መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ ከዓለም ህዝብ 103 ሚሊየን የሚሆኑት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለስደት ተዳርገዋል:: ታዲያ ከእነዚህ ስደተኞች መካከል 72 ከመቶ የሚሆኑት የሶሪያ፣ ቬንዙዌላ፣ ዩክሬን፣ አፍጋኒስታን እና ደቡብ ሱዳን ዜጎች ናቸው:: ስደትን አስከፊ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል ማሳያ የሚሆነው ደግሞ እአአ በ2021 ለስደት ከተዳረጉ ሰዎች መካከል 41 ከመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችና ህጻናት መሆናቸውን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ ያሳያል::
በተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች የተነሳ ለስደት የሚዳረጉት እነዚህን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም የተለያዩ ተቋማት በሚያዘጋጁት የስደተኛ ጣቢያዎች እገዛ ይደረግላቸዋል:: ከመሰረታዊ ድጋፍ ባለፈ ስደተኞች ካሳለፏቸው ከባድ ሁኔታዎች እንዲያገግሙና ወደ መልካም ማህበረሰባዊ ግንኙነት እንዲመለሱ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ:: ከእነዚህ መካከል አንዱ ስፖርት ሲሆን፤ አእምሯዊና አካላዊ ጤንነታቸውን ለመጠበቅም መሰረታዊ መሳሪያ ነው:: ስፖርት ማህበረሰብን በማንቃት፣ ንቅናቄን በመፍጠር፣ ጎጂ ልማዶችን በመቅረፍ፣ መልካም እሳቤን በማስረጽ እንዲሁም የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማዳበር ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ፤ እንደ ተባበሩት መንግስታት ያሉ ተቋማት በስፋት ይንቀሳቀሱበታል::
አሁን የ24 ዓመት ወጣት የሆነው አራም ማህሙድ በሶሪያ ደማስቆ ነበር ተወልዶ ያደገው:: ነገር ግን በአገሩ በተነሳው ጦርነት ምክንያት ከዓመታት በፊት ወደ ኔዘርላንድ ሊሰደድ የግድ ሆነ:: በአገሩ ሳለ የባድሜንተን ስፖርትን የሚያዘወትረው ይህ ወጣት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ መድረሻውን ባደረገበት የስደተኞች ካምፕ ዳግም የሚወደውን ስፖርት መከወን ቻለ:: በስፖርቱ ምክንያትም ያሳለፈውን መከራ ከመርሳት አልፎ አዳዲስ ጓደኞችን ማፍራትና ሌሎች ቋንቋዎችንም ለማወቅ ችሏል:: በዚህም ‹‹ስፖርት እጅግ ረድቶኛል›› ሲል ይናገራል::
በእርግጥ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ብቻውን ዓላማቸውን ከግቡ ማድረስ አይችልም፤ በመሆኑም ተቋማቱ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት ጋር በጥምረት ይሰራሉ:: ከእነዚህ መካከል አንዱ የሰው ልጆችን በጎ እንቅስቃሴ የሚዳስሰውና ሁሌም ከተገፉት ጎን በመቆም የሚታወቀው ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው:: ኮሚቴው ለረጅም ዓመታት ከእነዚህ ተቋማት ጋር በተለያየ መልክ ሲሰራ ከቆየ በኋላም እአአ ከ2016 አንስቶ የስደተኞች ስፖርትን በሚመለከት መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ችሏል:: ይኸውም የስደተኞች ስፖርት ቡድንን በማቋቋምና ኮሚቴውን እንዲወክሉ በማድረግ በብራዚሉ የሪዮ ዴጄኔሮ ኦሊምፒክ እና ፓራሊምፒክ እንደማንኛውም ቡድን በማሳተፍ ነው:: በመክፈቻው ወቅትም ስፖርተኞቹ በኮሚቴው ባንዲራ እና መዝሙር ታጅበው ከአዘጋጅ አገር ቀጥሎ ነበር ወደ ትርኢት ማሳያው ስታዲየም ያቀኑት:: እአአ በ2020ው የቶኪዮ ኦሊምፒክም በተመሳሳይ ቡድኑ ለሁለተኛ ጊዜ ተካፋይ ሆኖ ነበር:: ይህም በስፖርት ተሰጥኦና ብቃት ላላቸው ስደተኞች ተስፋ ሊሆናቸው ችሏል::
በሪዮ ኦሊምፒክ አስር ስፖርተኞች በአትሌቲክስ፣ ውሃ ዋና እና ጁዶ ሲሳተፉ፤ በቶኪዮ ደግሞ 29 ተወዳዳሪዎች በአትሌቲክስ፣ ውሃ ዋና፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ ባድሜንተን፣ ቀዘፋ፣ ጁዶ፣ ካራቴ፣ ቴኳንዶ፣ ክብደት ማንሳት፣ ትግል እና በኢላማ ተኩስ ተካፍለዋል:: በኦሊምፒኩ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት የሚልቁ ስደተኛ ስፖርተኞች ደግሞ በተለያየ መልክ ድጋፍ እና እገዛ በኮሚቴው ተደርጎላቸዋል::
መሃሙድም የዚሁ እድል ተጠቃሚ በመሆኑ ዛሬ ላይ ህይወቱ ሊለወጥ ችሏል:: በስደተኛ ጣቢያው ባድሜንተንን ከማዘውተር አልፎ ክለቦችን እስከ መቀላቀልና በውድድሮችም እስከመሳተፍ ደርሷል:: በሂደትም ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ቡድን ተመርጦ በታላቁ መድረክ ራሱን አግኝቷል:: በመጨረሻም የልጅነት ህልሙ ስለተሳካለት ‹‹በህይወት ዘመኔ የማልረሳው፣ ማንም የማይነጥቀኝ ትውስታዬ ነው›› ሲል ስፖርት ያስገኘለትን እድል ይገልጻል::
ይህንን የተመለከቱ ሌሎች ዓለም አቀፍ የስፖርት ማህበራትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በሚያካሂዷቸው ቻምፒዮናዎች ላይ የስደተኞች ቡድንን ማካተት ጀምረዋል:: እርምጃውን ከወሰዱ ማህበራት መካከል አንዱ የዓለም አትሌቲክስ ሲሆን፤ እአአ በ2017 በተካሄደው የዶሃ ዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለስደተኞች የተሳትፎ እድል ሰጥቷል:: በዚህ ያላበቃው ማህበሩ ከቻምፒዮናው በኋላም ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠል ለሙከራ የሚሆኑ የስልጠና ፕሮጀክቶችንም መክፈት ችሏል:: የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋም በተመሳሳይ በስደተኞች ጉዳይ ላይ ከግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር የሚሰራ ራሱን የቻለ ድርጅት አቋቁሟል:: በዚህም በ78 አገራት ላይ የሚሰሩ 169 ግብረሰናይ ድርጅቶች በተለይ በህጻናት ስፖርት ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ይረዳል:: የወርልድ ቴኳንዶ እና የጁዶ ፌዴሬሽኖችም በሚመሯቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስደተኛ ቡድኑን ያሳትፋሉ::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም