አቶ ደጀኔ ማሞ (ረዳት ፕሮፌሰር)፤ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖ ሚክስ መምህር ናቸው። በጣሊያን አገር ሚላን ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት በአፍሪካ ፖሊሲ ላይ የዶክተሬት ዲግሪያቸውን እየሰሩ ነው። በመጀመሪያ ዲግሪ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግና ፋይናንስ እንዲሁም ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ተመርቀዋል።
ሁለተ ኛው ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ አስተዳደር ተምረዋል። በፖሊሲ፣ በግብር እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ 18 የሚሆኑ የጥናት ጽሑፎች በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል። በጅማ እና በአዳማ ዩኒቨርሲቲዎችም አስተምረዋል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቶ ደጀኔን በአገራችን በግብር እና የመንግሥት የፋይናንስ ተጠያቂነት ዙሪያ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርጓል። እንደሚከተለውም አቅርበ ነዋል።
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያ ያለውን የግብር ሥርዓት በከፋዩና በአስከፋዩ ያለውን ሁኔታ በምሁር መነፅር እንዴት ያዩታል?
አቶ ደጀኔ ማሞ፡– በሥራ ሂደትና በምርምር እንዳየሁት የግብር ሥርዓታችን በብዙ ችግር የተተበተበ ነው። አስከፋዩም ከፋዩም ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም። አንዳንዴ የመንግሥትን ግብር የመሰብሰብ አቅም ጥያቄ ውስጥ የሚከትት ሁኔታ ታያለህ።
ኢኮኖሚው ከነችግሮቹ እያደገ ቢሆንም ግብር ግን በዕድገቱ ልክ እየተሰበ ሰበ አይደለም። በየዓመቱ የሚሰበሰበው ግብር ከቀደመው ዓመት ብልጫ ቢኖረውም ከዕድገቱ አንፃር ዝቅተኛ ነው። በመካከለኛው ምሥራቅ አፍሪካ ያሉ
አገራት ከአገራዊ ገቢያቸው ግብራቸው 19 እና 20 በመቶ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን ከ13 ነጥብ 2 በመቶ ማለፍ አልቻለም። ባለፈው ዓመት ይህ መጠን ወደ 11 በመቶ ወርዷል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ በኢኮኖሚ ዕድገት ክስተት ከሚባሉት ሰባት አገራት አንዷ ብትሆንም ግብር በመሰብሰብ ግን ከአፍሪካ ጭራ ነች። በሥርዓቱ ውስጥም ውስብስብ ችግር ያለባት ናት።
አዲስ ዘመን፡– ዋና ዋና ችግሮችና መንስዔዎች ምንድን ናቸው?
አቶ ደጀኔ ማሞ፡– ቀደም ሲል ዋናዎቹ ችግሮች የፖሊሲና የአስተዳደር ነበሩ። የፖሊሲው ከ2003 ዓ.ም በኋላ ተቀርፏል። በገቢ ግብር ላይ የተንጠለጠው ግብር የዕለት ሽያጭንና ፍጆታን መሠረት አድርጎ እንዲከፈል እየተደረገ ነው። ይህ ትልቅ መሻሻል ነው።
