
አዲስ አበባ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ849 ሺህ ሄክታር በላይ ለመኸር እርሻ እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ፣ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመኸር እርሻ የተለያዩ ሰብሎች ለማልማት በማቀድ የማስጀመሪያ መድረኮች ተካሂደዋል። በእዚህም ከ849 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት በቋሚ እና በዓመታዊ ሰብሎች ለመሸፈን ወደ ሥራ ተገብቷል።
ክልሉ የበልግ አምራች መሆኑን የጠቆሙት አቶ አድማሱ፤ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ68 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ከእዚህ ባሻገር ግን ክልሉ ከ738 ሺ ሄክታር መሬት በላይ ዓመታዊ ሰብሎች የሚለማበት አካባቢ እንደመሆኑ፤ በበልግ የተሸፈነውን ምርት በማንሳትም አሁን ላይ ከ170 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የመኸር እርሻ መታረሱን ገልጸዋል።
እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ፤ ለክልሉ የግብርና ሥራ ግብዓትን ከማቅረብ አኳያ ከ110 ሺህ ኩንታል በላይ የዳፕ ማዳበሪያ፣ እንዲሁም ከ60ሺ ኩንታል በላይ የዩሪያ ማዳበሪያ ገብቷል። ይሄም ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ይገኛል። ግብዓቶችን በመጠቀም በዋናነት ጤፍ፣ ቦሎቄ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ እና ገብስን የመሳሰሉ ሰብሎች የታረሰውን መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሠራ ይገኛል።
በ2018 ዓ.ም ክልሉ ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አድማሱ፤ በራስ አቅም ለማምረት ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ እስከ ዞንና ወረዳ ድረስ የንቅናቄ መድረክ በማዘጋጀት የደረሱ ሰብሎችን በማንሳት የታረሱ መሬቶችን በሰብል የመሸፈኑ ሥራ በትኩረት እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ለእዚህም ክልሉ በመኸር እርሻ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ ቶሎ እንዲደርስ አመራሩ በትኩረት እንዲሠራ፤ ቀደም ሲል የተዘሩ እና ያልተሰበሰቡ የበልግ ሰብሎችንም ቶሎ በማንሳት ወደ እርሻ በመግባትም በመኸር ሰብሎች እንዲሸፈን ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
አሁን ላይ በክልሉ የተወሰነ የዝናብ እጥረት መኖሩን የጠቀሱት አቶ አድማሱ፤ በተለይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ላይ በማተኮር እና ውሃ በማቆር፤ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ አሠራሮችን በመንደፍ አርሶ አደሩን የማንቃት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።
በሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም