የፕሪቶርያዋ ነጭ ርግብ እንዳትበር

በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የቆየው ጦርነት እንዲያበቃ አድርጓል። ስምምነቱን ተከትሎ የሰላም አየር ሲነፍስ ከርሟል።

በፕሪቶርያ ስምምነት የተገኙ ስኬቶችን አስመልክቶ የአፈፃፀም ሪፖርት ውይይት በተካሄደበት ወቅት ተሰናባቹ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፉኪ ማህማት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አመርቂ መሻሻሎችና ውጤቶች መገኘታቸውን መስክረዋል። የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በበኩላቸው፤ የሰላም ሂደቱ ተሳታፊዎች ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን ሰላም ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነትን በማሳየታቸው ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥ የሰላም ሂደቱን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ነው። መንግሥት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት የሚያጠያይቅ አይደለም ብለዋል። በወቅቱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ እንዲሁ የሰላም ሂደቱ ስኬት የተመዘገበበት እንደሆነ በመጥቀስ የአፍሪካ ችግሮችን በአፍሪካውያን መፍታት እንደሚቻል በተግባር የታየበት ነው ብለው ነበር።

የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት እንዲህ ያሉ ውዳሴዎች ሲቀርቡለት ቢሰማም መሠረታዊ የሆኑ ቀሪ የቤት ሥራዎቹ እንዳሉትም ይነገርለታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ የሰላም ስምምነት በተመለከተ ባደረጉት ንግግር፤ የፕሪቶርያው ስምምነት መሠረተ ልማቶችን በመመለስ የትግራይ ሕዝብ አገልግሎት እንዲያገኝ አድርጓል ብለዋል። ያም ሆኖ አሁንም በበቂ ሁኔታ ያልተፈጸሙ ጉዳዮች አሉ። ከዚህም አንደኛው የታጣቂዎች ተሐድሶ (ዲዲአር) ሥራ ነው። ይህ በዋናነት የሚጎዳው የትግራይ ሕዝብን ነው። ወጣቶች በታጣቂ ስም ከመቀመጥ ወደ ልማት መሠማራት አለባቸው። በየወሩ ለልማት መዋል የነበረበት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለዚህ ሥራ ይወጣል። ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ ረገድም በራያና ጸለምት ጥሩ ሥራ ተከናውኗል። በሌሎች አካባቢዎች ግን በተፈለገው ልክ አልሆነም። ይህ የሆነውም ሰብዓዊ ሥራ እና ፖለቲካ የሚቀላቅሉ ኃይሎች በመኖራቸው ማለታቸው ቀሪ የቤት ሥራው ቀላል እንዳልሆነ ጠቋሚ ነው።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲህ ባለ መንታ መንገድ ላይ ባለበት ሁኔታ ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስምምነቱን የሚንዱ እንቅስቃሴዎች መስተዋል የጀመሩት። በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ፣ ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የመሩት ውይይት መካሄዱ ይታወሳል። በመድረኩ የፕሪቶርያ ስምምነት የትግራይ ሕዝብ ለዓመታት የተጠማውን ሰላም እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ውጤት የተገኘበት ነው ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በስምምነቱ መሠረት እንዲፈፀሙ የተቀመጡ ጉዳዮች የራስን የግል ጥቅም ብቻ በማስቀደም ሊሳኩ አልቻሉም። ዛሬም ቢሆን ቡድኑ የትግራይ መሬትን ዳግም የጦርነት ዓውድማ ከማድረግ ውጪ ዓላማ የለውም። ሕዝቡ የተገኘውን ወርቃማ ዕድል በመጠቀም ይህንን እኩይ ተግባር ሊቃወም እና ሰላሙን ማፅናት ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በዚሁ መድረክ የታደሙ የውይይቱ ተሳታፊዎች በትግራይ ክልል ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል ከሚል ስጋት ያለፈ ተጨባጭ መረጃ እንዳላቸው ከሰነዘሯቸው ሃሳቦች መረዳት ይቻላል። መሬት ላይ እየተደገሠ ያለውን እንደሚያውቅ እማኝ የቀድሞ የሕወሓት አባላት እያስተጋቡ ያሉት የጦርነት ይብቃ ውትወታ ጆሮ ይፈልጋል።

የእነዚህ ወገኖች የሰላም ጥሪ በጦርነት የተከፈለውን የደም ዋጋ በቅጡ ከመገንዘብ የመነጨ ነው። የጦርነት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ የሚነገርለት የሕወሓት አንጃ ትናንት በክልሉ ሕዝብ ላይ ዘግናኝ የጦር ወንጀሎችን ከፈጸመው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ጋር የፈጸመው ስትራቴጂካዊ ያልሆነ ታክቲካል ጥምረት ቆሜለታለሁ ከሚለው ሕዝብ የሚለየው መርሕ አልባ ጋብቻ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት እንዳያደናቅፍ ተሰግቷል።

ኢትዮጵያ ተዳክማለች ብሎ ባሰበ ቁጥር በውስጥ ጉዳይዋ ገብተው የሚፈተፍቱ ጠላቶቿን እኩይ ዓላማ በመደግፍ በራስ ወገን እና ሕዝብ ላይ ጦር ማዝመት ታሪክ ይቅር የማይለው ተግባር ይሆናል። የሰላምን ዋጋ ተገንዝበው “ጦርነት ይብቃ” እያሉ የሚገኙን የቀድሞ የሕወሓት አባላት፣ የክልሉ ምሑራን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ድምፅ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል። የሃሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት ውጭ ያለ አማራጭ ሁሉ አጥፊ መሆኑ በአፅንዖት መነገር ይኖርበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰሞኑ የፓርላማ ንግግራቸው፤ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ወደ ጦርነት እንዳይገባ አሁኑኑ የሰላም ሚናችሁን ተወጡ። መንግሥት አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለውም። መልማት ነው ፍላጎታችን። ሁሉም ሕዝብ ማወቅ ያለበት ጦርነት አያስፈልግም ማለታቸው የፕሪቶርያ ስምምነት የተደቀነበትን አደጋ ከማሳየት ባለፈ በዙ አንድምታዎች ያሉት ነው።

የትግራይ ሕዝብ ጦርነት ፈጽሞ እንደማይፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዓለምን ሁኔታና የዘመኑን ውጊያ ባለመገንዘብ፣ መንግሥት በተለያዩ ችግሮች ተወሯል፤ የሚያግዙን ሀገራት አሉ በሚል የተሳሳተ ስሌት ጊዜው አሁን ነው በሚል ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ አሉ። ይህ የተሳሳተ አካሄድ ነው ትግራይ የሚያስፈልገው ሰላም፣ ችግሮችን በውይይት በንግግር መፍታት ነው ሲሉ የመንግሥታቸውን መሻት አሳውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሃይማኖት አባቶች ያስተላለፉት ጥሪ “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” ዓይነት አካሄድ ይበቃል የሚል መልዕክት ያዘለ ነው። ትክክል ናቸው። የሃይማኖት አባቶች የአቋም መግለጫ ከማውጣት ያለፈ ሚና ሊኖራቸው ይገባል። ጦርነት ከመፈጠሩ በፊት መጓዝ ያለባቸውን ርቀት ተጉዘው ሰላምን መስበክ ይጠበቅባቸዋል። ከዚያ በመለስ የሚከታተል የመግለጫ ጋጋታ ተቋማቱ በሕይወት መኖራቸውን ከመግለጽ ባለፈ አንዳች ፋይዳ አይኖረውም።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በቅርቡ ባካሄደው ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ ላይ የተሳተፉት የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ተወካዮች እና የቦርድ አባላት ጉባኤያቸውን ያጠቃለሉት በተለመደው መንገድ ነው። “በተለያዩ አካባቢዎች ያጋጠሙንን አለመግባባቶች እና ግጭቶች በንግግር በመፍታት በሰላም እና በፍቅር በአንድነት ልንኖር ይገባል” የሚል የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። የሚነድ እሳትን ከብቦ በመወያየት ማጥፋት አይቻልም።

ሕወሓት መራሹ የቀድሞ መንግሥት ከተሳኩለት ሴራዎች አንዱ የኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ ዕሴቶቻችንን ጉልበት ቄጤማ ማድረግ ነው። የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች ዛሬም ድረስ ሰላምን በማስፈን ረገድ የሚጫወቱትን ቁልፍ ሚና እንዳይጫወቱ የሆኑት ሆን ተብሎ በተቀናጀ መንገድ የተቋማቱን ማኅበራዊ መሠረት ለመናድ ለዓመታት በተሠራ ሥራ ነው። ይህ መቀልበስ አለበት።

ሰላም ሚኒስቴር “ማኅበራዊ ሀብቶቻችን ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የሀገር ሽማግሌዎች እና የማኅበራዊ የሰላም ተቋማት አመራሮች የምክክር መድረክ በቅርቡ ማካሄዱ ይታወሳል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማፅናት እና ብሔራዊ መግባባትን ለማጎልበት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚናንን አስመልክቶ ባደረጉት ውይይት፤ የሀገር ሽማግሌዎች ሕዝብና መንግሥትን የሚያስታርቁ ገለልተኛ ሆነው ለዕውነት መቆም ይገባቸዋል የሚል ሃሳብ ተነስቷል። በመድረኩ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እንድሪስም፤ ሽምግልና ከሁሉም ነፃ የሆነ ተቋም ሊሆን ይገባል። የሀገር ሽማግሌዎች ከእኔነት ትርክት ይልቅ አሰባሳቢ ትርክት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

