ክልሉ በበጀት ዓመቱ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶችን ተቀብሏል

አዳማ:- የኦሮሚያ ክልል በ2017 በጀት ዓመት ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ 20 ሺህ የሚደርሱ ባለሀብቶችን መቀበሉን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ኢድሪስ እንደተናገሩት፤ በሀገር ውስጥ ወደ ኢንቨስተርነት የተሸጋገሩ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን፤ አቅም የፈጠሩ አርሶ አደሮችና ዩኒየኖች እንዲሁም የውጭ ኢንቨስተሮችን ጨምሮ እንደ ክልል በጥቅሉ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘግቡ 20 ሺህ ያህል ባለሀብቶች በበጀት ዓመቱ ተቀብሎ ማስተናገድ ተችሏል።

እንደ አቶ አህመድ ማብራሪያ፤ ክልሉ በቀዳሚነት በበጀት ዓመቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ አቅሞችን መለየት እና የማስተዋወቅ ሥራ ሠርቷል። ይኼም የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያደርጉት ፍሰት በመጨመሩ፤ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ እና በግምት አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥሩ 20 ሺህ ያህል ባለሀብቶችን መቀበል ተችሏል።

በበጀት ዓመቱ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ ከሦስት ጊዜ በላይ በመገናኘት ከ12 ሺህ በላይ ኢንቨስትመንቶች ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረጉን የገለጹት አቶ ኢድሪስ፤ በበጀት ዓመቱ የነበረው የኢንቨስትመንት ፍሰትም ቀደም ሲል ከነበሩት ስድስት ዓመታት አፈጻጸም የሚበልጥ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

የኢንቨስትመንት መሬት የወሰዱ ግንባታ ወደ ግንባታ እንዲገቡ፣ ግንባታ የጨረሱም ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ የክትትልና የድጋፍ ሥራ መሠራቱን የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ በ2017 በጀት ዓመት ሦስት ሺህ 600 ኢንቨስትመንቶች ወደ ምርት እንዲገቡ ስለመደረጉም ተናግረዋል። ርምጃውም እንደ ጥሩ ውጤት ታይቷል ብለዋል።

አቶ አህመድ በማብራሪያቸው እንዳስረዱት፤ ተኪ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ለብቻ ተለይተው በተደረገላቸው ድጋፍና ክትትል ምርታቸውን ወደ ገበያ በማስገባት ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል። በአንጻሩም አበባን ጨምሮ ወደ ውጭ ገበያ ከተላኩ የሆርቲካልቸር ምርቶች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ በገቡ ኢንዱስትሪዎች በጊዜያዊና በቋሚነት ለ375 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል።

በበጀት ዓመቱ፣ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ዜጎችን፣ ክልሉንም ሆነ ባለ ሀብቱን ተጠቃሚ ማድረግ ስለመቻሉ ያስረዱት አቶ አህመድ፤ በተለይም አሠራሮችን በማዘመን የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስቀረት ሙከራ ስለመደረጉም ተናግረዋል። በእዚህም ሠራተኞች ዲሲፕሊን እንዲኖራቸውና አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ መደረጉን እና በየሦስት ወሩ ከባለሀብቱ ጋር እየተገናኙ በሚነሱ ቅሬታዎች ላይ ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

ከእዚህ በተጓዳኝ መሬት ወስደው አጥረው የተቀመጡ ባለሀብቶችም በተደረገላቸው ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ፈጥነው ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸውን የገለጹት የቢሮው ኃላፊው፤ ሥራዎችን በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ በማድረግም የኢንቨስትመንት ቅበላ ሰንሰለቱን ማሳጠር እንደተቻለም አስረድተዋል። ለእዚህም በፌዴራል ደረጃ ሥራ ላይ ከዋለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ልምድ በመውሰድ በአዳማ ከተማ፣ በሸገር ሲቲ እና በቢሾፍቱ ከተማ ሙከራ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You