የመድሃኒትና የህክምና መገልገያዎችን በአብዛኛው ከውጭ በማስገባት የሀገር ውስጥ ፍላጎታቸውን የሚሸፍኑ ሀገራት ለዋጋ መጨመርና ለአቅርቦት እጥረት የተጋለጡ ናቸው። ይኸው ችግር በኢትዮጵያም የሚስተዋል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከውጭ ገብተው በሚሸጡ መድሃኒቶች ላይ የሚደረገው ትርፍ ከ0 ነጥብ 6 በመቶ እስከ 400 በመቶ ይደርሳል። ተደራሽነትንም በተመለከተ አብዛኛዎቹ መድሃኒት ቤቶች በተወሰኑ አካባቢዎች የተከማቹ በመሆናቸው ተገልጋዩ የህክምና አገልግሎቱን የማግኘት እድሉ ጠባብ ነው።
እነዚህን አገልግሎቶች በበቂ መጠን፣ በቅርበትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ገበያውን ማረጋጋት ደግሞ ከመንግስት ይጠበቃል። ለዚህም የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ያደረገው ‹‹ሞዴል›› የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት አገልግሎት ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ከመቅረፍ ባሻገር በሀገሪቱ እየተከሰተ ያለውን የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ብክነት ለመታደግ እንደሚረዳ ተገልጿል።
በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ያዕቆብ ሰማን እንደተናገሩት፤ ሚኒስቴሩ ባደረገው ጥናት ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር በመንግስት ተቋማት ስር ያሉ መድሃኒት ቤቶች አገልግሎት ሲሰጡ የነበረው ውስን በሆኑ ቦታዎችና በመደበኛው የስራ ሰአት ብቻ ነው።
የግል መድሃኒት ቤቶችም ቢሆኑ መደብሮቻቸውን የሚከፍቱት ለህዝብ ተደራሽ መሆንን ከግምት በማስገባት ሳይሆን ለእነሱ ገበያ በሚመቻቸው ቦታ ነበር። ይህም ሆኖ ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ እጥረትን ብቻ ከግምት በማስገባት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ። በዚህም የተነሳ በርካታ ዜጎች ለእንግልት፣ ለተጨማሪ ወጪ እንዲሁም መድሃኒት ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ስቃይ በመዳረግ ላይ ይገኛሉ።
በመሆኑም ጤና ሚኒስቴር ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶችን በመክፈት ችግሩን ለመቅረፍ ወደ ተግባር እየገባ ይገኛል። እነዚህ ሞዴል መድሃኒት ቤቶች ከመንግስት ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን፣ በአንፃሩ መድሃኒቶችንም ሆነ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ለተገልጋይ የሚያቀርቡት በተቀመጠው መመሪያ መሰረት ብቻ ነው። በመመሪያው መሰረትም እያንዳንዱ ፋርማሲ እንዲያገኝ የሚፈቀድለት ትልቁ ትርፍ ከ25 በመቶ መብለጥ አይችልም።
ይህም የተደረገው የቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት፣ የሰራተኛና ሌሎች ወጪዎችን ከግምት በማስገባት ነው። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር አሳሳቢ ችግር የሆኑት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ናቸው፤ በመሆኑም እነዚህ የመድሃኒት መደብሮች በስራቸው ስኳርና ደም ግፊት በመመርመር ለተገልጋዩ መድሃኒት የሚያቀርቡ ይሆናል።
በተደራሽነት በኩልም እስካሁን ለህዝብ ከፍተኛውን የህክምና አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የፌዴራልና በዩኒቨርሲቲዎች ስር ያሉ የጤና ተቋማት ናቸው። በመሆኑም ከተያዘው በጀት ዓመት ጀምሮ እነዚህ የጤና ተቋማት በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት መመስረት ግዴታ የተጣለባቸው መሆኑን ነው ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ያዕቆብ የተናገሩት።
‹‹በመንግስትና በግሉ ዘርፍ በመገፋፋት የመሄድ አካሄድ ነበር›› የሚሉት ዶክተር ያዕቆብ፣ በግሉ በኩል ጤና ጥበቃ አያግዘንም የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ይቀርብ እንደነበርና በመንግስትም በኩል ዋጋችሁ ከፍተኛ ነው የሚል ቅሬታ እንዳለ ያስታውሳሉ።
አብዛኛዎቹ የግል ተቋማት የተጋነነ ዋጋ ጨምረው የሚሸጡ ቢሆንም፤ በጣም ትንሽ ትርፍ ይዘው የሚሸጡም በመኖራቸው እነዚህን ተቋማት በዚህ ሥርዓት ለማስገባትም የሚደረግ እንቅስቃሴ እንዳለም ይጠቁማሉ። ክልሎችም የፌዴራሉን በመከተል የራሳቸውን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግና መመሪያ በማዘጋጀት ሞዴል መድሃኒት ቤቶችን እንደሚያቋቁሙም ያመለክታሉ።
‹‹በሚቀጥለው ሶስት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ በመንግስት ስር ሆነው እንደ የጋራ መኖሪያ ቤት ባሉና በርካታ ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ሃምሳ መድሃኒት ቤቶች ይከፈታሉ›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህም በአሁኑ ወቅት ከከተማ መስተዳድሩ ቤት በመቀበል ላይ እንደሆኑ ገልፀዋል።
መመሪያው ይፋ ከመሆኑ በፊት ለሙከራ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሁለት በግቢውና ልደታ የጋራ መኖሪያ ስር በከፈተው መድሃኒት ቤት እንዲሁም ሁለት በአማኑኤል ሆስፒታል፣ አንድ በአለርት ሆስፒታል አገልግሎቱን እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
‹‹ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት መመስረት የመድሃኒት ብክነትን ለመቀነስና በየትኛውም ጊዜ መድሃኒት ለማግኘት ያስችላል›› የሚሉት ደግሞ በሚኒስቴሩ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ረጋሳ ባይሳ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ብክነት በየትኛውም ዓለም የሚከሰት ቢሆንም በኢትዮጵያ ያለው ግን ከፍተኛ ነው።
ይህም ሊሆን የቻለው ተጠቃሚ ባለመኖሩ ሳይሆን በመድሃኒት ቤቶቹ መካከል መቀራረብና ተገቢ የመረጃ ልውውጥ ባለመኖሩ ነው። በዚህም የተነሳ በአንድ መድሃኒት ቤት የአገልግሎት ጊዜውን ሊጨርስ የተቃረበ መድሃኒት እያለ ይሄው መድሃኒት በሌላ ቦታ ባለመኖሩ እጥረት ይፈጠራል።
በአዲሱ መመሪያ ሁሉም ሞዴል መድሃኒት ቤቶች በሌሎቹ ሞዴል መድሃኒት ቤቶች ያሉትንና የሌሉችን መድሃኒቶች ያውቃሉ። በመሆኑም እነሱ ዘንድ የሌለ መድሃኒት ፈልጎ ለመጣ ተገልጋይ የትኛው መድሃኒት ቤት እንደሚያገኝ ዋጋውንም ጨምረው በመግለፅ ተገልጋይን ከእንግልት መታደግ ይችላሉ። በተጨማሪም በአንዱ የማይፈለገውን ወደ ሌላው ለመቀያየር የሚያስችል አሰራር ስላለ በደንቡ መሰረት በመቀባበል እነሱም ተገልጋዩንም መጥቀም እንደሚቻል አመልክተዋል።
በአገልግሎት መስጫ ሰዓት ረገድም እስከ ቅርብ ጊዜ ከነማ መድሃኒት ቤቶች 24 ሰዓት ይሰሩ ነበር፤ በመካከል ግን የገንዘብ ምዝበራ ተስፋፍቶ ስለነበር የሚቆጣጠር ህግ እስኪወጣ ተቋርጦ ቆይቷል። በመሆኑም በሆስፒታል ያላገኘውን መድሃኒት ከስራ ሰዓት ውጪ መግዛት የሚፈልግ ተገልጋይ ወደ ግል በመሄድ ለወጪ እየተዳረገ ይገኛል። ሁሉም ሞዴል መድኃኒት ቤቶች የበአል ቀናትን እንዲሁም ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ እስከ አራት ሰዓት ይሰራሉ። በተጨማሪም 24 ሰዓት የሚሰሩ በተራ የሚመደቡ የሚኖሩ ሲሆን፣ ተረኛውም በሬዲዮና በቴሌቭዥን በየወቅቱ የሚገለፅ ይሆናል።
‹‹መድሃኒት ቤቶች እንደ ህክምና ተቋማት የሚያገለግሉበት ሁኔታም አለ›› የሚሉት አቶ ረጋሳ፣ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በርካታ ህሙማን በቀጥታ መድሃኒት ቤት በመሄድ ህመማቸውን በመንገር መድሃኒት ይወስዳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከሆስፒታል የታዘዙ መድሃኒቶችንም ገዝተው በተገቢው መንገድ እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው በቂ መረጃ ባለመያዝና በግምት በመገልገል ለከፍተኛ ጉዳት የሚዳረጉም በርካቶች ናቸው። እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ የሚያስችል የባለሙያ አደረጃጀት በሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች ተዘጋጅቷል።
በእያንዳንዱ መድሃኒት ቤት የግድ ሶስት ባለሙያ የሚመደብ ሲሆን፣ ሁለቱ የመጣውን ማዘዣ በሚመለከት መድሃኒቱን የሚሰጡ ሲሆኑ፣ ቀሪው አንዱ ተገልጋዩ የገዛውን መድሃኒት በመመልከት እንዴት መጠቀም እንዳለበት የሚያስረዳ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመነሻ ካፒታል፣ የሀብት ምንጭና ልዩ ልዩ ድጋፍን በተመለከተም የመንግስት የጤና ተቋማት ሞዴል መድሃኒት ቤቶችን ለማቋቋም ከሆስፒታሉ የውስጥ ገቢ ከሚገኝ ከወለድ ነፃ ብድር፣ ከመንግስት ከሚገኝ መደበኛ የበጀት ድጋፍ ወይም እንደአስፈላጊነቱ ከሌሎች ምንጮች ከሚገኝ ገቢ የሚያቋቁሙበት ሁኔታ ሲኖር፣ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩና ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት አገልግሎት መስጠት የሚፈልጉም መድሃኒቶቹ በመንግስት በኩል የሚቀርቡላቸው ይሆናል። እንዲሁም በጤና ሚኒስቴር ሚዲያ ራሳቸውን የማስተዋወቅና የተለያዩ ስልጠናዎችን የማግኘት እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን የሚያገኙ እንደሆነም አስረድተዋል።
‹‹የተዘጋጀው መመሪያ በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ሞዴል የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት በሚያቋቋሙ የፌዴራል ሆስፒታሎች እንዲሁም በዚህ መመሪያ መሰረት ለመተዳደር ፈቃደኛ በሆኑ የከነማ መድሃኒት ቤቶች፣ የቀይ መስቀልና የግል መድሃኒት ቤቶች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል›› የሚሉት አቶ ረጋሳ፣ ለሞዴል መድሃኒት ቤቶች የተቀመጡትን አስገዳጅ ህጎችም እንዳሉት ገልፀዋል።
ይኸውም ማንኛውም መድሃኒት ቤት ‹‹ሞዴል›› የሚል ስያሜ ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወይም ከጤና ቢሮዎች አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ ማግኘት አለበት። ማንኛውም ሞዴል መድሃኒት ቤት የሚከፈተው ከሌላ ሞዴል መድሃኒት ቤት ቢያንስ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቆ መሆን ይኖርበታል። ተመሳሳይ የግድግዳ ቀለምና ማስታወቂያን ይጠቀማል። ለህብረተሰቡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ መድሃኒቶች በሆስፒታሉ ማኔጅመንት ተወስኖ በህጋዊ ደብዳቤ ዋጋቸው ሲገለፅ ለማህበረሰብ በመግዣ ዋጋ እንዲሸጡ ሊደረግ ይችላል።
ዘወትር ከሰኞ እስከ አርብ በመንግስት የስራ ሰዓት አገልግሎት ይሰጣል፤ በተጨማሪም ከመንግስት የስራ ሰዓት ውጭ እንዲሁም ዘወትር ቅዳሜ፣ እሁድ እና በህዝባዊ በዓላት ቀናት ቢያንስ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ አገልግሎት መስጠት አለበት።
ማንኛውም ሞዴል መድሃኒት ቤት የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማርካትና የመድሃኒት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ተቋሙ ወይም መንግስት በሚያወጣው መሰረት በፈረቃ የመስራት ግዴታ አለበት። ማንኛውም ሞዴል መድሃኒት ቤት መድኃኒቶችን ለተጠቃሚው መሸጥ ያለበት ከ25 በመቶ ባልበለጠ የትርፍ ምጣኔ ሲሆን፣ የመድሃኒቶቹን የመሸጫ ዋጋ በዝርዝርና በግልጽ በሚታይ መልኩ ለተጠቃሚው መለጠፍ እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/201
ራስወርቅ ሙሉጌታ