ዛሬ በገበያ ላይ የሚገኙት እንደ ሙዝ፣ ማንጐ፣ አቦካዶ፣ ብርቱካን፣ ፓፓያና አፕል የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በነጋዴዎች፣ በሃይማኖት ቡድኖችና በውጭ ኃይሎች ነው ተብሎ ይታመናል። አብዛኛዎቹ አገር በቀል ፍራፍሬዎች ወፍ ዘራሽ ወይም ከጫካ የሚገኙ ናቸው።
ለገበያ የሚሆን ሰፋፊ የፍራፍሬ ምርቶች በተለይ ሙዝና ብርቱካንን ማልማት የተጀመረው በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግሥት ነው። የደርግ መንግሥት ደግሞ ሁሉንም ሰፋፊ የፍራፍሬ ተክል ልማቶችን ወረሰ። የተወረሱት ደግሞ ለመንግሥት እርሻዎችና ለአነስተኛ ገበሬዎች ተሰጡ።
ገሚሶቹ አገልግሎት መስጠት አቆሙ። በማረሚያ ቤቶች አካባቢ ያሉ የፍራፍሬ ልማቶች ቢበረታቱም ምርቱ ግን ማሽቆልቆሉ አልቀረም። አሁን ደግሞ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል። ሰፋፊ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለማካሄድ ከተለያዩ የውጭ አገር ባለሀብቶች ጋር የጋራ ስምምነቶች የተደረጉ ሲሆን አብዛኞቹም የውጪ ገበያን መሠረት ያደረጉ ናቸው።
መንግሥት አነስተኛ ፍራፍሬ አምራች አርሶ አደሮችን ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ ያበረታታል። መንግሥት በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ በሚገኙ ችግኝ ማፍያዎች አማካይነት የተሻሻሉ የችግኝ ምርቶች ላይ ወጪ እያደረገ ይገኛል።
የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪና የግብርና ምርምር ማዕከላት ለጥረቱ እገዛ ያደርጋሉ። ግብርና ሚኒስቴር ከግልና ከመንግሥት የሚዲያ ኃላፊዎች ጋር ሚያዝያ 3 እና 4 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው የምክክር መድረክ ማጠቃለያ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በመስኖ የለሙ የአትክልትና ፍራፍሬ ማሳዎች እና የተቀናጀ የዓሳና የዶሮ ዕርባታ ሥራዎች ተጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት እንደተገለፀው በምስራቅ ሸዋ ዞን በአስር ወረዳዎች 75 ሺህ ሄክታር መሬት
በመስኖ በማልማት 74 ሺህ 501 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በፍራፍሬ አንድ ሺህ 312 ሄክታር የለማ ሲሆን፣ በአቦካዶ ክላስተር ደግሞ 15 ሄክታር መሬት እንዲለማ ተደርጓል። በተጨማሪም በምስራቅ ሸዋ ዞን በአድአ ወረዳ የግብርና እድገት ፕሮግራም ድጋፍ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ 17 ሺህ 153 አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እየሆኑ ሲሆን፣ በወረዳው ባሉ በ22 ቀበሌዎች በአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ተቋማት ግብዓት በማቅረብ እና የገበያ ማዕከላትን በተመለከተ ለአርሶ አደሩ ሥልጠና በመስጠት፣ አዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ የግብርና ግብዓቶችን በመገንባትና በመስኖ ሥራ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል።
በአደዓ ወረዳ ጎዲኖ ቀበሌ አሳና ዶሮን አጣምሮ በማርባት የዶሮ ኩስን ወደ ኩሬ በመልቀቅ ለዓሣዎች መኖ እንዲሆን እና ውሃውን በአትክልትና ፍራፍሬ ማሳ ላይ በመልቀቅ እንደማዳበሪያ እንዲያገለግል በባቱ የዓሣ ምርምር ተቋም ድጋፍ ተደርጎላቸው ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮችን ሥራም ታይቷል።
በኦሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የፍራፍሬ ዳይሬክተር አቶ ተገኝ ኢረና እንደሚናገሩት፤ የፍራፍሬ ክላስተር ሲባል አቦካዶ ብቻ ሳይሆን ፓፓያና ሙዝን ይጨምራል። ቀደም ብሎ ምስራቅ ሸዋ የሚታወቀው በሽንኩርትና በቲማቲም ምርት ነበር።
እንደ አገር አርሶ አደሩ በአንድ ምርት ብቻ እንዳይቆዩ በተደረገው ጥረት ፍራፍሬም እንዲያመርቱ በተሠራው ሥራ ፓፓያ በአንድ ሰው ብቻ 12 ሄክታር እንዲተክል ተደርጓል።
በምርምር የተገኙ ድቅል የፓፓያ ችግኞች እንዲስፋፉም ተደርጓል። በአቦካዶ ላይም በተመሳሳይ ተሠርቷል። የፍራፍሬ ምርት ማሳደግ በክልል ደረጃ የተጀመረው 2009 ዓ.ም ላይ ነበር። በተሠራው ሥራም ውጤት ተገኝቶ አርሶ አደሮቹ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ልከዋል። በዘንድሮም ምርት የደረሰላቸው አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ይልካሉ።
አብዛኛው የፍራፍሬን ምርት ቀደም ብለው የጀመሩት ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ ውስጥ እና ጅማ አካባቢ ነው። ወደ ምስራቅ ሸዋ የማስፋፋት ሥራው በቅርብ የተጀመረ ሲሆን፣ በክላስተር ተደራጅተው በሰፊው የሚያለሙ ሰዎች ተይዞ ወደ ገበያ የሚገቡበትና የሚወዳደሩበት ሁኔታ ለመፍጠር ውጤታማ ሥራ ተከናውኗል።
ይህን ለማድረግ ደረጃውን የጠበቀ ከችግኝ ጣቢያ የሚፈለገው ዝርያ አግኝቶ የሚሠሩበት ሁኔታ ተመቻችቷል። በፊት ችግኝ የማግኘት ችግር ነበር። የችግኝ ችግር ለመፍታት በግብርና ሚኒስቴር ተባባሪነት በጅማና በምዕራብ ወለጋ የችግኝ ጣቢያ ተከፍቷል። ከጣቢያዎቹ ተዳቅለው የሚመጡት የአቦካዶ ችግኞች የስድስት ወራት ናቸው። ከተተከሉ ሁለት ዓመት ሳይሞላቸው እያበቡ እንደሚገኙ አቶ ተገኝ ያስረዳሉ።
በክልል ደረጃ ከአታክልት ደግሞ ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አርሶ አደር ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት እንዳለ የጠቀሱት አቶ ተገኝ፤ በዚህ ፕሮጀክት የተሰራው ቢታይ ሽንኩርት 116ሺ፣ ድንች 189 ሺ እና ቲማቲም 99 ሺ አካባቢ አርሶ አደር ተጠቃሚ መሆኑን ይናገራሉ። በአትክልት ልማት በአራት ዓመት ውስጥ በመስኖ እየለማ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ተገኝ አባባል፤ በመስኖ ልማት ይሁን በክላስተር አደረጃጀት ላይ ሙያዊ ድጋፍ ያስፈልጋል። ሥራው ጥረት ካልተደረገበት ማሳካት አይቻልም። ድጋፍ ለማድረግ ለአርሶ አደሩ በሚመች ሁኔታ ፓኬጅ ተዘጋጅቷል። ስለ ፓኬጁ ለልማት ሠራተኛውና ለወረዳው ባለሙያዎች ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
በዚህ መንገድ ድጋፍ ይደረጋል። ነገር ግን ምርቶቹ ሲተከሉ ቅድሚያ ቦታ ይመረጣል፣ የሥነ ምህዳሩ ተስማሚ መሆኑ ይጠናል፣ ውሃና ማዳበሪያ ያስፈልጋል። አቦካዶው ሁለት ዓመት እስኪፈጅ አርሶ አደሩ ሥራ እንዳይፈታ መሀል መሀል ላይ የሚተክላቸው ምርቶች ይሰጡታል።
ነገር ግን አቦካዶ የተተከለበት ቦታ እንዲተከሉ የማይፈቀዱ ምርቶች አሉ። ለምሳሌ ቲማቲም፣ በርበሬ እና ቃሪያ አይተከሉም። የሚተክሉት ይሰጣቸዋል። በምስራቅ ሸዋ አካባቢ የሚገኘው መሬት አሲዳማነት ባህሪ ስላለው ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ ድጋፍ ይደረጋል። አርሶ አደሩ በስፋት ማዳበሪያ መጠቀም ግዴታው ነው። ሌላው ውሃ ሲያጠጣ አቦካዶ ተክሉ አካባቢ ቀለበት ሰርቶ መሆን አለበት ምክንያቱም የአቦካዶ ስሩን ካገኘው በሽታ ሊያጠቃው ይችላል።
አርሶ አደር ተስፋዬ በዳዳ ምስራቅ ሸዋ ሉሜ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ የአቦካዶ ምርት በማሳቸው ላይ ተክለዋል። በአሁን ወቅት ከተተከሉት አቦካዶ ፍሬ ያፈራም አለ። የአቦካዶ ፍሬ ማፍራት የጀመረው ተክሉ ለአየር ንብረት የተስማማ ሲሆን የመጀመሪያ የተዘራ ጊዜ ከአንድ አቦካዶ ተክል ሶስት ኩንታል አግኝተዋል። ምርቱ እየበዛ ሲሄድ እስከ አምስት ኩንታል ድረስ ይገኛል።
አሁን አንድ ነጥብ ሁለት ሄክታር አቦካዶ የዘሩ ሰሆን የገበያ ሁኔታው የሚመቻች ከሆነ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የማግኘት ተስፋ አላቸው። ምርቱ ከደረሰ በኋላ የገበያ ሁኔታውን እራሳው እያመቻቹ ሲሆን በቀጣይ ግን የወረዳው ግብርና ፅህፈት ቤት ገበያ እንደሚፈልግላቸው ቃል ገብቶላቸዋል።
ፅህፈት ቤቱ ምርጥ ዘር በመስጠትና በማማከር እገዛ እያደረገ ይገኛል። የግብርና ባለሙያዎች በየቀኑ እየመጡ ውሃ በማጠጣት፣ ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ እንዲሁም ምርት እንዲበዛ ተክሉ እንዲገረዝ ምክር ይሰጣሉ። በተጨማሪም የአቦካዶ ተክል ቀምበጥ ለተደራጁ ወጣቶች በመሸጥ እንዲያዳቅሉ ይደረጋል። አጠቃላይ በክላስተር እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤታማ ነው።
የዓድዓ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ከበደ እንደሚሉት ከሆነ ወረዳው በስፋት በጤፍ ምርት የሚታወቅ ሲሆን፣ ምርቱን ለማምረት ዝናብ በመጠበቅና በመስኖ ያለማል። ለመስኖ ልማት በልበላ ወንዝን እንደሚጠቀም በመጥቀስ፤ በበጋ መስኖው 16 ቀበሌዎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በወረዳው የሚገኙ 22 ቀበሌዎች የግብርና እድገት ፕሮጀክት ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ።
የወረዳው የግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከተማ ነጋሽ፤ በ2003 ዓ.ም ላይ አርሶ አደሩ የመስኖ ተጠቃሚ እንዲሆን ፕሮጀክት ተቀርፆ መጀመሩንና በወቅቱ በመስኖ ልማት 209 ሄክታር ማልማት መቻሉን ይናገራሉ። በአሁን ወቅት በመስኖ 511 ሄክታር መሬት በማልማት አንድ ሺ አርሶ አደር ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2011
በመርድ ክፍሉ