ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የየመን ተፋላሚ ሀይሎች ለሰላማዊ መፍትሄ ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡
“ጦርነት መሰረታችሁን፣ ግንኙነታችሁን፣ መልካምነታችሁን ያጠፋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከጦርነት የሚገኘው ጥፋት ብቻ ነው ሲሉ ለተፋላሚዎቹ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
“በአንድ መሬት ላይ በሚኖር የአንድ ሀገር ህዝብ እንዲህ አይነት ነገር እንዴት ይከሰታል? ሀገራችሁን በምታወድሙበት ጊዜ የመን ለምን እየተዋጋች ነው የሚለውን ለምን አታስቡም? ከጦርነት እና ግጭት ቋንቋ ይልቅ በንግግር የማመን ቋንቋን ለምን አታስተምሩም ?” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
ያለምንም ደም መፋሰስ እና ጦርነት በነገሮች ላይ አለመግባባት እና መግባባት እንደሚቻል ምክረ ሀሳባቸውን የለገሱት ዶ/ር አብይ አህመድ የመን ላለችበት ነባራዊ ሁኔታ ተፋላሚዎቹ ሀላፊነት እንደሚወስዱና ተጠያቂም እንደሚሆኑ በመልዕክታቸው ገልፀዋል፡፡
የየመንን ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም እጅ ለእጅ ሊያያዝና በጋራ ሊሰራ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከግል ፍላጎት ይልቅ ለሀገር የሚጠቅም መልካም ስራ መስራት እንደሚጠበቅም ጥሪ አቅርበዋል።
በጦርነት ጉዳት የደረሰበትን የየመን ህዝብ ለመካስ ተፋላሚ ሀይሎቹ ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እንዲፈቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ ቤት መግለጫ ያመለክታል።