የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች የበጋ ወራት ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ

ከስድስት ወራት ለበለጠ ጊዜ በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ፉክክሮችን ሲያስተናግድ የቆየው የ2017 ዓ.ም የሠራተኞች የበጋ ወራት ውድድር ከትናንት በስቲያ ፍፃሜ አግኝቷል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንም አጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል። ኢትዮ ቴሌኮም የፀባይ ዋንጫ አሸናፊ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ደግሞ የሽብርቅ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።

እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቮሊቦል፣ ጠረጴዛ ቴኒስን ጨምሮ በተለያዩ አስር የስፖርት ዓይነቶች ከበርካታ ተቋማትና ድርጅቶች የተውጣጡ ከአንድ ሺ በላይ ሠራተኞችን ያፎካከረው የበጋ ወራት ውድድር በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በደማቅ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ሲጠናቀቅ፤ በሁለት ዲቪዚዮኖች በርካታ ቡድኖችን ያፎካከረው የእግር ኳስ ስፖርት ዋንጫ አሸናፊዎች ተለይተውበታል። በአትሌቲክስ የተለያዩ ርቀቶችና አዝናኝ በሆነው የገመድ ጉተታ ውድድርም አሸናፊዎች የታወቁበት የፍፃሜ ፉክክሮች ተካሂደዋል።

ጠንካራ ፉክክር በታየበት አንደኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዋንጫ ፍልሚያው የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶችን 4ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ አሸናፊ ሆኗል። በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ በቆየው የሁለተኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ የየምድቡ የነጥብ አሸናፊዎች ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ዋንጫውን ለማንሳት ተፋልመውበታል። በእዚህም ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የዋንጫው ባለቤት ሆኗል።

በሁለቱም ፆታ በአትሌቲክስ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን፤ በወንዶች ገመድ ጉተታ ውድድር የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች አንደኛ፣ ፋፋ ምግብ አክሲዮን ማህበር ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል። በሴቶች ደግሞ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎችና ፋፋ ምግብ አንደኛና ሁለተኛ ሆነው የፈፀሙ ቡድኖች ናቸው።

በሁለት ዲቪዚዮን የተካሄደው የወንዶች ቮሊቦል ውድድር ብርቱ ፉክክር ካስተናገዱ የሠራተኛው የበጋ ወራት ውድድሮች አንዱ ሲሆን፤ በአንደኛ ዲቪዚዮን ኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች በ16 ነጥብ ቀዳሚውን ደረጃ ይዞ አጠናቋል። አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በ11 ነጥብ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ አዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ በ7 ነጥብ ሦስተኛ ሆኗል። በተመሳሳይ በሁለተኛ ዲቪዚዮን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች በ12 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲፈጽም፤ ኢትዮ ቴሌኮም በ6 ነጥብ ተከታዩን ደረጃ ይዞ አጠናቋል። በሴቶች ቮሊቦል ደግሞ 20 ነጥብ በመሰብሰብ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች አሸናፊ ነው። አዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ 16 ነጥብ በመያዝ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀ ቡድን ነው።

ጥሩ ፉክክር ከታየባቸው የቤት ውስጥ ስፖርቶች መካከል በሁለት ዲቪዚዮን የተካሄደው የወንዶች ጠረጴዛ ቴኒስ ፉክክር በአንደኛው ዲቪዚዮን ኢትዮ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 22 ነጥብ በመሰብሰብ ቀዳሚ ሆኖ አጠናቋል። ብርሃንና ሰላም ማተሚያ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ ኢትዮ ቴሌኮም በተመሳሳይ 21 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሦስተኛ ሆኗል። የሁለተኛ ዲቪዚዮን ፉክክሩ 4 ነጥብ በያዘው ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ቀዳሚነት ሲደመደም፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ሁለተኛ ነው። በሴቶች ቮሊቦል አዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ በ20 ነጥብ አንደኛ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በ16 ነጥብ ሁለተኛ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ12 ነጥብ ሦስተኛ ሆነዋል።

አዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ በወንዶች ዳርት በ19 ነጥብ ቀዳሚ ሲሆን፤ መከላከያ ኮንስትራክሽን በ17 ነጥብ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ በ16 ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል። አዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ በሴቶች የዳርት ውድድርም በ12 ነጥብ ቀዳሚ ሲሆን፤ ኢትዮ ቴሌኮም በ8 ነጥብ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በ4 ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።

በወንዶች ከረንቦላ ውድድር ብርሃንና ሰላም አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ በዳማ ውድድር አዲስ አበባ የከተማ አውቶቡስ ቀዳሚ ሆኖ ፈጽሟል። በወንዶች ቼስ ውድድር ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም ቀዳሚ የሆነበትን ነጥብ ማስመዝገብ ችሏል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You