እአአ 2016 ላይ አልዩ የሱፍ በናይጄሪያ ከሚኖርበት ከተማ ተሰዶ ካምፕ ከመድረሱ በፊት ረሀብን የሚያስታግስ መድሃኒት ወይም ታርማዶል ምንነት አያውቅም ነበር፡፡ አልዩ በካሜሮን ድንበር አካባቢ ከምትገኘው ጎአዛ የተሰደደው ቦኮሀራም በአካባቢው ባደረሰው ጥቃት ነበር፡፡ አንድ ጠዋት በማዲንቱ ካምፕ ውስጥ 500 የሚሆኑ ስደተኞች የሚበሉት ምግብ አጥተው ይሰቃያሉ፡፡ ስደተኞቹ ረሀባቸው እንዲታገስላቸው ከመሀላቸው አንዱ ታርማዶል የተባለውን መድሃኒት ሲሰጣቸው የረሀብ ስሜታቸው ይጠፋል፡፡ ከዚህ ሁኔታ በኋላ ስደተኞቹ የታርማዶል ሱሰኞች ሆኑ።
የሱፍ እንደሚለው ከታርማዶልውጭ ባዶነት ይሰማዋል፡፡ ማንኛውንም የረሀብም ሆነ የህመም ስሜት ለማስታገስና ጠንካራ ለመሆን የግድ መድሃኒቱን መውሰድ እንዳለበት ይናገራል፡፡ በማንዲቱ ስደተኞች ካምፕ በታርማዶል ሱሰኛ ከሆኑ ሰዎች መካከል የሱፍ አንዱ ነው፡፡ የህመም ስሜቶችን ለማጥፋት የሚረዱ ብዙ መድሃኒቶች አሉ፡፡ መድሃኒቶቹ ከፍተኛ የሆነ የማነቃቃት ባህሪ ስላላቸው ልክ እንደ ሄሮይን ዕፅ ሱሰኛ ያደርጋሉ፡፡
ልክ እንደ የሱፍ አብዛኛዎቹ ሰዎች መድሃኒቱን የለመዱት ወደ ማዳንቱ ስደተኛ ካምፕ ከመጡ በኋላ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ እንደሚናገሩት ከሆነ የመድሃኒቱ ሱሰኛ የሆኑት በቦኮሀራም ጥቃት ወቅት የተፈጠረባቸውን መረበሽ ለመርሳትና በስደተኛ ካምፕ ውስጥ ያለውን ህይወት ለመልመድ ነው፡፡ የ23 ዓመቱ ሼቲማ ሁለት ወንድሞቹ እአአ 2015 በባማ ከተማ ቦኮሀራም ባደረሰው ጥቃት ተገድለዋል፡፡ እሱ እንደሚለው ታርማዶል እየወሰደ ምንም ቢፈጠር አይጨነቅም ምክንያቱም ችግር ቢመጣ ታርማዶል ያስወግደዋልና ነው፡፡
እአአ 2015 ላይ ታርማዶል ሳይታወቅ በፊት የስደተኞች ካምፕ ብጥብጥ ይፈጠርበት ነበር፡፡ ነገር ግን ነዋሪዎቹ የቦኮሀራምን አሰቃቂ ድርጊት ለመርሳት አደንዛዥ መድሃኒት መጠቀም ግድ ይላቸው ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ታርማዶል ብቸኛ ምርጫ ሆኖላቸዋል፡፡ የመድሃኒቱ ሻጮች ታርማዶል ማንኛውንም ስሜት የሚያጠፋ መድሃኒት ስለመሆኑ በካምፑ አካባቢ ሲያወሩ መስማቷን የምትናገረው ሀዋ ሳሊሁ ነች፡፡ ሀዋ እአአ 2015 ቦኮሀራም ዳምቦአ ከተማ ባደረሰው
ጥቃት የተፈናቀለች ስትሆን የነበረውን አሰቃቂ ሁኔታ ለመርሳት መድሃኒቱን ትጠቀማለች፡፡
የቀድሞ የቦኮሀራም ተጠላፊ የነበረውና በማዲያንቱ ካምፕ ታርማዶልን ያስተዋወቀው የ19 ዓመቱ አዳሙ ሙሳ ነው፡፡ አዳሙ በቦኮሀራም ተይዞ ለወራት የቆየ ሲሆን በወቅቱ ከጉዋዛ አካባቢ እሱና ሌሎች ወጣቶች ተጠልፈው ነበር፡፡ በተጠለፈበት ወቅት ሙሳ የቦኮሀራን ጦር ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን በወቅቱ በማህበረሰቡ ላይ ጥቃት ከመሰንዘር ጀምሮ በእሱ እድሜ ያሉትን ወጣቶች ይጠልፍ ነበር፡፡
በቦኮሀራም ካምፕ በነበረበት ወቅት ወደ ማንኛውም ግዳጅ ከመወጣቱ በፊት ታርማዶል ይዋጥ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በዚህ ሁኔታ የታማዶል ሱሰኛ የሆነ ሲሆን ከቦኮሀራ አምልጦ ወደ ስደተኞች ካምፕ ሲመጣ ለሌሎች ሰዎች አስተላለፈ፡፡ ሙሳ እንደሚለው፤ በካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በአዕምሯቸው ያለውን ነገር እንዲረሱ ይፈልጋል፡፡ ለዛም የታርማዶል መድሃኒት ቢወስዱ በዓለም ቁንጮ ላይ እንደሚቀመጡ ይሰብክ ነበር፡፡
በስደተኞች ካምፕ ማንኛውንም አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡ ብሄራዊ የፀረ አደንዛዥ ዕፅ ኤጀንሲ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በስደተኞች ካምፕ አካባቢ ዕፅ የሚጠቀሙና የሚሸጡ 19 ሰዎች ላይ እርምጃ ወስዷል፡፡ በማድጉሪ ካምፕ ባኪሲ እና ሞጎሊስ መንደሮች ላይ የሚገኙ ስደተኞች ዕፅ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ የቡርኖ ከተማ አስተዳደር እንደገለፀው ከሆነ ማንኛውም በስደተኞች ካምፕ የሚኖር ሰው ከአደንዛዥ ዕፅ ነፃ አይደለም፡፡
ታርማዶል በስደተኞች ካምፕ አካባቢ የተለመደ መድሃኒት ሆኗል፡፡ የእርዳታ ድርጅት ሰራተኞች እንደሚናገሩት፤ መድሃኒቱ በሚያመጣው የጎንዮሽ ችግር ብዙ ስደተኞች እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በማዲያንቱ ካምፕ እና አቅራቢው ካለው ቡሉሙኩቱ የስደተኞች ካምፖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በካፕሪኮርን እድገትና ሰላም አምጪ ድርጅት ውስጥ አማካሪና የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ የሆነው ጀብሪን ቡካር፤ በማዲያንቱና እና ቡሉሙኩቱ ስደተኞች ካምፕ ታርማዶልን የሚወስዱ ሰዎች በመሳደብ፣ በመበጥበጥና ሴቶችን ለመድፈር ሙከራ በማድረግ በተደጋጋሚ እንደሚከሰሱ ይናገራል፡፡ እሱ የሚሰራበት ድርጅትም በሱስ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችንና የሰዎች ዝውውር ተጠቂዎችን ይደግፋል፡፡
ጅብሊን እንደሚናገረው፤ የመድሃኒቱ ሱሰኞች የመፍራት፣ የመጨነቅና አንዳንዴም የባህሪ መቀያየር በማሳየት ከፍተኛ የሆነ የመጣላት ስሜት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በቡሉሙኩቱ መቶ የሚሆኑ ስደተኞች በአንድ ላይ በተጨናነቀ አየር ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ በዚህም የ36 ዓመቷ ማሪያ የታርማዶል መድሃኒት ተጠቃሚ ስለሆነች ለከፍተኛ ጭንቀት መጋለጧ ምልክቶች እየታዩባት ይገኛል፡፡
መድሃኒቱን መጠቀም የጀመረችው በካምፕ ውስጥ ያሉት ዜጎች ምግብ ለማግኘት የሚያደርጉትን ትግል ካየች በኋላ ነው፡፡ ማርያ ‹‹ አዎ መድሃኒቱን ስወስድ እንድረጋጋ ያደርገኛል፡፡ ነገር ግን ያሉኝን ነገሮች ይወስድብኛል›› ብላለች፡፡ ማንም ሰው ስለ መድሃኒቱ ጎጂነት ሊመክር መምጣት እንደሌለበት ትናገራለች፡፡ ያላትም ገንዘብ በሙሉ ታማዶልን ለመግዛት ታውላለች፡፡
መድሃኒቱ ከማንኛውም መድሃኒት መሸጫ ሱቅ በ30 ሳንቲም አስር ፍሬ መግዛት ይቻላል፡፡አብዛኛው መድሃኒት 225 ሚሊ ግራም አቅም ያለው ሲሆን በሌሎች አገራት ከሁለት ጊዜ በላይ መድሃኒቱን መውሰድ አይቻልም፡፡ የታርማዶል ተጠቃሚዎች ዓለም አቀፍ ህጎችን ያልተከተለ ምርት መጠቀምና ለደቡብ እስያ አገራት በተለይ ወደ ህንድ በማሰራጨት ከፍተኛ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት 90 በመቶ የመድሃኒት ምርት በታርማዶል የተያዘ ነው፡፡ በተለይ በምዕራብ፣ መካከለኛና ሰሜን አፍሪካ በብዛት ይስተዋላል፡፡ የናይጄሪያ ባለስልጣናት ህገወጥ የመድሃኒት ዝውውርን ለመከላከል ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ስራ ጀምረዋል፡፡