መንግሥት ፖሊሲውን ተግባራዊ ማድረግ ቢቻልም፤ የንግድ ድርጅቶችና ኅብረተሰቡን በግብር ሥርዓት ውስጥ ማስገባት ከፍተኛ ችግር ሆኖበታል። የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር መረጃ እንደሚያሳየው፤ በኢኮኖ ሚው ውስጥ ካለው እንቅስቃሴ 36 በመቶ የሚሆነው ኢ-መደበኛ ነው። ይህንን ግብር ማስከፈል አይቻልም። ከኢ-መደበኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በላይም በመደበኛው እንቅስቃሴ ውስጥ ግብሩን የሚከፍለው 40 በመቶ ብቻ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ግብር ያለመክፈሉ ችግር ከግብር ከፋይ ምዝገባ ሥርዓቱ፤ ከአገልግሎት አሰጣጡና ከሌሎች በርካታ ችግሮች ጋር ይያያዛል። ግብር መክፈል በመንግሥትና በዜጎች መካከል ያለ ስምምነት ነው። መንግሥት የሰበሰበውን ገንዘብ ግብር ከፋዩ በትክክለኛ ተግባር ላይ እያዋለ መሆኑን ማመን አለበት። የግብር አከፋፈሉ ፍትሃዊ መሆን አለበት። ዜጎች የመንግሥትን መንግሥትነት ጥያቄ ውስጥ ካስገቡ ትክክለኛ ግብር አይከፍሉም። ይህ በመሆኑ በግብር አሰባሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ፤ መንግሥት ግብር እየከፈሉ ያሉ ዜጎችን እየተከታተለበት ያለው መንገድ ብዙ ችግሮች አሉበት። ለምሳሌ፤ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት መንግሥት ያለቀረጥ ከውጭ እንዲገባው የፈቀደውን በሙሉ ካስገቡ በኋላ መሬት ላይ ሲታይ ኢንቨስትመንቱ አይደለም ድንጋይ የለም።
በኢንቨስትመንት ላይ ማዋል ሳይሆን ይህንን ክፍተት በመጠቀም ዕቃ እያስገቡ የሚነግዱ ሰዎች ሥራ ቀረጥ ከፍሎ የሚያስገባውን ነጋዴ ከጨዋታ ውጪ ያደርገዋል። ገበያውንም ምስቅልቅሉን አውጥቶታል። መንግሥት በየዓመቱ ከቀረጥ ነፃ መብት ማግኘት የነበረበትን 26 ቢሊዮን ብር ያጣል። ይህ ኢንቨስትመንቱም ሳይለማ ገበያውን ምስቅልቅሉን በማውጣት የመንግሥትን ግብር የሚያስቀር ነው። አገሪቱንም ለትልቅ ችግር እየዳረገ ያለ ጉዳይ ነው።
ከኢኮኖሚው መዋቅር ጋር የተያያዘ ችግርም አለ። የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረቱ ግብርና ነው። ግብርናው ምርታማነቱን መሠረት አድርጎ ግብር አይከፈልም። ግብርም የሚከፈለው ሰዎች በያዙት መሬት ስፋት ነው። ከኢኮኖሚው ዕድገት 45 በመቶ የሚሆነው የግብርናው ዘርፍ ነው። በዘርፉ የሚሰበሰብው ግብር ምርታማነትን መሠረት አድርጎ ስላልሆነ ይኸም በራሱ ተጽዕኖ አለው።
አዲስ ዘመን፡– የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱ በዚሁ ከቀጠለ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
አቶ ደጀኔ፡– አገር እንዲቆም ግብር መሰብሰብ አለበት። አገር ለማቆምና መከላከያ፤ ደህንነት፤ ፖሊስ፤ ሌሎች በርካታ በመንግሥት የሚቀርቡ አገልግሎ ቶችን ለማቅረብ ገንዘብ ያስፈልጋል። መንግሥት በግብር ገንዘብ ካላገኘ አገልግሎቶቹን አያቀርብም። በመሆኑም፤ ግብር የአገር ልዕልናና ህልውና ማስጠ በቂያ መሣሪያ ነው። ይህ ካልሆነ አገር አይቆምም።
መንግሥት ሉዓላዊና ፍትሃዊ ከሆነ ዜጎች ግብር ይከፍላሉ። በበለጸጉት አገራት ግብርን ማጭበርብር እንደአገር ክህደት ነው የሚቆጠረው። ተጠያቂነቱም በዚያው ልክ ነው። ምክንያቱም የአገር ህልውና የሚቆመው በግብር ስለሆነ፤ ግብር መሰብሰብ የማይችል መንግሥትና ግብር የማይከፍሉ ዜጎች ያሉባት አገር ከወረራ እራሷን ማስጠበቅ አትችልም። ለምሳሌ፤ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መሣሪያ መግዣ በመጥፋቱ መንግሥት ሕዝቡን ለምኖ ጭምር ነው ጦርነቱን በአሸናፊነት ያጠና ቀቅነው፤ ይህ ጥሩ መማሪያ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ግብርን ሰብስቦ ለተገቢው ዓላማ የማያውል መንግሥት ግብር መሰብስብ ይችላል?
