
የፍርድ ቤቶች የክስ መዝገብ ላይ የታጨቀው ምን ይሆን ብለን ብንጠይቅ፤ ድሮም ቢሆን ዘንድሮ አንዳንድ ግርምትን የሚያጭሩ የመንደር አቤቱታና አሉባልታዎች ሁሉ ሰፍረው ልናገኝ እንችላለን፡፡ እንደ አንድ ግለሰብ እየተገረምንም ይሁን እንበል፤ አንድ ሃምሳ አለቃ የዶሮዬን እግር ሰበሩ ብሎ ፍርድ ቤት መካሰስን ምን ይሉታል? ባሕልና የማኅበረሰብ አኗኗራችን ያላመደን አለና ጉዳዩን ዘጋቢው ያትትልናል፡፡ አብዝቶ እዩኝ እዩኝ ማለቱ ኋላ ደብቁኝን ያመጣልና ሁለቱ ጓደኛሞች ‹እኔ ነኝ ጋባዥ› እየተባባሉ ሲሟገቱ ነገርዬው ከጸብም አልፎ ለመገዳደል ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ እኚህና ሌላ አንድ ሀሳብን ጨምሮ ለዛሬው ትውስታችን መርጠናቸዋል።
እግሯ የተሰበረ ዶሮ ጉዳይ ፍርድ ቤት ቀረበ
አንዲት ሴት ልጅ ንብረትነቷ የሃምሳ አለቃ ታደሰ አህመድ የሆነችውን ነጭ ዶሮ እሽ ብላ በጫማ ስትመታት ትሰበራለች። ሃምሳ አለቃው ዶሮዬ ተሰብራብኛለች ብለው ዘጠነኛ ወረዳ ፍርድ ቤት በልጅቷ ላይ የወንጀል ክስ ይመሠርታሉ ዳኛው የክሱን ቀላልነት አይተው ሃምሳ አለቃው ክሱን እንዲተው የዶሮዋን ዋጋ ሦስት ብር ከኪሳቸው አውጥተው ልክፈል ቢሉ ሃምሳ አለቃው “ነገሩ ተጣርቶ ፍርድ ቤት ካልተሰጠኝ በስተቀር አይደረግም” ይላሉ፡፡
ነገሩ ያስገረማቸው ዳኛው በበኩላቸው ሃምሳ አለቃው ዶሮዋ ለመሰበሯ የሃኪም ማስረጃ እንዲያመጡ ወይም የተሰበረችዋን ዶሮ ፍርድ ቤት ይዘው እንዲያቀርቡ ያዛሉ፡፡ የተመሠረተው ክስ መስመሩን በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ክርክሩ ይቀጥላል።
የዶሮ እግር ሰበረች ተብላ ክስ የተመሠረተባት ወ/ት በቀለች ታፈሰ 9ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርባ የእምነት ክህደት ብትጠየቅ የዶሮዋን እግር ያልሰበረች መሆኗን ብትገልጥም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ቀርበው ስለመሰከሩባት ጥፋተኝነቷ ተረጋግጦ ዳኛው የክሱን አመሠራረትና ሁኔታ መዝነው ውሳኔ እንዳስተላለፉ የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል።
በአዲስ አበባ ከተማ የዘጠነኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት አቶ ውበት ተፈራ ስለክሱ አመሠራረትና ክሱን ስለመሠረቱት ግለሰብ ሰፊ የሆነውን ትችት በሰጡት የፍርድ መዝገብ ላይ አስፍረዋል። መዝገቡ እንደሚለው «ተከሳሽ ዶሮ እሽ! ብላ በጫማ ወርውራ መምታቷ አድራጎቷ ትክክል ነው ባንልም የግል ተበዳዩ ግን ይህን ክስ በመመስረታቸው ፍርድ ቤቱን አሳዝኖታል። ምክንያቱም በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ከአንድ ወታደር ፖሊስ የማይጠበቅ ተግባር ነው በማለት ስለታመነበት ነው።
በአሁኑ የመሸጋገሪያ ጊዜ ከአንድ ሕጋዊ ፖሊስ የሚጠበቀው በሆነው ባልሆነው ፍርድ ቤት በክርክር የሚነታረኩትንና ወደ ክስ የሚሮጡትን ሰዎች መምከርና ማስተማር የሚገባው የሃምሳ አለቃ ታደሰ አህመድ አንድ ዶሮ ተሰበረች ብሎ ክስ ሲያቀርብ በሆነ ባልሆነው ክርክሩ ፍርድ ቤት መቅረብን ማስተማር ወይም መጋበዙን መረዳት ያለበትን በመዘንጋቱ ነው።
አንድ ዶሮ ስንል በዋጋዋ ማነስ ሳይሆን “ተከሳሽ ጫማ ወርውራ የዶሮዬን እግር ሰብራለች አሁን ግን ድናለች” በማለት ከሳሽ ያስረዳ ከመሆኑም በላይ በምስክሮቹም አንደበት የተመታችው ዶሮ እግሯ ድኖ እንደቀድሞዋ የምትራመድ መሆኗን ከመመስከራቸውም በላይ በችሎት ላይ ቀርባ ታይታለች።
ነገሩ ይህ መሆኑ ሲታወቅ የግል ተበዳይ ነኝ ባይ ሃምሳ አለቃ ክሱን ቢያነሱ ወይም ቢተውት ምን ይጎዳቸዋል? ለማለት ነው፡፡ ተከሳሽ ፈጸመች ስለተባለው የወንጀል ድርጊት የሚከተለው ውሳኔ የተሰጠ መሆ ኑን መዝገቡ ያስረዳል።
ተከሳሽ ምንም እንኳን የፈጸመችው የዶሮ ውርወራ በትር ትክክል ነው፤ ሸጋ አደረገች! ማለታችን ሳይሆን ክስ መሥራቹ ሃምሳ አለቃ የዶሮዋን መዳን አይቶ ክሱን ቢተው ኖሮ 1ኛ የመንግሥት ወረቀትና ቀለም፣ 2ኛ የሃምሳ አለቃው በየቀጠሮው በመመላለስ ያባከነው ጊዜና ለመንግሥት የሚያበረክተው አገልግሎት 3ኛ የፍርድ ቤቱን የሥራ ጊዜ ባላባከነ ነበር።
ወንጀል የተፈጸመባት ዶሮ ተከሳሿ ደጃፍ ብትገኝም ሕጋዊ በሆነ መከላከል እሽ! ብላ አቅሟ በሚችለው መጠን ማባረር ነበረባት እንጂ ዶሮዋ በማትችለው ሁኔታ ጫማ አንስታ ዶሮዋን በመደብደቧ በሁለት ምስክሮች የተመሰከረባት ስለሆነ ክሱ በቀረበበት የወንጀል ሕግ ቁጥር 753 መሠረት ጥፋተኛ በማለት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጥተናል።
ተከሳሻም በበኩሏ የፍርድ ቤቱን አስተያየት በመጠየቋ ዳኛው ሁኔታውን ተመልክተው የሰጡት ፍርድ ከእዚህ የሚከተለው ነው “ተከሳሽ በሃምሳ አለቃው ዶሮ ላይ የድብደባ በትር በማድረሷ ሕጋዊ ቅጣት መወሰን ሲቻል የነገሩን አነስተኛነትና ተመታች የተባለችውም ዶሮ ድና በመገኘቷና እንዲሁም ተከሳሿ በሌላ ወንጀል ተከሳ የማታውቅ መሆኑን ተገንዝበን በወንጀል ሕግ ቁጥር 87 ና 121 መሠረት ወደፊት ንብረቷ ያልሆነውን የሰው ዶሮ ወይም እንስሳ እንዳትደበድብ መክረንና ወቅሰን በእዚህ ማስጠንቀቂያና ወቀሳ ቅጣት አልፈን ተከሳሽን በማሰናበት መዝገቡን ዘግተን ለጽሕፈት ቤት ተመላሽ አድርገናል።”
( አዲስ ዘመን ጋሰኔ 12 ቀን 1968 ዓ.ም)
በመገባበዝ ተጣልተው ተጋደሉ
ሰውዬው ጓደኛውን ጋብዞት ሁለቱም ቁርሳቸውን ከበሉ በኋላ “እኔ እከፍላለሁ” “አይ እኔ እከፍላለሁ” በመባባል ተጣልተው ተጋባዡ ጋባዡን በጥይት የገደለው መሆኑን ከቤሩት የተላለፈልን ዜና አመልክቷል፡፡
ጠቡ የተነሳበትን ምክንያት ፖሊስ ሲገልጽ ጓደኛሞቹ አንደኛው ጋባዥ ሆኖ ወደ ሆቴል ቤት ገቡ፡፡ ከተመገቡ በኋላም ተጋባዡ እኔ እከፍላለሁ በማለት ስለተግደረደረ ጋባዡ ሰደበው፡፡ ወዲያውም በጥፊ መታው፡፡
ተመቺው ተጋባዥ ከሆቴል ቤት ሲሮጥ ወጥቶ ሽጉጥ ይዞ መጣ፡፡ ወዲያውም ጓደኛውን ገደለው ብሏል፡፡
(አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ መጋቢት 8 ቀን 1957 ዓ/ም)
የሥራና የሠራተኞች ክርክር
ሠራተኞች ነን የሚሉ ሁሉ ሥራ አጣን እያሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ፤ሥራ ደግሞ ሠራተኞችን አላገኘሁም እያለች በበኩልዋ ታማርራለች፡፡ የሆኖ ሆኖ ሥራ አልተራሁም ትል እንደሆን እንጂ መኖራቸው እርግጥ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንግዲህ ለማን ወይም በማን ይፈርደዋል? በሥራ ነውን ወይስ በሠራተኞች?
(አዲስ ዘመን ነሐሴ 13 ቀን 1974ዓ.ም)
በሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም