በመዲናዋ አንድ ሺህ 392 ኪ.ሜ የሚሸፍን የመንገድ ግንባታና የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ በ24 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር፣ አንድ ሺህ 392 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ እና የጥገና ሥራዎች መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሙህዲን ረሻድ፣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ በ2017 በጀት ዓመት 371 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ እንዲሁም አንድ ሺህ 21 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል።

እነዚህ የመንገድ ግንባታ እና ጥገና ተግባራትም በመንገድ ልማት ዘርፍ የከተማውን የመንገድ መረብ ሽፋን ከማሳደር ባሻገር፤ የከተማዋን የመንገድ ደህንነትን የሚያረጋግጡ እና የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሳልጡ ናቸው። በተጨማሪም፣ ለኢንቨስመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ፤ የጉዞ ጊዜንና ገንዘብን የሚቀንሱም ናቸው።

እንደ ኢንጅነር ሙህዲን ገለጻ፤ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ የግንባታ ሥራዎች 69 ነጥብ አራት ኪሎ ሜትሩ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሲሆን፤ 95 ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትሩ ደግሞ የጌጠኛ ድንጋይ (የኮብል ስቶን) መንገድ ግንባታ ነው። 16 ነጥብ አንድ ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ፣ 107 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ እንዲሁም ሦስት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ እና የድሬንጅ ግንባታዎችን ተከናውነዋል።

በተመሳሳይ ባለሥልጣኑ 110 ኪሎ ሜትር የአስፓልት፣ 29 ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር የኮብል፣ 19 ነጥብ ዘጠኝ የእግረኛ መንገድና የኮብል ስቶም፣ 22 ነጥብ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የጠጠር፤ እንዲሁም 483 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅ መስመር ጥገና እና ጽዳት ሥራዎች ተከናውኗል።በተጨማሪም፣ 347 ኪሎ ሜትር የመንገድ ቀለም ቅብ ተከናውኗል።

የአንድ ወር የጥገና ዘመቻ በማድረግ በክረምቱ ተጎድተው የነበሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በመጠገን የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥ መቻሉን የጠቆሙት ኢንጅነር ሙህዲን፤ ለእዚህ ሥራ በአጠቃላይ 24 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል።

ኢንጅነር ሙህዲን አይይዘው እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ 84 ሺህ 250 ካሬ ሜትር የሚሆን የፓርኪንግ፣ የባስና የታክሲ መጫኛና ማውረጃዎችን ያካተተ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ተከናውኗል።

በግንባታ ላይ የነበሩ ዘመናዊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የቃሊቲ-ቂሊንጦ እና የቃሊቲ-ቱሉዲምቱን ጨምሮ፤ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውና ከ31 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት እና ከ15 እስከ 60 ሜትር የጐን ስፋት ያላቸው 13 የመንገድ ፕሮጀክቶችን እና ስምንት ድልድዮችን በአጠቃላይ 21 ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።

የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ከመገንባትና ከመጠገን በተጫማሪ በበጀት ዓመቱ 56 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍኑ የ21 የዋና ዋና መንገድ ዲዛይን ሥራቸው መጠናቀቃቸውን ኢንጅነር ሙህዲን ጠቁመዋል።

በሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You