የቻይና ካምፓኒ ግንባታው በ2009 ዓ.ም የተጀመረው ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 የስኳር ፕሮጀክት 50 ሺህ ሄክታር መሬት የተዘጋጀለት ነው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ በቀን 24ሺ ቶን አገዳ ይፈጫል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመሆኑ ግንባታው በሚፈለገው ደረጃ እየሄደ አለመሆኑ ይነገርለታል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ጥር ወር አንድ ቡድን ወደ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1፣3 እና 5 ስኳር ፋብሪካዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል፡ ፡
የመስክ ምልከታ ሪፖርት ዙሪያ ቋሚ ኮሚቴው ከስኳር ኮርፖሬሽን የስራ ኃላፊዎችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰሞኑን ውይይት አድርጓል፡፡ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ መቋረጡንና የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ሰራተኞች መበተናቸውን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት እንደሚሉት ለፋብሪካው ግንባታ መከፈል የሚገባው ክፍያ በውሉ መሰረት ባለመፈጸሙ የፋብሪካው ግንባታ አፈጻጸም እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑም ባሻገር የግንባታው ስራ መቋረጡ ችግሩ ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል፡ ፡ በዚህም ምክንያት በተቀመጠለት እቅድ መሰረት እየሄደ አይደለም፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት 50 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ቢጠበቅም ገና 24 በመቶ ላይ ነው፡ ፡ ይህ ሊሆን የቻለው መከናወን ያለባቸው ተግባራት በጊዜው ባለመከናወናቸው ነው፤ በጣም አሳሳቢ ችግርም ነው ብሏል፡፡
ገንዘብ በጊዜው ቀርቦ የግንባታው ስራ አለመከናወኑ የኮርፖሬሽኑን እቅድ ከማዛባቱም ባሻገር፤ ሀገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓል ያለው ቋሚ ኮሚቴው፤የፋይናንስ ችግሩ በአፋጣኝ ተፈትቶ የፋብሪካው ግንባታ የማይጠናቀቅ ከሆነ የባንክ ወለድ እየተቆለለ ይሄዳል ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ የፋብሪካውን አዋጪነት አጠያያቂ እያደረገው የሚሄድ ነው፡፡ በመሆኑም ችግሩ በአጭር ጊዜው ውስጥ ተፈትቶ የተበታተነው የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት ሰራተኞች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ሊደረግ እንደሚገባ አስምረውበታል፡፡
እንደ ቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ፤ ፕሮጀክቱ ስለመጓተቱ በተደጋጋሚ ሲነሳ የሰነበተ ሲሆን፤ችግሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታል የሚል ምላሽ ይሰጣል፡ ፡ ነገር ግን የችግሩ ባለቤት ማን እንደሆነ ለይቶ ያለማቅረብ ክፍተት አለ፡፡ የችግሩን ባለቤት ለይቶ ችግሩን ለማስተካከል መሰራት አለበት፡፡ የችግሩ
ባለቤት ካልተለየ ግን የአፈጻጸም ችግሮች ይቀጥላሉ፡፡
በተለይም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተጠሪነታቸው ለገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሆን የተደረገው የፋይናንስ ችግሮችን ለመቅረፍ ቢሆንም የኦሞ ኩራዝ 5 የፋይናንስ ችግር ሳይቀረፍ መቆየቱ ትክክል አይደለም፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር መንግስት የጀመረውን ፕራይቬታይዜሽን ተጠቅሞ የኦሞ ኩራዝ አምስት የፋይናንስ ችግር ሳይፈታ መቆየቱ ተቀባይነት የለውም፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ደምሴ እንደሚሉት ገንዘብ ባለመከፈሉ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 የስኳር ፕሮጀክት ግንባታ ተቀዛቅዟል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ያነሳቸው ክፍተቶችም ተገቢነት ያላቸው ናቸው፡፡ ለችግሩ መንስኤ የሆነው ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል ፋብሪካውን ለሚገነባው ኩባንያ ክፍያ አለመፈጸሙ ነው፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን ለኮንትራክተሩ መክፈል ያለበት እዳ እንዲከፈል የሚጠበቅበትን አድርጓል፡፡ ኮንትራክተሩ የሰራውን ስራ ኮርፖሬሽኑ አረጋግጦ ክፍያው እንዲፈጸምለት ለባንክ ልኳል፡፡ ይሁን እንጂ ክፍያውን መፈጸም የነበረበት ባንክ ክፍያውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
ባንኩ ሌላ ቦታ ያልተከፈለ እዳ ስላለውና እዳው እስኪከፈል ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5ትን ለሚገነባው ኮንትራክተር ገንዘብ አልከፍልም የሚል አቋም በመያዙ ክፍያውን እንዳልፈጸመ የሚናገሩት አቶ አብርሃም ይህ ማለት ጉዳዩ ከስኳር ኮርፖሬሽን አቅም በላይ መሆኑን ነው ይላሉ፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ገንዘብ ሚኒስቴር ከባንኩ ጋር ውይይት እያደረገ ሲሆን፤ ባንኩ ሊከፈለው የሚገባው ገንዘብ እንዲከፈለውና ባንኩ ደግሞ ለኮንትራክተሩ መክፈል ያለበትን እንዲከፍል እየተሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ ገንዘብ ለማቅረብ ከተለያዩ ባንኮች ጋር ስለ እዳ አቅርቦት ውይይቶች እየተካሄደ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ አቶ ብሩክ ታዬ ናቸው፡፡ እሳቸው በዚህ መድረክ ላይ እንዳሉት የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ጥቅም ላይ ያልዋለ ራሱን የቻለ ብድር አለ፡፡
