ዛሬ ላይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና ምርምር ወደፊት የሚገሰግሱት እንደ ኮርያና መሰል በእድገት ላይ ያሉ አገራት ትምህርትን ለለውጥና እድገታቸው መሰረት አድርገዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ውሃ ብቻ ሳይሆን ትምህርትም ተጠምቶ የቆየ እንደመሆኑ፤ መንግስት ይሄን ታሳቢ ያደረገ ስራ ሲያከናውን ቆይቷል። የግል ኮሌጆች ወደዚህ ተግባር ሲገቡም ችግሩን የማቃለል እገዛ አድርገው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አዎንታዊ ተግባር አሉታዊ ገጽታዎችም አልጠፉትም።
በከፍተኛ የትምህርት ኢንቨስትመንት ውስጥ የግል ተቋማት እንዲገቡ ከተፈቀደ በኋላ በመጀመሪያ ዓመታት ውስጥ በጣት ከሚቆጠሩት ተቋማት በአሁን ወቅት 170 የሚደርሱ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ።
ይህ ዘርፍ ወደፊት እድገት እንዲያስመዘገብና የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ዘርፉ የሚመራባቸው ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ሲወጡ ቆይተዋል። እነዚህ ፖሊሲዎችና መመሪያዎችም በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ረቂቅ ስነስርዓት መመሪያ ላይ እንደተቀመጠው፤ አንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሚያሰለጥንባቸው ፕሮግራሞች ከተፈቀደውና ከተወሰነው ጊዜ በማሳጠር እያስተማረ ያለ ወይም ያስመረቀ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ የመመረቂያ መስፈርቶችን ያላሟላ ተማሪ ያስመረቀ ከሆነ የሚሰጠው ትምህርት ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም። ተቋሙ ይህን ተግባር ለመጀመሪያ ጊዜ የፈፀመ እንደሆነ አዲስ ተማሪ እንዳይቀበል ይደረጋል። በተጨማሪም የሶስት ዓመት እገዳ ይጣልበታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የግል የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስነምግባር በጠበቀ መንገድ እየተንቀሳቀሱ አለመሆኑ ይነገራል። በተለይ በአንዳንድ ተቋማት እውቅና ሳይኖራቸው ትምህርት መስጠትና የትምህርት ማስረጃዎችን መሸጥ ተጠቃሽ የስነምግባር ግድፈቶች ናቸው።
በዚህም፣ በአንድና ሁለት ወር ስልጠና የማስተርስ ዲግሪ ከመስጠት ጀምሮ፤ ያለ እውቅና ፈቃድ የመስራት፤ መስፈርቱን ያላሟሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር፤ በቂ ግብዓትና መምህር በሌለበት ከአቅም በላይ ተማሪ መቀበልን የመሳሰሉ ለትምህርት ጥራት ችግር የሚሆኑ ግድፈቶች በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስለመኖራቸው ይነገራል። በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የተከናወነ የዳሰሳ ጥናት እንዳመለከተው ከሆነ ደግሞ ምንም አይነት የማስተማር እውቅና
የሌላቸውና በሌላ ዘርፍ የስራ ፈቃድ የሚሰሩ ነገር ግን በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አሉ።
ለአብነትም፣ የንግድ ፈቃድ ተሰጥቷቸው በማህበር ያቋቋሙት አስመጪና ላኪ፣ ኮሚሽን ኤጀንት፣ ችርቻሮና ጅምላ፣ አገልግሎትና ኢንዱስትሪ፣ ግብርና፣ የማሽን ስራ ማቋቋምና መጠገን፣ የህክምና መገልገያ መሳሪያ ማምረት፣ ህክምና መስጠት፣ የኮሚሽን ወኪልነት፣ የንግድ ወኪልነት፣ የንግድ ደላላነት፣ እንደራሴነት ጅምላና ችርቻሮ፣ የመኪና ሞተር ብስክሌት ጥገና፣ የቤት ውስጥ ዕቃዎች፣ የሆቴልና ሬስቶራንት፣ ኮምፒውተር መሸጫና መጻህፍት መሸጫ፣ አደንና ሌሎችም ስራዎችን ለመስራት የንግድ ፈቃድ የተሰጣቸው ሆነው በማስተማር ስራ ላይ የተሰማሩ መኖራቸው ታውቋል።
