመተማመን መንፈስ እና ላሳዩት ወገንተኝነት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዜጎችን በዓለም አቀፍ ወሳኝ ቦታዎች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንዱ እና ዋነኛ ስራው ነው፡፡ ዜጎች በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የኃላፊነት ቦታ እንዲይዙ በማድረግ ለአገራቸው ብሎም ለአፍሪካ አገራት ጥቅም መጠበቅ ሰርተዋል፡፡
አፍሪካ የሲቪል አቭየሽን እ.ኤ.አ. በ1964 በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ እንድነት ድርጅት ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ስራውን የጀመረው በ19 69 ነው፡፡
የሲቪል አቭየሽኑ መቀመጫም በሴኔጋል ዳካር ከተማ ነው፡፡
አቶ ተፈራ መኮንን በአቭየሽን ስራ የ37 ዓመት ልምድ አካብተዋል፡፡ በኬኒያ ናይሮቢ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቬየሽን ድርጅት ፕሮጀክት ማኔጀር በመሆን እንዲሁም በአፍሪካ የሲቪል አቪየሽን ትራንስፖርት ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት እንዳስታወቀው በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ በመሆንም ለስምንት ዓመታት ያክል በካናዳ ሞንቴሪያል ሰርተዋል፡፡