በተሰራው ስራም ወደ 600 ሚሊዮን የመድሃኒት እንክብሎችን በአገሪቱ ወደብ ይዘዋል፡፡ ነገር ግን በናይጄሪያ ድንበር አካባቢ መድሃኒቶች በህገወጥ መንገድ ከአገሪቱ እንዲወጣ ይፈቅዳሉ፡፡ በተለይ ከቤኒን መድሃኒቶች በህገወጥ መልኩ እንዲገቡ ያደርጋሉ፡፡ በናይጄሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መረጃ ናይጄሪያ ታርማዶልን ወደ ህንድ በመሸጥ ከዓለም ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛ አገር ነች፡፡
በቡርኖ ከተማ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆነው የሱፍ መሀመድ፤ አብዛኛው በስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚገኙት ስደተኞች የታርማዶል መድሃኒት ተጠቃሚነታቸው እያደገ የመጣው መድሃኒቱን በህገወጥ መንገድ ስለሚገዙ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የቡርኖ ከተማ በመድሃኒት ሱሰኛ የሆኑ ስደተኞችን፣ በህገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ ዜጎችን እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸውን ዜጎች ይረዳል፡፡ በህገወጥ መንገድ ታርማዶልን የሚነግዱ ሰዎች በስደተኞች ካምፕ ከፍተኛ ገበያ አግኝተዋል፡፡
በአጠቃላይ በናይጄሪያ ያለው የመድሃኒት ሽያጭና ተጠቃሚነት አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የአውሮፓ ህብረት የመድሃኒትና የጤና ጥናት እንደሚያሳየው፤ በናይጄሪያ 14 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ህዝብ ወይም 15 በመቶ የአገሪቱ ዜጋ በወጣትነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ማለት በዓለም ከሚገኘው የወጣት ብዛት አምስት ነጥብ ሶስት በመቶው ሲሆን ይህ ወጣት ክፍል ማሰብና ምርታማነት ላይ የሚገኝ ዜጋ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ በናይጄሪያ ከሚገኘው ወጣት ውስጥ አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮኑ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ታማዶልን ይጠቀማሉ፡፡
“በስደተኞች ካምፕ አካባቢ የመድሃኒት ጥገኝነትን መቀነስ ከተቻለ ሰላም ማምጣትና የመድሃኒት ህገወጥ ሽያጭን ያስቆማል፡፡ በናይጄሪያ የሚገኙ ፋርማሲዎች ታማዶልን ሲሸጡ የሀኪም ማስረጃ መጠየቅ አለባቸው፡፡ በተጨማሪም በድንበር አካባቢ ያለው ቁጥጥር የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ እነዚህን ነገሮች መተግበር ካልተቻለ በአገሪቱ የተጀመረው ዘመቻ ሊሳካ አይችልም” ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2011
በመርድ ክፍሉ