ይህ ሂደት ደግሞ ትምህርት በአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ ሊያበረክት የሚገባውን ሚና እንዳያበረክት ብቻ ሳይሆን በዚህ መልኩ ሰልጥነው የሚወጡ ተመራቂዎች ወደስራ ኢንዱስትሪው ሲገቡ ትልቅ አገራዊ ጥፋትን የሚያስከትሉበት እድል ሰፊ እንደመሆኑ ችግሩን መቅረፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ምክንያቱም አንድ ሺ ተማሪ አስመርቆ ሜዳ ላይ ከመበተን 100 ተማሪ አስመርቆ ወደስራ ማስገባት የተሻለ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አገራዊ ፋይዳ አለውና። ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስነሥርዓት መመሪያ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ሰሞኑን ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ ረቂቅ መመሪያው የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንቅስቃሴ ሕጋዊ መሰረት እንዲኖረው፣ ጤናማ ውድድር እንዲኖርና ችግሮች ሲኖሩም ተጠያቂነትን ማስፈን ዓላማው ያደረገም ነው።
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ያለውን የማስተማር ችግሮች ላይ ሰሞኑን ውይይት አድርጓል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የሜዲሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቱ ዶክተር አረጋ ይርዳው እንደሚሉት፤ የመመሪያው መዘጋጀት ከመዘግየቱ በስተቀር እጅጉን አስፈላጊ ነው።
ምክንያቱም ትምህርት የዕውቀት መገብያ እንጂ ንግድ አይደለም። እናም በዚህ አግባብ እርምጃ ለመውሰድና ህግ ለማስከበር የተጀመረው ጉዞ ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ህግ የማስከበርና የማረቅ ሂደቱ ሌላ ገቢ ማስገኛ ዘርፍ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል። ኤጀንሲውም አሁን በጀመረው ሂደት ተጠናክሮ መሄድና ይሄንኑም አጠንክሮ በመተግበር የተሻለ መስመር ማስያዝ ተገቢ ነው። ለዚህም ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተሳተፉት አቶ እንዳልካቸው ስሜ እንዳሉት፤ ጅምሩ የሚበረታታ ነው። ይህ እርምጃም የግሉ ዘርፍ ያለውን ሚና እንዲወጣ የሚደረገውን ስራ የሚያግዝ ሲሆን፤ ጉዞው ግን የዘርፉን ባህሪ ተገንዝቦ መስራትን ይጠይቃል። ምክንያቱም የትምህርት ዘርፉ በርካታ ሴክተሮች ያሉት፤ በዛው ልክ የተለያዩ ግብዓቶችን የሚፈልግ እንደመሆኑ፤ ያንን ማስገባትም ሆነ ማስወገድ የሚቻልበትን እድል መፍጠር የግድ ይሆናል። እናም ሂደቱ አሳታፊ ሆኖ መጓዝ ይኖርበታል።
መመሪያው ችግሩን ለመፍታት ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ ኩዊንስ ኮሌጅን በመወከል የተገኙት አቶ ቶላ ገዳ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በኤጀንሲው በኩል ከፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮች ተለይተው መፈታት ይኖርባቸዋል።
