አካል ጉዳተኞችን በፈጠራ የማገዝ ትጋት

አቶ ተሾመ ግርማ ይባላል። የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን የሠራ ባለሙያ ነው። አብዛኞቹ የፈጠራ ሥራዎቹም በአካል ጉዳተኞች ማዕከል ያደረጉ ናቸው። የእዚህ መነሻ ምክንያቱ ደግሞ በአካባቢው በቅርበት የሚያውቃቸው አካል ጉዳተኞች በዕለት ተዕለት ኑሮአቸው የሚያጋጥማቸውን ችግሮች መመልከቱ ነው። እናም የፈጠራ ክህሎቱና ችሎታውን ተጠቅሞ ለችግራቸው መፍትሔ ይሆናሉ ያላቸውን ሦስት ፈጠራዎች ሠራ።

አንድ የፈጠራ ባለሙያ በአካባቢው ያሉ የኅብረተሰቡ ችግሮችን በደንብ ለይቶ በማወቅ ሙያዊ መፍትሔ ማመንጨት ይጠበቅበታል የሚለው አቶ ተሾመ፤ እርሱም ይሄንኑ መነሻ በማድረግ የፈጠራ ሥራዎችን ማከናወኑን ይገልጻል። ለአብነትም፣ አካል ጉዳተኞች የሚጠቀሙባቸው በተለይም ኤሌክትሪክ ዊልቸሮች ረጅም ጊዜ ስለሚያገለግሉ ባትሪው መቀየር በሚያስፈልገው ጊዜ በሀገር ውስጥ ስለማይኖር መቀየር እንደማይችሉ በመጠቆም፤ በእዚህ የተነሳ ሲቸገሩ መመልከቱን ይናገራል።

የኤሌክትሪክ ዊልቸር የሌላቸው ደግሞ ማኑዋር ዊልቸር እየገፉ እንደሚጓዙ ገልጾ፤ እርሱም የፈጠራ ሥራዎቹን ሲጀምር እነዚህን ሁሉ ችግሮች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆኑን ያስረዳል።

በኢትዮጵያ ይሄ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች አሉ የሚለው አቶ ተሾመ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ የሚጠቀሙበት ማነዋል ዊልቸር ምክንያት ብዙ ጊዜ ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረጉ ማስተዋሉን ይገልጻል። ይህን ታሳቢ በማድረግም ለእነዚህ አካል ጉዳተኞች ተስማሚ የሆኑ፤ የሀገሪቱንም ነባራዊ ሁኔታዎች ከግንዛቤ ያስገቡ ሦስት የፈጠራ ሥራዎች መሥራቱን ይገልጻል።

አቶ ተሾመ እንዳብራራው፤ የመጀመሪያው የፈጠራ ሥራው ባለሦስት እግር ትራይሳይክል ነው። ይሄም አንድ ጊዜ ቻርጅ ከተደረገ በኋላ አርባ ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ ይችላል። የሀገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎም የሠራው ነው። ለምሳሌ፣ ከመሬት ከፍ ያለ ሲሆን፤ እግሩም ከፍ ተደርጎ የተሠራ ነው። ብዙ ቦታም የማይፈጅ ነው። ውሃ እንዳያስገባ ተደርጎም በመሠራቱ በክረምት ወቅት ያለምንም ችግር ማገልገል ያስችላል። ለቀን ብቻ ሳይሆን ለማታም ማገልገል የሚችሉ የተለያዩ ምልክቶች ተገጥመውለታል።

ሁለተኛው የፈጠራ ሥራው ደግሞ፣ ማነዋል ዊልቸርን ወደ ኤሌክትሪክ ዊልቸር ለመለወጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው። የትኛውም ማንዋል ዊልቸር ላይ ከፊት ብቻ ተገጥሞ ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር የሚያስችል ነው።

ለእዚህ ተግባር የሚውለው ቴክኖሎጂም ባትሪዎቹም በሀገር ውስጥ ራሱ እንደሚያመርት የሚገልጸው አቶ ተሾመ፤ ባትሪው በዊልቸሩ ላይ ለአካል ጉዳተኞች እንዲመቻቸው ተደርጎ የተገጠመ በመሆኑ ባትሪውን ለመሙላት (ቻርጅ) ለማድረግ ነቅሎ በመውሰድ ጭምር መሙላት የሚቻል መሆኑን ተናግሯዋል።

ዊልቸሩን የሚጓዝበት ርቀት (የፍጥነት ወሰን) የደንበኞች ፍላጎት መሠረት አድርጎ መሥራት እንደሚቻል ጠቅሶ፤ ደንበኛው በዊልቸሩ በሰዓት ምንያህል ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደሚፈልግ ሲገልጽ፤ ከፍጥነቱ ጋር በማመጣጠን የሚሠራ መሆኑን ያመላክታል። ከእዛ ውጪ ቴክኖሎጂው ዊልቸሩን በማንዋል ወይም በኤሌክትሪክ አድርጎ መጠቀም እንደሚቻልም ይገልጻል።

አቶ ተሾመ እንደሚያስረዳው፤ ሦስተኛው የፈጠራ ሥራው የታማሚዎች ማንቀሳቀሻ ወንበር (ፔሸንት ትራንስፈር ቼር) ነው። ይሄ ወንበር በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባን ምርት ለማስቀረት በማሰብ የተሠራ ነው። ወንበሩ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን፤ በተለይ ለሆስፒታሎች አገልግሎት የሚሰጥ ነው። እንደ መቄዶንያ ያሉ በጎ አድራጎት ድርጅቶችም ለአረጋውያኑ ሊጠቀሙበት የሚያስችላቸው ነው።

ይህ የፈጠራ ሥራ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉ ታማሚዎችን ለማንቀሳቀስ ከማስቻሉ ባለፈ፤ ታማሚው መጸዳዳት ሲያስፈልገው በቀላሉ ተቀምጦ እንዲጸዳዳ ለማድረግ ያስችላል። በሆስፒታሎችም ከአልጋ ወደ ኦፕራሲዮን ክፍል ወይም ከኦፕራሲዮን ክፍል ወደ አልጋ ክፍል፤ ወይም ወደ ሌላ ወደተፈለገበት ቦታ በቀላሉ ለማንቀሳቀስ ምቹ ስለመሆኑም ነው አቶ ተሾመ የሚያስረዳው።

በተለይ የመጀመሪያና ሁለተኛው የፈጠራ ሥራዎች በገበያው ላይ ዋጋቸው በጣም ውድ እና በሀገር ውስጥ የሌሉ በመሆናቸው ከውጭ በከፍተኛ ዶላር የሚመጡ ናቸው የሚለው አቶ ተሾመ፤ እነዚህ ዊልቸሮች ሀገር ውስጥ በቀላሉ ማምረት የሚቻል ቢሆንም ዊልቸሮቹን ለመሥራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከውጭ ለማስገባት የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻል። በመሆኑም መንግሥት ከሚያስገባቸው የማምረቻ ግብዓቶች ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል። ይሄ ሲሆን የአካል ጉዳተኛው ዊልቸሮቹን የመግዛት አቅም ያገናዘቡና ተመጣጣኝ ዊልቸሮችን አምርቶ ለማቅረብ እንደሚያግዝ አስረድቷል።

አቶ ተሾመ፣ አሁን ላይ ግሪን ቴክ ኢንጂነሪንግ ፒኤልሲ የተሰኘ ድርጅት መስርቶ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። በቀጣይ እነዚህ ዊልቸሮችን በማምረት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግ እቅድ እንዳለው ተናግሯል።

በወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You