አቶ ደጀኔ፡– ግብርን ሰብስቦ ለተገቢ ተግባር የማያውል መንግሥት አስገድዶ ግብር ሊያስከፍል ይችላል። በኃይል ግብርን ማስከፈል የሚያመጣው ጣጣ ግን ብዙ ነው። ግብር ለመሰብስብ ከፍተኛ ወጪ ያስወጣዋል። በመንግሥትና በሕ ዝብ መካከል መተማመን ይጠፋል። በየትም ያለ የሰለጠነ ዜጋ ግብር አልከፍልም አይልም። በመንግሥት ላይ እምነት ቢያጣም ጭምር በምርጫ እለውጠዋለሁ
ይላል እንጂ ግብር የዜጎች የውዴታ ግዴታ ነው። በመንግሥትና በዜጎች መካከል መተማመን ካለ ግብርን በቀላሉ መሰብሰብ ይቻላል። መተማመን ከጠፋ ግን ግብር ለመሰብሰብ አስቸጋሪ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– በእኛ አገር ግብር ያለመክፈሉ መንስዔ በመንግሥትና በዜጎች መካከል ካለው አለመተማመን ጋር የተያያዘ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ደጀኔ፡- በተወሰነ ደረጃ አዎ። ይህ በሌላም ዓለም ያለ ነው። በኢትዮጵያ መሠረታዊው ችግር የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱ አላደገም። ግብር ከፋዩን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መቆጣጠርና አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን ይገባል። ግብር ከፋዩን የሚቆጣጠር ሥርዓት ከሌለ ግብር ከፋዩ አለመክፈሉን ሊመርጥ ይችላል።
የግብር ሥርዓቱ ዘምኖ፤ የምርመራ፤ የሂሳብ ቁጥጥርና ሌሎች ሥርዓቶች ጠንካራ ሲሆኑ «መንግሥት እኔን ተከታትሎ የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ ነው። ከተያዝሁ በራሴ ላይ ችግር አመጣለሁ» ብሎ ስለሚያስብ ግብር ይከፍላል።
አሁን ግን የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠንካራ ስላልሆነ ግብር ባልከፍል የመገኘት ዕድሌ ዝቅተኛ ነው ብሎ ያስባል። ገንዘብ እንደሚቆጥብም ያስባል። ግብር ቢያሸሽና ቢቀጣ የሚያጣውን ገንዘብ በማስላት ግብር መደበቅን እንደቁማር ይቆጥረዋል። በግብር ከፋዮች መካከል እኩል ተጠያቂነትና ፍትሃዊነት እስኪኖር ግብር መሰወሩን አይተውም።
አዲስ ዘመን፡– የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ባለፉት ስምንት ዓመታት 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መባከኑን፤ ይህም አለመመለሱንና ማንም ተጠያቂ አለመደረጉን አስታውቋል። ብክነቱ በግብር መሰብሰቡ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራል?
አቶ ደጀኔ፡- በፓርላሜንታዊ ሥርዓት በሕግ አውጪና አስፈፃሚው መካከል ያለውን ድንበር መለየት አስቸጋሪ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ አስፈፃሚው መሪ ናቸው። የፓርላማም አባል ናቸው።
ሁለቱ የተደባለቀ ስለሆነ በቀላሉ ድንበር ማበጀት አስቸጋሪ ነው። በዚህ የተነሳም በተፈጥሮው ሥራ አስፈፃሚው በፓርላማው ላይ ጫና ያደርጋል። ምክንያቱም አጀንዳዎችን የሚፈጽመው ሥራ አስፈፃሚው ነው። በአንድ አገር ውስጥ ምሉዕ ተጠያቂነት ያለው መንግሥት የሚባለው ሕግ አውጪ፤ አስፈፃሚና ተርጓሚ ኖሮ አንዱ በሌላው ላይ ጫና ሳያሳድር እርስ በእርስ መቆጣጠር ሲቻል ነው።
በኢትዮጵያ ሦስቱ አካላት በመዋቅር ደረጃ ቢኖሩም በተጠያቂነት ረገድ ጉድለት አለ። የመንግሥትን ወጪ ሥራ አስፈፃሚው በበጀት አዘጋጅቶ ያቀርባል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከአገሪቱ ፖሊሲና ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ከሆነ መርምሮ ያጸድቀዋል። አስፈፃሚው በጸደቀለት በጀት መሠረት ሥራዎችን ያከናውናል።
ሥራ አስፈፃሚውና ምክር ቤቱም በጀቱ ለታለመለት ዓለማ መዋሉን ክትትል ያደርጋል። በጀቱ በትክክል መሬት ላይ ወርዶ መፈጸሙን ገለልተኛ በሆነው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በኩል ኦዲት በማስደረግ ምክር ቤቱ የበጀትና ፋይናንስ አጠቃቀምን መቆጣጠሪያ ዋና መሣሪያ ይሆናል። በየዓመቱም የበጀት፤ የፋይናንስና የሥራ አፈፃፀም ኦዲት በማድረግ መስሪያ ቤቱ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀርባል።
ምክር ቤቱ የቀረበለትን የኦዲት ግኝት መሠረት አድርጎ ሥራ አስፈፃሚውን ተጠያቂ ማድረግ አለበት። የባከነውን ገንዘብም ማስመለስ ይገባዋል። ምክር ቤቱ ይህን ማድረግ አልቻለም። ደካማ ነው። ሥራውን እየሰራም አይደለም።
ምክር ቤቱ ሥራውን እየሰራ ቢሆን ኖሮ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር አይደለም ለስምንት ዓመት ለስምንት ቀን አይቆይም ነበር። ፓርላማውና በጀትን የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለመቆጣጠር እስከተቀመጠ ድረስ ይህንን መጠየቅ አለበት። መጠየቅ ያለባቸውን ኃላፊዎች ምክር ቤቱ መጠየቅ አለበት። በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጭምር እንዲከሰሱ መረጃ ማቅረብና ግፊት በማድረግ ማስጠየቅ ነበረበት።
ይሁንና አስፈፃሚው ጡንቻው የፈረጠመ በመሆኑ ምክር ቤቱ ተጠያቂ ማድረግ አልቻለም። አሁንም ተጠያቂ አያደርግም የሚል ስጋት አለኝ። ዋና አዲተር የኦዲት ጉድለት አቅርቦባቸው ሲጠየቁ የፓርላማ አባላትን እስከመሳደብ የደረሱበት ሁኔታ አለ። ይህ ጉዳይ እጅግ አስገራሚ ነው። አስፈፃሚው ምንም አይመጣብኝም በማለቱና ምክር ቤቱም ኃላፊነቱን ባለመወጣቱና ብሎም በሚመጥን ደረጃ ባለመደራጀቱ አገሪቱና ሕዝቦቿ እየተጎዱ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በአስፈፃሚውና በሕግ አውጪው መካከል የእርስ በርስ መጠያየቅ የለም ማለት ነው?
አቶ ደጀኔ፡- ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂነት የለም ማለት አይቻልም። ሥራ አስፈፃሚው የበላይነት ይዟል። በሥራ አስፈፃሚው የሚመራው ተቋማትና ኃላፊዎች ምንም እንደማይመጣባቸውና እንደማይሰማቸው በግልጽ ይታያል። ከዚያ ውጪ ግን የፓርላማው ድክመት ነው።
ሥርዓቱ ተዘርግቶ ሥርዓቱን ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም። ፓርላማው የኦዲት ግኝቱን መሠረት አድርጎ ኃላፊነቱን አልተወጣም። በጀት አጽድቆ የተመደበው በጀት በትክክል ጥቅም ላይ አልዋለም ብሎ የኦዲት መስሪያ ቤት ሪፖርት ሲያቀርብለት ይህን የፈጸሙ ተቋማትና ሰዎች እንዲከሰሱ ማድረግ ነበረበት።
አዲስ ዘመን፡– ከስምንት ዓመት በኋላም ቢሆን የፌዴራል መንግሥት አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ያበከኑ 35 ተቋማትን ለመከሰስ ማቀዱን አሳውቋል። ስለዚህ ምን ይላሉ?
አቶ ደጀኔ፡– ከመዘግየቱ ውጪ መልካም ነው። ውጤትም ያመጣል ብዬ አስባለሁ። ውጤቱ ግን በአንድ ጊዜ አይመጣም። ርምጃ መውሰድ ሲጀመር ተጠያቂነት እንዳለ አስፈፃሚውና ኃላፊዎች ስለሚያስቡ ገንዘቡን በትክክል ለታለመለት ዓላማ ያውላሉ። ይህ በጣም አስተማሪ ነው። በሕጉ መሠረት ተጠያቂ ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– በዚህ ዓይነት መልኩ ተጠያቂ ማድረግ ዘመቻ ይመስላል። የዘመቻ ፍትህ ውጤት አያመጣም፤ በሚጠየቁ ተቋማት ላይም ጫና ያመጣል የሚሉ አሉ። እርስዎ ለዚህ ምን ይላሉ?
አቶ ደጀኔ፡– እውነት ነው አንድ ሰሞን ተደርጎ የሚቆም ከሆነ ውጤት አያመጣም። እንደተባለው ነው የሚሆነው፤ አንድ ሰሞን አጥፊዎችን ከጠየቀ በኋላ የሚተው ከሆነ የዘመቻ ፍትህ ነው። ውጤት የለውም። ከዚህ በኋላ ግን ፓርላማ እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ በግልጽ ተለይቶ ሲቀርብለት የሚጠይቅ ከሆነ ውጤት ያመጣል።
በተጠያቂ ተቋማት ላይም ችግር አይፈጥርም። በፋይናንስ ሥራ ላይ የሚሰሩ ሰዎች ሕጉን መሠረት አድርገው እስከሰሩ ድረስ ችግር አይገጥማቸው። በተቋማቱ ላይም ችግር ይገጥማቸዋል ማለት አልችልም። ችግር ያለበትም ይሻሻላል።
ሥራዎችም በሕጉ መሠረት ይሰራሉ። ይህም ሁሉም ተጠያቂነት ባለው መልኩ ሥራውን እንዲሰራ ያበረታታል። ለአጭር ጊዜ ድንጋጤ ሊፈጥር ቢችልም ተጠያቂነቱ የሚቀጥል ከሆነ መልካም ውጤት ነው የሚኖረው፤
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ቃለ ምልልስ በአንባቢዎች ስም አመሰግናለሁ!
አቶ ደጀኔ፡– እኔም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16/2011
በአጎናፍር ገዛኸኝ