የዛሬዋ ኢትዮጵያ የምትሻው እንዲህ ያሉ የሃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ነው። ኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ ዕሴቶቻችን ችግር ከመፈጠሩ በፊት የምንድንባቸው መፍትሔዎቻችን መሆን መቻል አለባቸው። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የመንግሥትን ጥሪ ሳይጠብቁ ለሕዝባቸው ግድ እንደሚላቸው በተግባር ማሳየት መቻል አለባቸው።

ራሳቸውን “መንበረ ሠላማ” ብለው የሚጠሩት ከማዕከላዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ተነጥለው የራሳቸውን ሲኖዶስ የሰየሙት የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳትና አባቶች ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የሃይማኖት አባቶቹ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት በትግራይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በየፕሪቶርያ የተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት በትግራይ የተኩስ ድምፅን ማስቀረቱን በመግለጫቸው የጠቀሱት የሃይማኖት አባቶቹ፣ ከትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የትግራይን እውነተኛ ምስል እና የትግራይ ሕዝብ ምኞት ዘላቂ ሰላም መሆኑን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያስረዳ ልዑካን ቡድን ለመላክ መወሰናቸውንም አሳውቀዋል። በክልሉ ለሰላም የሁለት ቀናት ፆምና ጸሎት እንዲደረግም ጥሪ አድርገዋል።

በትግራይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶችና ጳጳሳት አቡነ ማትያስ ከሚመሩት ዋናው ቅዱስ ሲኖዶስ ተለይተው “መንበረ ሠላማ” የተባለውን ሲኖዶስ አቋቁመናል ያሉት፣ በጦርነቱ ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አጋርነቱን ማሳየት አልቻለም በማለት ነው። የሃይማኖት አባቶቹ ከማዕከላዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ጋር ያላቸውን ቅራኔ ባልፈቱበት ሁኔታ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ መንቀሳቀሳቸው ጥያቄ የሚያስነሳ ቢሆንም የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ መጀመራቸው ይበል የሚያሰኝ ነው።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተካሄደው ጦርነት መቋጨቱን ያበሰረችው የፕሪቶርያዋ ነጭ ርግብ በርራ ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መጥቷል።

በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራውን ሕወሓትን ‘ሕገወጥ እና ኋላ ቀር ቡድን’ በማለት የጠራው በቅርቡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅድመ እውቅና ምዝገባ ፍቃድ የተሰጠው በእነ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት መግለጫ የትግራይ ሕዝብ ወደከፋ ሁኔታ እያመራ ነው። ሕወሓት ሕገመንግሥት በመጣስ ከኤርትራ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈል ዝግጅቱን አገባዷል ሲል ከሷል።

ቡድኑ በአፋር በኩል ተደጋጋሚ ትንኮሳ እያደረገ መሆኑን የጠቆመው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት፤ ጦርነት ለማወጅ ጫፍ ላይ ያለ ቡድን ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ከመጠን በላይ ሊያስታምመው አይገባም ሲል ተማጽኗል። ኋላቀር ቡድን ባለው ሕወሓት ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ወደ ዳግም ጦርነት እንዳይገባ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዳይስተጓጎሉ እንደሚሰጋ ገልፆ፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነቱ ይወጣ ሲል ይፋዊ ጥሪ አቅርቧል።

የወቅቱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው በቅርቡ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል ስላለው ሁኔታ በሰጡት አስተያየት፤ በተሳሳተ አረዳድ እና ድምዳሜ ምክንያት ዳግም ጦርነት እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። ያሉ ልዩነቶች እና ያልተፈፀሙ የፕሪቶርያ ስምምነት ይዘቶች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ፍላጎት በትግራይ በኩል መኖሩን ገልጸዋል።

ጦርነት እጅግ መራር መሆኑን እንደ ሀገር በከፈልነው ውድ ዋጋ ተረድተናል። የፕሪቶርያዋ ነጭ ርግብ እንዳትበር ልዩነቶችን በሃሳብ ትግል በሰጥቶ መቀበል መርሕ መፍታትን ብቸኛ አማራጭ አድርገን መውሰድ አለብን። መጥፎ የሚባል ሰላም፤ ጥሩ የሚባል ጦርነት የለም!

በተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You