የአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ዘላቂ የአካባቢና የደን አያያዝ፣ልማትና አጠቃቀምን በማረጋገጥ በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን የገነባችና መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር እንድትሆን ራዕይ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለ ተቋም ነው፡፡
ሀገሪቱ የምትከተለውን ግብርና መር የኢንዱስትሪ የልማት ፖሊሲ መነሻ በማድረግ በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉና በቀጣይም የሚገነቡ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ከመኖራቸው አኳያ ዘለቂታዊ የኢንዱስትሪ ልማትና አካባቢዎችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡
በደንና የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ባሉ ህጎች አፈፃፀምና ህጎቹን ለማሻሻል እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ዙሪያ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ልማት ከአካባቢያዊና ማህበራዊ ዘላቂነት ጋር እንዴት ተጣጥመው መሄድ እንደሚችሉ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡ ፡
አዲስ ዘመን፡– በአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ያሉ ህጎችና አዋጆች አፈፃፀማቸው ምን ይመስላል?
ወይዘሮ ፍሬነሽ፡– ከህግ አኳያ መስሪያ ቤቱ በደንም ሆነ በአካባቢ ዙሪያ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን ይሰራል፡፡ እነዚህን የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች ለማከናወንም ህጎች፣አዋጆችና ደንቦች ተዘጋጅተዋል፡፡ በተጨማሪም የአካባቢና የደን ልማት ጥበቃ ፖሊሲዎችና አዋጆች ወጥተው ተግባራዊ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ከአካባቢ አኳያ የተለያዩ አዋጆችና ደንቦች ተዘጋጅተዋል፡ ፡ የአካባቢ ብክለት ክትትልና ቁጥጥር አዋጅን ተከትሎም አዋጁን ለማስፈፀም የሚያግዙ ደንቦች ወጥተዋል፡፡
ሀገሪቱ የምትከተለው የልማት ፖሊሲ ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ከመሆኑ አኳያ ኢንዱስትሪዎች በብዛት እንዲስፋፉ ይፈለጋል፡፡ በዚህ ረገድም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይም ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ሰፊ ስራዎችን መስራት ይጠይቃል፡፡ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ ታዲያ የአካባቢ ጉዳይ ወሳኝ በመሆኑ አካባቢን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ህጎችንና
አዋጆችን ማውጣት የግድ ይላል፡፡ በእርግጥ ህጎቹ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ አፈፃፀማቸው ሲታይ ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን እየተሻሻሉና እየጠበቁ መጥተዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ያሉ ህጎችንና ፖሊሲዎችን ለማሻሻል ምን አይነት ስራዎች እየተሰሩ ነው?
ወይዘሮ ፍሬነሽ፡– በመጀመሪያ ደረጃ፣ ህጎች አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታና በቀጣይ የሚከናወኑ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይወጣሉ፡፡ ህጎቹ ወጥተው ወደ ተግባር በሚሸጋገሩበት ሂደት ውስጥ አፈፃፀማቸው ይታያል፡፡ ቀደም ሲል በ1986 ዓ.ም የወጣው የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር፣ የተፈጥሮ ሀብት መመናመንን ተከትሎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችንና ሌሎች ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ አልነበረም፡፡ ይህንንም ተከትሎ እነዚህን ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ፖሊሲዎቹን የማሻሻል ስራዎች ተሰርተው በአሁኑ ወቅት ወደ መጠናቀቅ ሂደት ላይ ተቃርበዋል፡፡
በተመሳሳይም የአካባቢና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ አዋጅ በ1995 ዓ.ም የወጣና በተግባር ሂደት ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም፤ በሂደት አንዳንድ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው አዋጁ እየተሻሻለ ይገኛል፡፡ የአዋጁ ረቂቅም ተጠናቆ በቀጣይ ከፀደቀ በኋላ ተግባር ላይ የሚውል ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል በ1999 ዓ.ም የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ የወጣ ሲሆን፣ አዋጁ በአሁኑ ወቅት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ፣ የህዝብ ቁጥሩንና የከተሞችን መስፋፋት ተከትሎ የሚመነጨውን የቆሻሻ አይነትና መጠን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተሻሽሎ በረቂቅ ደረጃ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል አዳዲስ ነባራዊ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ሌሎች ህጎችና አዋጆች ይወጣሉ፡፡ በዚህም መሰረት የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ወጥቷል፡፡ አዋጁ ብክለትን የአየር፣ አፈር፣ ውሃና የድምፅ በሚልም ያስቀምጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት የድምፅ ብክለት በከተሞች አካባቢ እየታየ ያለ ችግር ከመሆኑ አኳያ የድምፅ ብክለት መከላከልና መቆጣጠር ደንብ ከዚህ አዋጅ መንጭቶ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡ ፡ ኮሚሽኑ በተግባር ሂደት ውስጥ በሚያገኛቸው ግኝቶችና በሚፈጠሩ የተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎች
አዳዳስ ህጎችንና አዋጆችን የማውጣትና የማሻሻል ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡– ኢንዱስትሪዎች የሚለቋቸው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት አሉታዊ ተፅዕኖ እንዴት ሊቀረፍ ይችላል?
ወይዘሮ ፍሬነሽ፡- የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በአሁን ወቅትም የፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡ ፡ ሀገሪቱ ካስቀመጠችው ግብ አኳያም በቀጣይ በርካታ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ይገነባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይሁን እንጂ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ በመጡ ቁጥር በአካባቢ ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉት አሉታዊ ተፅዕኖም አብሮ ሊታይ ይገባል፡፡ የአካባቢና ማህበራዊ ዘላቂነትንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ማስኬድም ያስፈልጋል፡ ፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ በሀገሪቱ በ1995 ዓ.ም የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ተቋቁሞና የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ወጥቶ ወደተግባር ተሸጋግሯል፡፡
ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ ብዙም አስገዳጅ ሁኔታዎች ስላልነበሩ ህጎችንና አዋጆችን የማውጣቱ ተግባር እምብዛም አልተከናወነም፡፡ ይሁንና በሂደት የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትን ተክትሎ የአካባቢ ጥበቃ ስራም ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በአካባቢ ዙሪያ ያሉ አዋጆችና ህጎች ወጥተው ወደ ስራ ተገብቷል፡ ፡ የልማት ዘላቂነት በዋናነት የሚረጋገጠው የአካባቢና ማህበራዊ ዘለቄታን ማጣጣም ሲቻል በመሆኑ ህጎችንና አዋጆችን በማውጣት ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከዚህ በፊት በሀገሪቱ የነበሩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ሰዎች በማይኖሩባቸው አካ ባቢዎች ላይ የነበሩና በቁጥርም አነስተኛ በመሆ ናቸው በአካባቢ ላይ ሲያደርሱ የነበረው ተፅዕኖ አነስተኛ ነበር፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት የህዝብ ቁጥር መጨመርና የከተሞች መስፋፋትን ተክትሎ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ወደ መሃል እየመጡና ከሰዎች ጋር ያላቸው ንክኪም እየጨመረ መጥቷል፡ ፡
ይህንንም ተከትሎ ፋብሪካዎቹና ኢንዱስትሪዎቹ የሚለቋቸው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች በአካባቢና በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እያስከተሉ ይገኛሉ፡ ፡ ለዚህም ህጎችና አዋጆች ወጥተዋል፡፡ ሆኖም ህጎቹና አዋጆቹ በአግባቡ ተፈፃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ የወጣበት ዋነኛ ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ልማቶች በአካባቢና በማህበረሰቡ ላይ ጎጂ ተፅዕኖ ማድረስ እንደሌለባቸው በመታመኑና ይህንንም መቆጣጠር እንደሚገባ ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት በመታሰቡ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የልማት ስራ ሲታቀድ በመጀመሪያ በአካባቢውና በማህበረሰቡ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጥናት ይካሄዳል፡፡ በጥናቱ መሰረትም ግምገማ ይካሄዳል፡፡ በመቀጠልም ጥቅምና ጉዳቱ ታይቶ ግንባታው እንዲጀመር ይደረጋል፡፡ ልማቱን፣ አካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ዘላቂ ለማድረግ የአካባቢና የማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ አዋጅ ወጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡– በከተሞች የሚገኙ የወንዝ ዳርቻዎችን ለማስዋብና ከብክለት ለመከላከል ምን አይነት ጥረቶች እየተደረጉ ነው?
ወይዘሮ ፍሬነሽ፡- ኮሚሽኑ በህግ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት ውስጥ አንዱ የአካባቢ ብክለት ችግር እንዳይፈጠርና ማንኛውም የልማት ስራዎች የአካባቢ ጥበቃን ከግምት ውስጥ ያስገቡ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በወንዞች አካባቢ የሚገኙ የተለያዩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ፍሳሾቻቸውን አጣርተው በስታንዳርዱ መሰረት እንዲለቁ ከማድረግ አኳያ ኮሚሽኑ የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን ይሰራል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የደረቅ ቆሻሻዎችን የሚያመነጩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎችም ቆሻሻዎችን በአግባቡ እንዲያስወግዱና መጠቀም እንዲችሉ ተመሳሳይ የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች በኮሚሽኑ ይሰራሉ፡ ፡ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን አስገብተው የቆሻሻ አያያዙን ዘመናዊ ማድረግ እንዲችሉም ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡– በአዲስ አበባ የወንዝና ወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ዙሪያ የኮሚሽኑ ሚና ምንድን ነው? ፕሮጀክቱ ውጤታማ ይሆናል ብለውስ ያምናሉ?
ወይዘሮ ፍሬነሽ፡– የአዲስ አበባ የወንዝና ወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት በ29 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ይከናወናል፡፡ ፕሮጀክቱ በተለይ ለአዲስ አበባ ከተማ ፅዳትና ውበት ወሳኝ ነው ተብሎም ይታመናል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በርካታ ፋብሪካዎ ችና ልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ፡፡ በተለይም በከተማዋ ቀደም ብለው የተሰሩ ፋብሪካዎች ወደ ወንዝ ተጠግተው ስራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ፋብሪካዎቹ በሚለቋቸው ፍሳሽ ቆሻሻዎችና ከየቤቱ ተጠርገው ወደ ወንዝ በሚጣሉ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ምክንያት የአዲስ አበባ የወንዝ ተፋሰሶች ተበክለዋል። ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝና ወንዝ ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት በብዙ መልኩ ወሳኝ ነው ማለት ይቻላል።
ኮሚሽኑ የአካባቢ ጥበቃ የሚመለከተው ጉዳይ በመሆኑ ለወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቱ አፈፃፀም ትልቅ ድጋፍ ያደርጋል። ከነዚህ ድጋፎች ውስጥ አንዱ በወንዝ ዳርቻ አካባቢ የሚገኙ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትዎች ፍሳሻቸውን በአግባቡ አጣርተውና የሚፈለገውን ደረጃ አሟልተው እንዲለቁ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፋብሪካዎቹና ኢንዱስትሪዎቹ ደረቅ ቆሻሻቸውን በአግባቡ እንዲይዙና እንዲያስወግዱ መከታተ ልና መቆጣጠር ነው።
በተጨማሪም የከተማ ደን እንዲስፋፋና የአረንጓዴ ልማት እንዲረጋገጥ ኮሚሽኑ ይሰራል። የሚከናወኑ ስራዎች በጥ ናት የተደገፉና ምሁራንም የተሳተፉበት በመ ሆኑ ፕሮጀክቱ ውጤታማ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባ ቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰ ግናለን።
ወይዘሮ ፍሬነሽ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011
በአስናቀ ፀጋዬ