ይህ ብድር ፋብሪካውን ሊያስጨርስ የሚችል ቢሆንም ከብድር ድርድሩ ጋር መጠናቀቅ ያለባቸው ነገሮች ባለመጠናቀቃቸው አልተለቀቀም፡፡ ይሁን እንጂ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ድርድሩ በቅርቡ ሲያልቅ ባንኩ ብድሩን ይለቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በፕሮጀክቱ ላይም የተሻለ ስራ ያሰራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከኦሞ ቁጥር 5 በተጨማሪ ሌሎች የስኳር ፕሮጀክቶችም ቀሪ ስራዎቻቸውን ሊሰሩ የሚችሉበት፤ ያልተከፈሉ ብድሮችን ሊከፍሉ የሚችሉበት በቂ ገንዘብ ማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ያብራሩት አቶ
ብሩክ በስኳር ኮርፖሬሽን ስር በሚገኙ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚገኙ ችግሮች በገንዘብ ብቻ የሚፈቱ ባለመሆናቸው ከገንዘብ አቅርቦት ጎን ለጎን ሌሎች ስራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ብሩክ ማብራሪያ ከፕራይቬታይዜሽንና ከሪፎርም ጋር በተያያዘ ገንዘብ ሚኒስቴር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ መንግስት ባስቀመጠው አካሄድ መሰረት የፕራይቤታይዜሽንና የሪፎርም ስራው ስኳር ኮርፖሬሽንን ጨምሮ እየተሰራ ነው፡፡ በዚያው መሰረት በኦሞ የሚገኙ ስኳር ፕሮጀክቶችና ሌሎች ፋብሪካዎች ላይም የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡
ከሚሰሩ ስራዎች መካከል አንዱ ፋብሪካዎቹ ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ መለየት፤ ፋብሪካዎቹ ምን ያህል ተሰርተዋል፤ የስኳር ፖሊሲም እየተዘጋጀ ነው፤ የተለያዩ ፋብሪካዎች ቴክኒካል የሆኑ ነገሮች እየተሰራ ነው፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሀድጉ እንደተናገሩት፤ ህዝቡ ውጤት ይፈልጋል፡፡ ህዝቡ ለስኳር ያለው ፍላጎት በከተማም በገጠርም እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከፍተኛ ፍላጎት ባለበት ሀገር ውስጥ እነዚህ ስኳር ፕሮጀክቶች ቢጠናቀቁ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡
ውጭ ሀገር በመላክ ምንዛሬ ማስገኘት ባይቻል እንኳ በሀገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት በማሟላት ስኳር ከውጭ ለማስገባት እየወጣ ያለውን ወጪ ማዳን ያስፈልጋል፡፡ መድሃኒትን የመሳሰሉ እጅግ አስፈላጊ ነገሮችን ከውጭ ሀገራት ለማስገባት መዋል ያለበት ምንዛሬ ስኳር ለማስገባት ማዋል መቆም አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ለኮንትራክተሩ መክፈል ያለበት ገንዘብ ተከፍሎ የፕሮጀክቱ ግንባታ እንዲፋጠን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሀገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ ስኳር እንዴት ከውጭ ይገባል የሚል ቁጭት በውስጣችን ሊያድር ይገባል ያሉት ሰብሳቢዋ፤ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንጻር እጅግ የተጓተተ ነው፡፡ ህዝቡ ፈጣን ውጤት ነው የሚፈልገው፡፡ ኮርፖሬሽኑ የጀመራቸውን የሪፎርም ስራዎች በአፋጣኝ በማጠናቀቅ ውጤት ማሳየት አለበት፡፡ ከአሁን በኋላ በሪፎርም ስራዎች በሂደት ላይ ነው የሚለውን የማዘናጊያ ንግግሮች መቆም አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ህብተረተሰቡ የሚፈልገው ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም ውጤት በማስመዝገብ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ለምለም ማብራሪያ፤ አብዛኞቹ የስኳር ፋብሪካዎች መቼ ግንባታቸው ተጠናቀው መቼ መቼ ምርት ማምረት እንደሚጀምር አይታወቅም፡፡ ይጠናቀቃል ተብሎ መርሃ ግብር ይያዛል ነገር ግን ሲጠናቀቅ አይታይም፡፡
ለማጠናቀቅ ገደብ ተቀምጦ ሦስቴና ሁለቴ የተራዘሙ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ስህተት አንዴ ወይም ሁለቴ ሊከሰት ይችላል፡፡ ስህተት ግን እየተደጋገመ መቀጠል የለበትም፡፡ ፕሮጀክቶቹ ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት በድህነት ውስጥ ያለች ሀገርና ህዝብ እያጡ ያለውን ጥቅም ቆም ብሎ ካለማየት የመነጨ ይመስላል፡፡ ይህ አካሄድ ከአሁን በኋላ መቀጠል የሌለበት፤ በመሆኑ መስተካከል አለበት፡፡
በአጠቃላይ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 የስኳር ፕሮጀክት እንደ አጀማመሩና እንደታቀደው ቢሆን ዛሬ አገራችን ስኳርን ከውጭ ማስገባት ሳይሆን ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ የአቅርቦቱን ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በመቅረፍ ተጠቃሚ እያደርገን ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ፕሮጀክቱ ያለበትን የፋይናስ ችግር መቅረፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገሪቱን የኢኮኖሚ አቅም መደጎማ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17/2011
በመላኩ ኤሮሴ