ሞሐመድ ቦአዚዝ የተባለ ወጣት በአደባባይ ራሱን ማቃጠሉን ተከትሎ እኤአ በ2011 በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ቱኒዚያ የተለኮሰው ሕዝባዊ ዓመፅ ከ23 ዓመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ ፕሬዚዳንት ቤን አሊን አገር ጥለው እንዲሸሹ በማስገደድ ብቻ አላበቃም፡፡
ቤን አሊ ለዓመታት የተቀመጡበትን የሞቀ ወንበር የለበለበው ሰደድ እሳት ውሎ ሳያድር ወደ ሌሎች አምባገነኖችም ተሸጋግሯል። ሊቢያና ግብፅ የህዝባዊ አመፅ እሳቱ ቀዳሚ ቀማሾች ይሁኑ እንጂ የተለያዩ መንግስታት ዙፋንም ከመቃጠል አላመለጠም።
እሳቱ የተለኮሰባት ቱኒዚያም እኤአ 2014 ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዚዳንቷን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በፈቃዷ መርጣለች። በምርጫውም ቤጂ ካይድ ኤሴቢ ተቀናቃኛችው ሞንሴፍ ማርዙኪን በመርታት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
በቤን አሊ ዘመነ መንግስት የፓርላማ አፈ ጉባኤ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኤሴቢ፤ ምንም እንኳን የአገሪቱ ህገ መንግስት በመከላከያና በውጭ ግንኙነቱ ረገድ ስልጣናቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲተገብሩ ፈቃድ ባይሰጣቸውም ሰውየው ግን ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት አራት ዓመታት ከሰሜን አፍሪካ አገር ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥ ጉልህ ተፅዕኖን ማሳረፍ ችለዋል።
ከቀውሱ በኋላ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር በማድረጓ የተደነቀችውና በእነዚህ ዓመታት በጥምር ፓርቲ የምትመራው ሰሜን አፍሪካዊቷ አገርም፤ ምንም እንኳን ከቤን አሊ ዘመን የተሻለ ለውጥ መመልከት ብትችልም፤ እንደወትሮው ሁሉ የኢኮኖሚ ቀውሷን በተለይም የዋጋ ግሽበትና ስራ አጥነት ማቃለል አልሆነላትም።
ይህ ችግር መቃለል አለማሳየቱና አገሪቱ በከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መዘፈቋም በህዝቡ ዘንድ ቅሬታና ተቃውሞ እያስተናገደ ይገኛል። በያዝነው ዓመት በወርሃ ጥር የአገሬው መንግስት የ670 ሺ ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄን ለማስተናገድ ፈቃደኛ ሆኖ ባለመታየቱ ከባድ ተቃውሞ ማስተናገዱም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሆኖ ይጠቀሳል።
ይህ በሆነበት ቱኒዚያ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ማብቃያ ላይ የፓርላማና የፕሬዚዳንት ምርጫ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ይዛለች። ምርጫውን ለማካሄድ ወራት እየቀሩት ገና ከወዲሁ አወዛጋቢ መሆን ጀምሯል። የ92 ዓመቱ የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቤጂ ካይድ ኤሴቢም ከቀናት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ በስልጣን የመወዳዳር ፍላጎት እንደሌላቸው ማሳወቃቸው የውዝግቡ ዋነኛ መነሻ መሆኑን መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።
የአገሪቱ ህገ መንግስት ፕሬዚዳንቱ ለሁለተኛ ጊዜ በምርጫው መወዳደር እንደሚችሉ ዋስትና ቢሰጣቸውም፤ እርሳቸው ግን ፍላጎቱ እንደሌላቸው እወቁልኝ ብለዋል። ይህን ያሉትም ለይስሙላ ሳይሆን የእውነት ስለመሆኑ አስረግጠዋል።
«በአሁኑ ወቅት ቱኒዚያ ለውጥ ያስፈልጋታል፤ ለወጣቶች በር መክፈት ያለባት ትክክለኛው ጊዜም መጥቷል›› ሲሉም የተደመጡት ፕሬዚዳንቱ፤ ከመጪው ምርጫ አስቀድሞም በፓርቲያቸው አባላትና በአገሪቱ ፖለቲካ ተሳታፊዎች መካከል የሚስተዋለው መከፋፈል ውስጣዊ ሽኩቻ ሊወገድ እንደሚገባው አፅዕኖት ሰጥተውታል።
ፕሬዚዳንቱ ይህን ይበሉ እንጂ ቀደም ሲል ከአገር ውስጥም ሆነ ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋር በሚያደርጉት ቃለ ምልልስ በቀጣዩ ምርጫ ስለመወዳደራቸው እንቅጩን ለመናገር ሲያመነቱ መታየታቸው በአገሬው ህዝብ ዘንድ ሁለት አይነት ስሜትን ፈጥሯል።
በዚህ ረገድ ሰፊ ትንታኔውን የሰራው የአልሞኒተሩ አሜን አል ሂላሊ፤ ፕሬዚዳንቱ በዳግም ምርጫ እንደማይወዳደሩ ማሳወቃቸው በቱኒዚያውያን መካከል ጉራማይሌ እሳቤን ስለመፍጠሩ አትቷል። እንደ ዘገባው ከሆነም፤ አንዳንዶች የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ የሚደነቅና ታሪኳዊ ሲሉት ሌሎች በአንፃሩ፤ የለም ሰውየው ተቀናቃኞቻቸውን ለማለዘብ የተጠቀሙበት ፖለቲካዊ ቀመር ነው የሚል አቋም ይዘዋል።
የቀድሞ አልኢርዳ ፓርቲ አባል ጣሪክ አል ካላዊን ጨምሮ አንዳንድ ፖለቲከኞች፤ ፕሬዚዳንቱ በዳግም ምርጫው የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው ከወዲሁ ማሳወቃቸው ድብቅ አላማን ያነገበ ስለመሆኑ ተረድተውታል።
ፕሬዚዳንቱ በንግግር ደረጃ ይህን ይበሉ እንጂ «ነገ በምርጫው ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ካርድ በሌላኛው እጃቸው አንጠልጥለው ይታያሉ›› ሲሉም ተደምጠዋል። የፕሬዚዳንቱ ፓርቲና አንዳንድ የፓርላማ አባላት በአንፃሩ፤ ውሳኔው በተለይ ለወጣቶች የስልጣን በሩን የሚከፍት ነው ብለውታል። ሲሉ በእጀጉ አድንቀውታል።
ቱኒዚያ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ የፓርላማና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮን ይዛለች። የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንትም በምርጫ እንደማይወዳደሩ በአደባባይ ከገለፁ ቀናትን ቢያስቆጥሩም፤ ፓርቲያቸው ግን እስካሁን በምትካቸው የሚያስቀምጠውን ሰው በይፋ አላሳወቀም።
ይህ እንደመሆኑም የምርጫው ቀነ ቀጠሮ ወራት በቀሩት በዚህ ወቅት ገና ከወዲሁ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሱፍ ቻህድ እና በፕሬዚዳንቱ ልጅ ሃፌድ ካይድ ኤሴቢ መካከል በስልጣን ወንበሩ ላይ የመቀመጥ ትንቅንቅ መታየት መጀመሩ ተመላክቷል።
የአገሬው መሪ «የኒዳ ፓርቲ» ከቀናት በፊት
ሁለት መሪዎችን መርጧል። አንደኛው የምርጫ ካውንስል ሶፊያ ቱቤል የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የበላይ አድርጎ ሲመርጥ ሌላኛው ደግሞ የፕሬዚዳንቱን ልጅ ሃፌድ ካይድ ኤሴቢ፤ ፈቅዷል።
በዚህ ልዩነት ላይ ሰፊ ትንታኔውን ያሰፈረው ሮይተርስ፤ ታሬክ አማራ ዘገባ ታዲያ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ሊካሄድ ለታቀደው የአገሪቱ ፓርላማና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወራት ሲቀሩት ከወዲሁ የተከሰተው የኮንግረሱ ምርጫ የየቅል ፍላጎትና ልዩነትም እኤአ ከ2015 ወዲህ ፓርቲው ለሁለት ከፍሎታል ሲል አስነብቧል።
የፕሬዚዳንቱ ልጅ የፓርቲው የበላይ ለመሆን ብርቱ ምኞት እንዳለውና ለፍላጎቱ እውነትም በርትቶ እየሰራ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፤ ከእነዚህም አንዱ በርካታ የፓርቲውን አመራሮች ስልጣን እንዲለቁ ማድረጉ ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትር የሱፍ ቻሄድና አንዳንድ የፓርቲው አመራሮችም ‹‹የፕሬዚዳንቱ ልጅ የመረጠው ኮንግረስ አግባብነትን የተከተለ አይደለም›› ብለውታል። የፕሬዚዳንቱ ልጅ ሃፌድ ካይድ ኤሴቢ በበኩሉ፤ በአንፃሩ የሚቀርብበትን ወቀሳ እንደማይቀበልና ይልቅስ አንዳንድ አባላትም በሚያሳዩት ፀባይም በእጅጉ እየተገረመ ስለመሆኑ ሲናገር ተደምጧል።
ከቀናት በፊት በሁለቱ ግለሰቦች መካከል ማን የስልጣን እድል አለው የሚለውን በሚመለከት በተሰራ የዳሰሳ ጥናት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሻለ ድምፅ ማግኘታቸው ቢገለፅም፤ አንዳንዶች ግን በግለሰቦቹ መካከል ከምርጫውም መካሄድ አስቀድሞ የሚስተዋሉ ሽኩቻዎች ስለ መጪው እንዲጨነቁ አስገድዷቸዋል።
ሻረግ ጌርዌልን ለመሳሰሉ የብሩክሊን የመካከለኛው ምስራቅ ፖሊሲ ተመራማሪዎች በአንፃሩ፤ ፕሬዚዳንቱ ከፖለቲካው በጡረታ ሲገለሉ የልጃቸውም ወቅታዊ የፖለቲካ ሹመት አብሮ መቋጫውን የሚያገኝ እንደመሆኑ አሳሳቢ ሊሆን አይገባም» ሲሉ ለ ዘናሽናል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ግራም ነፈሰ ቀኝ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ማብቂያ ላይ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የፓርላማና የፕሬዚዳንት ምርጫ እስላማዊው ኢንሃዳ በታህያ ቶንስ በ «ኒዳ ፓርቲ» መካከል የጦፈ ፉክክር እንደሚያሳይም ታምኖበታል።
አሁን ላይ ሶስቱም ፓርቲዎች በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው በማን እንደሚወከሉ ትንፍሽ ባይሉም በፓርቲዎቹ አመራሮችና ጋሻ ጃግሬ ፖለቲከኞቻቸው መካከል ከወዲሁ በወንበሩ ለመቀመጥ የሚካሄዱ ግብግቦች ግን ነገን ተናፋቂ አድርገውታል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2011
በታምራት ተስፋዬ