ለምሳሌ፣ በግል ፍላጎትና ጥላቻ ወይም የተለየ ጥቅም ከመፈለግ አኳያ እስካሁን የተከሰቱ ችግሮች አሉ፤ በቀጣይም ይሄ ጉዳይ እንዳይካሄድ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል። ምክንያቱም በእስካሁን ሂደት መስፈርቱን ሁሉ አሟልተው አላሟሉም፤ ሳያሟሉም በባዶ ቤት አሟልተዋል እየተባሉ ፈቃድ ሲሰጣቸውና እድሳት ሲከናወንላቸው የነበረበትና ለዚህ ሁሉ ችግር መንስኤ የሆኑ አካሄዶችን ተገንዝቦ መስራት ይገባል።
የመካነ እየሱስ ተወካዩ አቶ ብሩክ አየለ በበኩላቸው እንዳሉት፤ አሁን የተጀመረው የመፍትሄ እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ቀደም ሲል ችግሩን ተረድተው ወደ መፍትሄ እርምጃ የገቡ ተቋማት አሉ። እናም ሂደቱ እነዚህን በሽግግር ላይ ያሉ ተቋማትን ከግምት ማስገባት ይኖርበታል። ከዚህ ባለፈም ሕጉ ማስፈራሪያ እንዳይሆን፤ ብቻውንም ውጤታማ ስለማይሆን ህጉን ላለመተግበር እንቅፋት የሚሆኑ የአሰራር ግድፈቶች (በተለይ ከስነምግባር ጋር የተያያዙ ችግሮች) እንዳይጋለጥም ቀድሞ ማሰብ ይገባል።
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምክትል ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ወንድወሰን ታምራት በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በመመሪያው ትግበራ ሁሉም አካል ባለድርሻ ነው። ምክንያቱም አፈጻጸሙ ሁሉን አቀፍ ካልሆነ እንደ ሌሎች መመሪያዎች ሁሉ በሼልፍ ከመዋል የሚያግደው ስለማይኖር ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።
ለምሳሌ፣ የቁጥጥርና ድጋፍ ስርዓቱ አሁን ያለውን ሁኔታ የለየ፣ የሽግግር ወቅቱን ያገናዘበና የቀጣይ ሂደቶችን የሚመለከት መሆን ይኖርበታል። የትምህርት ዘርፎችና ሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ፣ በፍቃድና በመመዘኛዎች ተመስርቶ መስራትም አስፈላጊ ይሆናል። ይሄን መሰል ኃላፊነት የመውሰድ ተግባራት ሲኖሩ ነው ውጤቱ ሊመጣ የሚችለው።
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱአለም አድማሴ እንደሚሉት ደግሞ፤ በእስካሁን ሂደት የተፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂው የኤጀንሲው፣ የትምህርት ተቋማቱና የህብረተሰቡም ጭምር ነው። ምክንያቱም ኤጀንሲው ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ፣ ተቋማቱም ባለው የህግ ማዕቀፍ መሰረት መስራት፣ ህብረተሰቡም በተቋማቱ የሚታየውን ግድፈት እንዲታረም የድርሻውን መወጣት ይጠበቅባቸው ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሳይሆን ያለ እውቅና ሲሰሩ፣ በአንድና ሁለት ወርም በማስተርስ ሲያስመርቁ ቆይተዋል። የመመሪያው አስፈላጊነትም እነዚህ ተቋማት ለአገር ማበርከት ያለባቸውን ድርሻ ሳያበረክቱ ተሸማቅቀው ወደኋላ እንዳይቀሩ የሚያስችል የአሰራር ማዕቀፍ ለማበጀት ሲሆን፤ በዘርፉ የሚታየውን ችግር በመፍታት በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር እድል የሚሰጥ ነው።
ከዚህ አኳያ ሁሉም አካል ይሄን ጊዜ ሳያጠፋ ሊጠቀምበት ይገባል። ምክንያቱም አሁን ላይ ህዝቡ የሰጠውን እምነት በመጠቀም የሚፈልገውን መስራትና ጊዜውን እንደ ሽግግር ወቅት መጠቀም ይገባል። ካልሆነ ግን ህዝብ ተስፋ ከቆረጠ በኋላ እምነቱን መመለስ ይከብዳል። መንግሥት ባለበት አገርም ችግሩ ሊቀጥል አይገባውም። መመሪያውም አስፈላጊው ግብዓት ተካትቶበት በቅርቡ ጸድቆ ወደስራ ስለሚገባ ተጠያቂነቱም አብሮ ይከተላል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2011
በመርድ ክፍሉ